Translate

Thursday, September 27, 2012

በመተማ ከአቶ መለስ ሞት ጋር በተያያዘ ከ120 በላይ ሰዎች ታሰሩ


ኢሳት ዜና:-ኢሳት እንዳረጋገጠው በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ ከተማ በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ደስታችሁን ገልጣችሁዋል የተባሉ ከ120 በላይ ሰዎች ታስረው ስቃይ እየደረሰባቸው ነው።
የመተማ አካባቢ ነዋሪዎች   እንደገለጡት አቶ መለስ ዜናዊ ሞታቸው እንደተሰማ ” መለስ እንኳንም ሞተ፣ ተገላገልን” በማለት በመጠጥ ቤቶች ውስጥም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ደስታቸውን ገልጠዋል የተባሉ ከ120 በላይ ሰዎች ታስረዋል።
ግለሰቦቹ ታስረው ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እና ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪዎች ፣ እስረኞቹ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውም ታውቋል።
በዚሁ ዞን በጃን አሞራ ወረዳ ውስጥ የሚኖረው የኢህአዴግ አባልና ባለስልጣን የሆነው አቶ ዳምጠው ሞገስ ለኢሳት እንደተናገረው፡ ኢህአዴግ በእያንዳንዱ ቀበሌ ከ200 እስከ 400 የሚደርሱ አባሎች ወደ ወረዳና _ ወደ ዞን በመሄድ ሀዘናቸውን እንዲገልጡ  መመሪያ አውርዶ ነበር።
የአካባቢውን ህዝብ አስተባብሮ ለአቶ መለስ ዜናዊ  ሀዘናቸውን እንዲገልጡ ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው ወጣት በጉዳዩ ዙሪያ ከኢሳት ጋር ቃለምልልስ አድርጓል።
የተሻለ ለቅሶ ለማሳየት ወይም ከሌሎች ወረዳዎች አንሶ ላለመገኘት ወረዳዎች ፉክክር ውስጥ ገብተው እንደነበር አስተባባሪው ገልጧል
ዋናዉ ተፈላጊዉ ነገር ወረዳዎች ሀዘናቸውን በበቂ ሁኔታ አልገለጡም ተብለው እንዳይገመገሙ ነበር ያለው አስተባባሪው፣ እርሱ እና ባልደረባው “አባይን የደፈረ መሪ ፣ ለራሱ ያልኖረ መሪ” የሚሉ ከዞን ተዘጋጅተው የመጡ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ገልጧል
ለሀዘን የወጣው ህዝብ ሀዘኑን ገልጦ ሲጨርስ ከ64 ብር እስከ 700 ብር የሚደርስ ገንዘብ መቀበሉንና እርሱም እንደ ወረዳ ካቢኔ አባላት ሁሉ ከፍተኛው ተከፋይ እንደነበር  የተቀሰው አሰተባባሪው: በአበል ክፍያ የተነሳም ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር አጋልጧል
ከአቶ ዳምጠው ሞገስ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለምልልስ በድረገጻችን ላይ መከታተል ትችላላችሁ።

No comments:

Post a Comment