ኢሳት ዜና:-የችግሩ መንስዔ በከተማዋ የሚያልፈው የመንገድ ፕሮጀክት በሌላ በኩል በማለፉ ምክንያት ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃወሞውን ለማሰማት በመውጣቱ ነው።
ለህዝቡ የታውሞ ሰልፍ የመንግስት ተወካዮች ምላሽ እንሰጣለን ባሉት መሰረት የአካባቢው ነዋሪ ቀና ምላሽ እየጠበቀ ባለበት ሁኔታ < ምላሽ እንሰጣለን >ያለው መንግስት ያሰማራው ልዩ ሃይል በትናንትናው ዕለት ሰልፈኛውን ህዝብ በጅምላ በቆመጥ ሲደበድብ ውሏል።
የፖሊስ አባላቱ መውሰድ በጀመሩት ድንገተኛ የሀይል እርምጃ ህዝቡን በማስቆጣቱ ረብሻና ግርግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ያመለከተው የ ኢሳት ወኪል፤በዚህ ጊዜ ፖሊሶቹ ወደ ሰልፈኛው ጥይት መተኮሳቸውን ገልጿል።
በፖሊስ ጥይት የሞቱ እና የቆሰሉ ጥቂት አለመሆናቸውን ያመለከተው ዘገባው፤ የአካባቢው ፖሊስም ሆነ መንግስት እንኳን ስለሞቱት ሰዎች ቀርቶ ተከስቶ ስለነበረው ክስተት ምንም ነገር አለማለታቸው ህብረተሰቡን ይበልጥ እንዳበሳጨው ጠቁሟል።
በተለይ የተቃውሞው አስተባባሪዎች ናቸው በተባሉት የከተማዋ ወንዶች ላይ ከፍተኛ የሀይል እርምጃ መወሰዱን የጠቆመው ወኪላችን፤ እየተወሰደባቸው ያለው ድብደባና አፈና ሊገታ ባለመቻሉ አብዛኞቹ ወንዶች አካባቢያቸውን ለቅቀው መሰደዳቸውንና በከተማዋ ሴቶችና ህፃናት ብቻ መቅረታቸውን አመልክቷል።
ፖሊስ በህዝብ ላይ የወሰደው እርምጃ በመገናኛ ብዙሀን ባይዘገብም ወሬው በከተማዋ ዙሪያ ወዳሉ ወረዳዎች በስፋት የተዛመተ ሲሆን፤ የየወረዳዎቹ ነዋሪዎች የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ እየተቃወሙ መሆናቸውንና ችግሩ ወደ ሌሎች ወረዳዎች እየተስፋፋ መሆኑን የወኪላችን ዘገባ ያስረዳል።
No comments:
Post a Comment