አቤ ቶኪቻው
ወጣቱ ከአስረኛ ፎቅ ላይ ቁልቁል ተወረወረ። ትንሽ እንደሄደ ነፍሱ በሆዷ ከዚህ ላይ ወድቆ ላይተርፍ ነገር ምን አለፋኝ” ብላ ከስጋው ተለየች። እና ወደ ደመናው መሄድ ጀመረች። ስጋው ግን፤ “አይ አበሳዬ” ብሎ አስፋልቱ ላይ ፍጥፍጥ አለ።
የወጣቱ ነፍስ አስከሬኑ ግባ ከመሬት አስኪፈፀም ድረስ ከዳመና ዳመና እየዘለለች ቆየች እና የቀብር ቀን ሲደርስ ዝቅ ብላ በየሰዉ አናት ላይ እያንጃበበች ስለ ሬሳው የሚወራውን “ቡጨቃ” አዳመጠች። አብዛኛውን ሰው ከፎቅ የመፈጥፈጤ ምክንያት “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ነው” ብሎ በኪሱ ውስጥ ያስቀመጠውን ወረቀት አላመኑትም።
ያመኑትም ቢሆኑ እርምጃው አላደነቁለትም። አንደውም አንዳንዶቹ ሲያለቀሱ… “አንተ ምን ቤት ነህ… አንተ ምን ቤት ነህ… አንተ ጀነራል ነህ ሆይ…. አንተ ሚኒስቴር ነህ ሆይ እንኳን ሚኒስቴር ሚስቱስ ምን ሆኑ…? አንተ አካባጅ አንተ አካባጅ… ማበድህን መቼ አወኩ መታመምህን መች ሰማሁ… አልሰማሁምኮ አልሰማሁምኮ…” ብለው ሲያለቅሱ ብትሰማ ነፍሱ ተስፋ ቆረጠች።
ከመቼው ሄዳ ከመቼው እርሳቸውን አግኝታ በርሳቸው ምክንያት ስጋዋን እንደጃኬት አሽቀንጥራ ጥላ እንደመጣች ነግራ በአልቃሹ ዘንድ ያጣችውን ሞገስ ከእርሳቸው ልታገኝ ቸኮለች። ሳጥኑ መሬት ገብቶ የመጀመሪያው አካፋ አፈር እንደተወረወረ እየተጣደፈች ወደ ሰማይ ገሰገሰች።
የወጣቱ ነፍስ ሰማይ ቤት እንደደረሰች ማረፊያ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መቃኘት ጀመረች። ልታገኛቸው አልቻለችም። ማረፊያ ክፍሉ ከላይ ዳመና ከስር ዳመና ሲሆን ግራ እና ቀኙ ቪዲዮ የሚያሳይ ስክሪን ተገጥሞለታል። ከፊት እና ከኋላ ምን እንዳለ እንጃ፤ በግራ በኩል በሲኦል ያሉ ነፍሶች አበሳቸውን ሲያዩ በቀኝ በኩል ደግሞ በገነት ያሉ ነፍሶች ሃሴት ሲያደርጉ ቀጥታ ይተላለፋል።
ከአስረኛ ፎቅ ስጋዋን ፈጥፍጣ የመጣችው ነፍስ ከገነት የሚተላለፈውን ቀጥታ ስርጭት እየተመለከተች የሞተችላቸውን ሰውዬ መፈለግ ጀመረች። ብትመለከት ብትመለከት የሉም። ምናልባት ከስር በሚፃፈው ፅሁፍ ላይ “አባይን የደፈሩ ባለ ራዕዩ መሪ በገነት ውስጥ አቀበበል ተደረገላቸው!” የሚል ዜና ካለ ብላ መከታተል ጀመረች። ግን ምንም የለም። “ወይኔ ኢቲቪ ይግደለኝ!” ልትል አሰበችና ለካስ ሞታለች።
በገነት ውስጥ ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር ተረት ሲያወራ አንዲት እናት ነበር እና ልጆቿ ከበው ሲሰሙት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቀጭኔ አንገት ላይ ሆነው የሚመለከቱትን አየር ላይ ሲስሉ ሜሪ አርምዴ ጋሽ ጥላሁን ኬኔዲ መንገሻ እና ማይክል ጃክሰን… እየተቀባበሉ እየዘፈኑ አንበሳ እና ሚዳቋ ተቃቅፈው ሲወዛወዙ ተመለከተች። በሀሳቧም “እነዚህ አርቲስቶች ለባለ ራዕዩ መሪ ምንም አይዘፍኑም እንዴ…?” ስትል ራሷን ጠየቀች።
ሌላው የወጣቱ ነፍስ ግራ የገባት በገነት ውስጥ ያለውን ልማት በሚመለከት አንድም ዝግጅት አለማየቷ ነበር። ለስድስት ቀናት ያህል ከገነት የሚተላለፈውን ቀጥታ ስርጭት ስትከታተል ብትቆይም ስለ ጓድ መለስም ሆነ ስለ ልማት ምንም ሳይነገር መቆየቱ አስደመማት።
ከሰባት ቀን በኋላ ፍርድ ቤት ትቀርባለች። ስድስቱን ቀን የተከታተለችው የገነት ስርጭት ስድስት ደቂቃ ሳይመስላት ፊቷን ወደ ግራ አዙራ ከሲኦል የሚተላለፈውን ቀጥታ ስርጭት ማየት ጀመረች።
ስደሰትኛወ ድቂቃ ላይ ታከታት እንደምንም እያዛጋች ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ደረሰች። የሚታየው ነገር በሙሉ ወዝ ያለው ነገር አይደለም። ትልልቅ ሰዎች “አንተ… አንተ” እየተባባሉ በፀያፍ መልኩ ሲሰዳደቡ አንዱ በአንዱ ላይ ሲዝት “ጣትህን ነው የምቆርጠው ቂጥህን በሳንጃ እንዳልወጋው” ሲባባሉ ሰማች። ሰበተኛው ደቂቃ ላይ ፊቷን ወደ ቀኝ መልሳ የገነቱን ጣፋጭ ትዕይንት ልትከታተል ስትል አንገቷ አልዞር አላት። ለካስ እስካሁንም በርሷ ፈቃድ አልነበረምና ገነትን ስትኮመኩም የነበረችው። ወይ ግሩም…!
ለመሆኑ መለስ የት ናቸው? ገነት ውስጥ ለስድስት ቀናት አየች የሉም። ይኸው ዛሬ በሳተኛው ቀን ሲኦልን እየተመለከተች ነው። የሉም። ገና ፍርድ አላገኙ ይሆን ብላ ከፊቷ የተደረደሩትን ነፍሶች ለማስታወስ ሞከረች ሁሉንም አልፋ ስትሰለፍ አላየቻቸውም። ከኋላዋ ያሉትም በኋላ የመጡ ናቸው። ታድያ እርሳቸው የት ናቸው…? ይህንን እያሰበች በሲዖል ስክሪን ከስድድቦሹ መሃል አባን አየቻቸው።
እርሳቸው አይሳደቡም። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፎቶ ይዘዋል። ከኋላቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ልብ አለች። ከዛም ድምፅ ይሰማት ጀመር… “እንዳይመጡብን…!” እንዳይገቡብን…! ድርሽ እንዳይሉ እያሉብን” እያሉ ይፈክራሉ።
አዎ በሲዖል ታላቅ ተቃውሞ እየተደረገ ነው። ተቃውሞው መለስ እንዳይመጡብን የሚል ነው። ምክንያታቸው ምን ይሆን? ብላ የወጣቱ ነፈስ ስታስብ በድምፅ ማጉያ “ምክንያቱም እኒህ የምታያቸው በርሱ የተነሳ ከሲኦል የተወረወሩ ናቸው…” የሚል መለስ መጣ። “እንግዲያስ ገነት እማይገቡ…? ስትል አሰበች። በገደል ማሚቶ የታጀበ ሳቅ… አስተጋባባት። ቀጥሎም “በዛማ እርሱ ያስጠፋቸው ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አሮጊት እና ሽማግሌዎች እያሉ በየት አልፎ ይግባ እነርሱ ዝም ቢሉት አናብስቶቹ ዝም ይሉታልን…?” ብሎ ድጋሚ በገደል ማሚቶ አጀብ ሳቁ ቀጠለ…
የወጣቱ ነፍስ ከሲኦልን ቀጥታ ስርጭት ማየት ከጀመረች ጀምሮ ያለው ጊዜ ሰላሟን ነስቷታል…! ይሄኔ ስለ እርሳቸው ማሰቧን ትታ ስለራሷ ማሰብ ጀመረች…
ወድያውም፤ “በስራዬ የት ይሆን መግቢያዬ በስራዬ የት ይሆን መግቢያዬ…” የሚል በገና ሰማች። ቀጥሎም
የዋጋ ዝርዝር የሚል ፅሁፍ ተመለከተች።
“የገደለ ያስገደለ ራሱን ያጠፋ….. ዋገው ኪስ የማይጎዳ ሲኦል። በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር ጎጂ ባህል ነው።” ይላል።
No comments:
Post a Comment