Translate

Saturday, September 15, 2012

ወታደራዊ ሚስጥሮችን ለኦነግና ለኤርትራ አሳልፎ በመስጠት የተጠረጠሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተከሰሱ


-    አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ሚስጥር አሳልፈው መስጠታቸው ተጠቁሟል
በሚስጥር የሚጠበቁና በሕዝብ በይፋ የማይታወቁ ወታደራዊ ሚስጥሮችን ለኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) እና ለኤርትራ የደኅንነት ሠራተኞች አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል የተጠረጠሩ ሁለት የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሁለት ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች በመከላከያ የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮሌጅ የሰው ሀብት አመራር ቡድን መሪ ሻምበል ደበላ ሙለታ ዴንሳ፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የመዝገብ ቤት ኃላፊ በኃይሉ ነጋሽ፣ በደርግ ዘመን የደኅንነት ሠራተኛ ሆኖ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጸሐፊና ኦፕሬተር ሆኖ ይሠራ የነበረው ተሾመ መንግሥቱ (ሚስጥር ስም ታሪኩ) እና መቶ አለቃ ለማ በቀለ ይባላሉ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪው ተሾመ መንግሥቱ በ1996 ዓ.ም. ማዕሽ ገብረ እግዚአብሔር ከተባለ ኤርትራዊ ጋር ሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ ከተማ ውስጥ ይተዋወቃሉ፡፡ ማዕሽ ተሾመን በሚስጥር ስሙ ሰለሞን አስራት ከተባለ የኤርትራ የደኅንነት ሠራተኛ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር ያደርገዋል፡፡ ተጠርጣሪው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ በመሰብሰብ ለኦነግና ለኤርትራ መረጃ የሚሰጡ ከኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የደኅንነት ሠራተኞችን እንዲመለመል ተልዕኮ ይሰጠዋል፡፡ ተሾመ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ራሱ መረጃዎችን በመሰብሰብ ሲልክ መቆየቱ ተገልጿል፡፡ 


ክሱ እንደሚያብራራው፣ ተጠርጣሪው በተልዕኮው መሠረት ለመለመለው ሻለቃ ሰለሞን በላይ ከ300 እስከ 400 ብር እየከፈለው ከ1997 ዓ.ም. እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን ሲልክ ቆይቷል፡፡ በመቀጠል በመከላከያ ሚኒስቴር በመዝገብ ቤት ኃላፊነት ይሠራ የነበረውን በኃይሉ ነጋሽ የተባለውን ተጠርጣሪ፣ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በመተዋወቅና በመመልመል ስለሚሠሩት ሥራ ይስማማሉ፡፡ የመዝገብ ቤት ኃላፊው በሥራው አጋጣሚ በእጁ የገቡ በሚስጥር የሚጠበቁና በሕዝብ በይፋ የማይታወቁ በፊት ገጽ ሁለት ቦታ ላይ ክልክል የሚሉና ርዕሳቸው የወታደራዊ ትምህርት፣ የቅስቀሳና የቡድን መሣሪያ የተኩስ ልምምድ መመሪያ፣ የማዘዢያ ጣቢያ አመሠራረት፣ የሌሊት ውጊያ፣ የውጊያ ዝግጅትና የብቃት ደረጃ መለኪያ መመሪያ፣ በማውጫው አሃድን ለውጊያ በማዘጋጀት የአመራር ቅደም ተከተል የውጊያ ብቃት መሠረቶችና አሃድን ለውጊያ ለማዘጋጀት የሚደረጉ ተግባራት የሚሉ ርዕሶችን የያዘ ሰነድ፣ የዘመቻ ሪፖርት ሥርዓት፣ ወታደራዊ ምልክቶች፣ በማውጫው የሚስጥር ቃል አጠቃቀም የሚልና አምስት ርዕሶችን የያዙ ሰነዶች ለተሾመ መንግሥቱ አሳልፎ መስጠቱን ያስረዳል፡፡

ሌላው ተጠርጣሪው የመዝገብ ቤት ኃላፊ፣ የተሰጠው ተልዕኮ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ በቅርብ ጊዜ ያቀደችው ወታደራዊ ዕርምጃ መኖር አለመኖሩን እንዲያጣራ ሲሆን፣ ግለሰቡ ቅርበት ካላቸውና ወደ አካባቢው ለሥራ ከሚጓዙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በኤርትራ ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ እንቅስቅሴዎች እየተደረጉ መሆኑን በመግለጽ መረጃ መስጠቱን ክሱ ይገልጻል፡፡

የደርግ የደኅንነት ሠራተኛና በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጸሐፊና ኦፕሬተር የነበረው ተሾመ መንግሥቱ፣ ከኤርትራ መንግሥት በተላከለት ፋክስና ላፕቶፕ ተጠቅሞ በራሱና በመለመላቸው ሰዎች የተገኙትንና ለአገር ደኅንነት አስጊ የሆኑ መረጃዎችን፣ ከ1996 ዓ.ም. እጁ እስከተያዘበት ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በወር ከ500 ብር እስከ 700 ብር እየተከፈለው መረጃ ሲሰበስብና ሲያስተላልፍ እንደነበረ በክሱ ተገልጿል፡፡ ሁለቱም በዋና ወንጀል አድራጊነት የስለላ ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ያብራራል፡፡ እንዲሁም የመዝገብ ቤት ኃላፊው በፈጸመው የክህደት ወንጀልም ተከሷል፡፡

መቶ አለቃ ለማ በቀለ ኤጄታ የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ በኢትዮጵያና በዜጐቿ ላይ ጉዳት በሚያደርስና ለጦርነት በሚያሰጋ ሁኔታ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) አባልና በስዊዘርላንድ አስተባባሪ በሆነው ሁንዴሣ ዋቀሳ አማካይነት፣ የኤርትራ መንግሥት ተወካይ በመሆን ከኦነግ ጋር ከሚሠራው አሥራት አሰፋ ጋር መተዋወቁን ክሱ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪው በ1995 ዓ.ም. አስራት አሰፋ ከተባለው ግለሰብ ጋር በስልክ ከተዋወቀና አብሮ ለመሥራት ከተስማማ በኋላ አድራሻ በመለዋወጥ፣ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ጠለቅ ያለ ሚስጥር የሚያውቅ ሰው ሲያፈላልግ 25ኛ ክፍለ ጦር በነበረበት ጊዜ በፎቶግራፈርነት ይሠራ የነበረውን አሥር አለቃ መሳይ ታደሰን በ2001 ዓ.ም. እንደመለመለውና አብረው መሥራት መጀመራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ፎቶግራፈሩ የሠራዊቱን አሠፋፈር የሚያሳይ ካርታ፣ ወደ ግንባሩ የተጨመሩና የተቀነሱ የሠራዊት አባላትንና በግንባር ላይ ያሉ የሠራዊት ብዛት፣ የ25ኛ ክፍለ ጦር ሪፖርቶችን፣ የሰሜን ዕዝ 11ኛ ክፍለ ጦር ዛላንበሳ ግንባርና የ25ኛ ክፍለ ጦር ቡሬ ግንባር የሠራዊት አሠፋፈር ዝርዝር መረጃ፣ የሠራዊቱን አጠቃላይ ሪፖርት፣ ሠራዊቱ የሚጠቀምበትን የመሣሪያ ዝርዝር መረጃዎች በመሰብሰብ፣ በራሱ ስም በፖስታ ቤት ለመቶ አለቃ ለማ በቀለ እስከ ህዳር ወር 2003 ዓ.ም. ድረስ እንደላከለት በክስ ቻርጁ ተገልጿል፡፡ ፎቶግራፈሩ ለሠራበት ከ350 እስከ 1,500 ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ይላክለት እንደነበረም ተጠቁሟል፡፡ 

ፎቶግራፈሩ አሥር አለቃ መሳይ ታደሰ መረጃዎችን ማቀበል ሲያቆም መቶ አለቃ ለማ በራሱ ሚስጥር ናቸው የሚለውን መረጃ ቢልክም፣ ኤርትራዊው አስራት ተስፋ “መረጃቹ ሚስጥራዊ አይደሉም” በማለት ሌላ ሰው እንዲያፈላልግ በሰጠው መመርያ መሠረት፣ የመከላከያ የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮሌጅ የሰው ሀብት አመራር ቡድን መሪ የነበረውንና ተጠርጥሮ የተከሰሰውን ሻምበል ደበላ ሙለታን መመልመሉን ክሱ ያስረዳል፡፡

ሻምበል ደበላ ከተመለመለበት ከ2003 ዓ.ም. ክረምት ወር ጀምሮ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ ክፍለ ጦሮች ብዛትና በጦሩ ውስጥ ያለውን የሠራዊት ብዛት፣ በመከላከያ ኮሌጅ ውስጥ እየሠለጠነ ያለውን የሰው ሀይል ብዛት፣ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ሰላም ለማስከበር የሚሄዱ የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊዎችን ብዛት፣ ከማሠልጠኛ ኮሌጅ የተቀነሱና የከዱ የሠራዊት አባላት ብዛት፣ በመከላከያ ሚኒስቴር የተዘጋጀ የሠራዊቱ የአምስት ዓመታት ዕቅድ፣ የመከላከያ ሠራዊት ወርኀዊ መጽሔትና የኮሌጁ የሁለተኛ ዙር ተመራቂ የሠራዊት አባላት ብዛት ዝርዝር መረጃዎችና ደብዳቤዎችን በመሰብሰብ፣ በቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ እስከ 3,000 ብር እየተከፈለው መረጃዎችን ያቀብል እንደነበር ክሱ በዝርዝር ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በስለላ፣ በክህደትና ወታደራዊ ሚስጥርን በመግለጽ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸውን ክስ በመቃወም የመቃወሚያ ሐሳብ በማቅረባቸው፣ ዓቃቤ ሕግም የመቃወሚያ መቃወሚያ ሐሳብ በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ወገኖች ባቀረቡዋቸው የመቃወሚያና የመቃወሚያ መቃወሚያ ሐሳቦች ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

No comments:

Post a Comment