Translate

Sunday, September 30, 2012

“ወቅቱ ትርጉም ያለው ተሃድሶ፣ ዕርቅና ፍትሕ የሚመሠረትበት ሊሆን ይገባዋል!”


የጋራ ንቅናቄው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትመሠረት የምትችልበትን ፈጣንና ደፋር እርምጃዎች አቶ ኃይለማርያም እንዲወስዱ ይጠይቃል፡፡

ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
መ.ሣ.ቁጥር 1031
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
ውድ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም፤
ይህንን ደብዳቤ የምንጽፍልዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾምዎ የተሰማንን ለመግለጽ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓስርተ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ካስተዳደሩት ጠቅላይ ሚኒስትሮችEthiopian news አንድ ሶስተኛው የሚሆኑት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሥልጣን ሽግግር እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ምክንያት ከእነርሱ በፊት የነበረው ጠ/ሚ/ር በመሞቱ ምክንያት መሆኑን በውል የሚታወቅ ነው፡፡ እርስዎም በዚህ የሥልጣን ቦታ ላይ መቀመጥዎ ያልተጠበቀ የመሆኑ ያህል በፈጣሪ ምሪት የሚያሻው በመሆኑ ለአገራችን እውነተኛ ሰላም፣ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ዕርቅና ፈውስ ሊመጣ የሚያሻበት ወቅት ላይ በመሆናችን ይህንንም ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው“ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ” በመስጠት መሆኑን ስለምናምን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ እርስዎ የአገር መሪ ሆነዋል፤ ይህም ማለት እርስዎ መሪ የሆኑት ለወከልዎት ፓርቲ/ግንባር (ኢህአዴግ/ደኢህዴን/ህወሓት…) ወይም ከእርስዎ ጋር ለሚስማሙት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም ከእርስዎም ሆነ ከድርጅትዎ ጋር ለማይስማሙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መሪ ሆነዋል፡፡ በተለይ እነዚህ በተቃዋሚ ጎራ የተፈረጁት ግለሰቦች በእርስዎ ድርጅት “አክራሪ”፣ “አሸባሪ”፣ …ተብለው የተፈረጁ ናቸው፡፡ እናም የእነዚህ ሁሉ መሪ ነዎት፡፡ የሚሰጡት አመራርና ውሳኔ ደጋፊዎችዎን የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን በደጋፊዎችዎ ጎራ የሌሉትንም የሚመለከት መሆኑን የሚዘነጉት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት እንጂ የአንድ ጎሣ፣ ብሔር፣ ቡድን፣ ሃይማኖት፣ ድርጅት፣ ፓርቲ፣…ብቻ አይደለችም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መብት እንደገና ይጎናጸፉና ይለማመዱ ዘንድ እርስዎ የሚወስዷቸው ደፋር እርምጃዎችና ቀልጣፋ አመራሮች ወሳኝነት አላቸው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤
እንዲያውቁት ያህል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” በሚል መሪ ዓላማ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚታገል ከማንም ያልወገነ፤ በሰላማዊ ትግል የሚያምንና ያንንም የሚያራምድ፤ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚያቅፍና በበርካታ የዓለም ዙሪያ ቅርንጫፍ ያለው ድርጅት ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን በተለይ የተቋቋመበት ዓላማ እንደ ህወሓት ዓይነት በዘር ላይ የተመሰረተ የአርነት ንቅናቄ በማቋቋም ለጥፋት፣ ለብቀላ፣ ደርግን ለመጣል፣ አገራችንን ለመቆጣጠር፣ አገራችን ወደብ አልባ እንድትሆን ለማድረግ፣ እንደ አፓርታይድ ዓይነት የዘር የበላይነትን ለማስፈን፣ የኢትዮጵያን የአንድነት ስዕል “ህዝቦች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች” የሚል ሓሳዊ ስርዓት ለማካሄድ፣ የአንድ ጎሣ ወይም ዘር ወይም ቤተሰብ ወይም ግለሰብ የበላይነት ለማቋቋም ወዘተ የተካሄደውንና በመካሄድ ላይ ያለውን የማያቋርጥ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆምና ህወሓት በኢህአዴግ ስም በአገራችን ላይ ያደረሰውን ግፍ፣ መከራ፣ እስር፣ እንግልት፣ ግድያ፣ ስቃይ፣ … እልባት ለመስጠት ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው እነዚህን ሁሉ ለማከናወን አንድም ደም የማይፈስበት የሰላማዊ ትግል አማራጭ የሌለው መፍትሔና ለአገራችን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ዕርቅ ሊያመጣ እንደሚችል የጋራ ንቅናቄያችን አጥብቆ ያምናል፡፡ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት” ቅድሚያ ከሰጠንና የእያንዳንዳችን ነጻ መውጣት ከሁሉም ነጻ መውጣት ጋር የተያያዘ መሆኑን በማመን ከታገልን አዲሲቷ ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚያስቸግር ነገር እንደሌለ እናምናለን፡፡
ከዚህ በፊት በጭቆና ውስጥ የኖሩ ሁሉ ያንን ጭቆናቸውን እንደ ምክንያት በመቁጠር አሁን ደግሞ በተራቸው ሌሎችን ለመጨቆን፣ ለማሰቃየት፣ ለማስጨነቅ … ፈጽሞ እንደማይገባቸውና ይህንንም የሚያደርጉ ሁሉ በጥብቅ ሊወገዙ እንደሚገባቸው የጋራ ንቅናቄያችን የሚያምን ቢሆንም የኢህአዴግን ድርጅታዊ ካባ በመልበስ ህወሓት በአገራችን ላይ እስካሁን እያደረሰ የሚገኘው ይህ እንደሆነ ግን ሐቁ ይመስክራል፡፡ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ያመለከተ ወጣት “ለአማራዎች የሚሰጠው ኮታ ስለሞላ አታስፈልግም” ተብሎ ከችሎታው፣ ብቃቱና የትምህርት ማስረጃው ይልቅ የዘር ግንዱ ተቆጥሮ ከትምህርት ገበታ መከልከሉ እጅግ በርካታ ከሆኑት ተጠቃሽ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ የአንድ ሰው የዘር ማንነት የተለየ ጥቅም ሊያስገኝለትም ሆነ ሊያገኝ ከሚገባው ጥቅም ሊያስቀረው ፈጽሞ አይገባም! ይህ ሕገወጥ የሆነ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከግብረገብነትም ውጪ ነው፡፡ ለዚህ ነው “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” በማለት የጋራ ንቅናቄያችን አጥብቆ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ የሚሟገተው!!
ስለሆነም “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” እንድትመሰረት የቀደመችው ኢትዮጵያ መታደስ አለባት – ለአገራችን ተሃድሶ ያስፈልጋል የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ ይህም ተሃድሶ እኩልነትን፣ ሰላምን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ዕርቅን መሠረት በማድረግ “ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነትን በማስቀደም” ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ እኛን በተቃዋሚ ጎራ ያለነውን ስለሚጠቅም ለራሳችን በማሰብ የምናቀርበው ሳይሆን በቀደምት ስርዓቶችም ይሁን በአሁኑ እርስዎ በሚመሩት የኢህአዴግ አገዛዝ ሥር ለሚገኙት መብታቸው ለተነፈገ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም እርስዎንም ጨምሮ ለእያንዳንዱ የደኢህዴን፣ የኦህዴድ፣ የህወሓት፣ የብአዴን … ኢህአዴግ አባላትም ጭምር የሚጠቅምና ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ የኢትዮጵያ ፈውስ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ መንፈስ የምትመሰረተው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዘረኝነት የመከነባትና ከፈጣሪ የተሰጡ መብቶች የተከበሩባት እንደምትሆን እንደ እርስዎ ያለ መንፈሳዊ ሰው በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤
በልጅነቱ ሐኪም የመሆን ሕልም የነበረውና ከወንድሙ ጋር ወደ ትምህርት ቤት በኪሎሜትሮች የሚቆጠር ርቀት በመጓዝ ትምህርቱን የተከታተለው የቦሎሶሬው ወጣት ዛሬ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ብሎ ያሰበና የገመተ ማን ይሆን? ከፈጣሪ ዕቅድ ውጪ ይህንን ሊያስብ የሚችል አንዳችም ፍጡር የለም፤ ስለሆነም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ባማረ የአበባ ስፍራ በምትመሰለውና እያንዳንዳችንም አንድ ውብ አበባ በመሆን ትልቁን የኢትዮጵያን እርሻ የምናሳምርባት አገራችን መሪ መሆንዎ እንደ ንግሥት አስቴር ፈጣሪ ለዚህ ጊዜ ለምክንያት ያደረገው ይሆን?
ለአገራችን የምናስበውም ሆነ የምናቅደው ዓላማ በቀና ኅሊና፣ ፍቅርንና እውነትንና ነጻ አስተሳሰብን መሠረት ባደረገ መንፈስ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በጋራ ንቅናቄያችን እምነት በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገን ዋንኛው “ትራንስፎርሜሽን” ከሁከት ይልቅ ውይይት፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከብቀላ ይልቅ ይቅርታ ነው፡፡ ይህንንም ጉዳይ አስመልክቶ ለአቶ መለስ በተደጋጋሚ ግልጽ ደብዳቤን በመላክ ጥሪ ብናደርግም ለጥሪያችን መልስ ካለመስጠት አልፈው የሕዝብን መንገድ በመናቅ የራሳቸውን መንገድ ሊከተሉ ቆይተዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያመጣውን እጅግ አስከፊ ውጤት ምን እንደሆነ ሁሉም “አብዮታዊ ዴሞክራቶች” የሚረዱት ሐቅ ነው፡፡ ሆኖ ዛሬ እርስዎ ይህ ከፈጣሪ የተሰጠዎትን ኃላፊነት በመጠቀም ልዩነት መፍጠር ይችላሉ፡፡
አገር በሰውነት ክፍል ይመሰላል፤ ከሰውነት ክፍል አንዱ ሲጎዳ ሁሉም ይታመማል፤ ሁሉም ይጎዳል፡፡ ይህ በሰውነት ክፍል የመሰልነው የሁላችንም መኖርያና መመኪያ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ በዚህች አገራችን ውስጥ የታመሙ የሰውነት ክፍሎች አሉ፡፡ እነዚህን ክፍሎች በጥቅሉ “አሸባሪ፣ ለሕግ የማይገዙ፣ ባለ ሁለት ባርኔጣ ለባሾች፣ …” ከማለት በፊት ህመማቸው ምን እንደሆነና ለዚህም ህመማቸው ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ተገቢው መንገድ ነው፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ፈጣሪ ከእርስዎ ጋር ይሆናል፤ ሕዝብም ከጎንዎ ይቆማል፡፡ እምቢ በማለት ግን የታመመውን ክፍል ከማከም ይልቅ “ማስወገድ ነው፤ እርምጃ መውሰድ ነው” የሚል ግትረኛ መንገድ የሚከተሉ ከሆነ በጥቂቱ የተጎዳው የሰውነት ክፍል አመርቅዞ መላውን ሰውነት ከጥቅም ውጪ ያደርገዋል፤ እርስዎም ለብቻዎ የሚቆሙ ይሆናሉ፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የደቡብ ክልል ወይም የድርጅትዎ ተወካይ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ መሪ እንደመሆንዎ ሕዝብን ለማዳመጥ ጊዜ መስጠት ያሻል፡፡ በተለይም “ተቃዋሚ፣ አሸባሪ፣ … ” የተባሉትን በድርጅትዎ በጠላትነት የተፈረጁትን የኢትዮጵያ ክፍሎች በማዳመጥ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣትና በበርካታ ሕመም የተጎዳውን የኢትዮጵያን ሰውነት ክፍል ማከም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆን ቃለ እግዚአብሔርን በጥልቅ ከሚያውቅ እንደ እርስዎ ያለ መንፈሳዊ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅና ወደፊት በሐዋርያነት የሚጠቀስ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ምናልባት እስካሁን ካለው የድርጅትዎ አሠራር ጋር የማይስማማ ቢሆንም የአገራችንን ሕመም እስከፈወሰና ሕዝብን እስካዳነ ድረስ ሕዝባዊ አካሄድ ነው፡፡
በመሆኑም አገራችን የምትፈልገው የተሃድሶ፣ የዕርቅና የፍትሕ መፍትሔ ሥር የሰደደና ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል መሆን ያለበት ነው፡፡ ይህንን ዓይነት አካሄድ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ፈጽመውት የነጻነት፣ የዕርቅና የፍትሕ ፋና ወጊ መሆን ችለዋል፡፡ በእኛም አገር ይህንን ማካሄድ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንዲሁም የመንግሥት ዋንኛው ሥራ አስፈጻሚ እንደመሆንዎ በእስር ላይ የሚገኙት የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ የማድረግ፣ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ፊት ለፊት የመገናኘትና የመነጋገር፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት ወዘተ መብቶችን በተለያየ ሁኔታ ያገዱ ሕግጋትን የማሻሻልና የማስሻር፣ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኛ እንዳይኖር የማድረግ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ የማድረግ፣ “በልማት ስም” ከነዋሪዎች ላይ እየተነጠቁ ያሉትን የመሬት ይዞታዎችን እና ነዋሪዎችን ከቀያቸው የማፈናቀል ተግባራትን የማስቆም፣ ይህንን ዓይነቱን ተግባራት እየፈጸሙ ያሉትን የሠራዊቱና የደኅንነቱ አባላት ለፍርድ የማቅረብ፣ የሃይማኖት ጭቆናንና መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያደርገውን ጣልቃገብነት የማስቆም፣ ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈና በእውነትና በኢትዮጵያዊ የዕርቅ ባሕል ላይ የተመሠረተ ዕርቅ የመጥራት፣ በዚህም የዕርቅ ሒደት ውስጥ በድርጅትዎ ውስጥ ያሉት የሚካተቱ መሆናቸውን የማሳሰብና የማሳመን ኃላፊነት፣ ጉዳያቸው ከዕርቅ ባለፈ መልኩ በሕግ መታየት ያለበትንም በሕግ የሚዳኙ እንጂ በመንገድ ላይ ለፍርድ የሚቀርቡ አለመሆናቸውን የማሳመን፣ በተቃዋሚው ጎራም ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ በወንጀል የሚጠየቁ ሁሉ ጉዳያቸውን በሚመለከት ፍትሕ የሚበየን መሆኑን እንጂ “አሸናፊ” የሆነው ኃይል የፈለገውን እርምጃ የማይወስድባቸው መሆኑን የማሳመን፣ ወዘተ ኃላፊነት የእርስዎ ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው ይህ የድርጅትዎ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትዎና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነትዎ በቅድሚያ የእርስዎ ነው፡፡
ክቡር ጠ/ሚ/ር፤
ከዚህ በፊት እርስዎ ሲናገሩ “እመኝ የነበረው አገልጋይ ለመሆን ነበር። ወደ ድርጅት ከሄድኩም በኋላ ስራዬን በታማኝነት እሰራ ነበር። አሁንም እየሰራሁ ነው። የህዝብ አገልጋይ ነኝ። ህዝብ የምጨቁን ሰው አይደለሁም። ለህዝብ የምታዘዝ ሰው ነኝ”ብለው ነበር፡፡ አሁንም ይህንን ቃልዎን በተግባር በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ –  እርስዎንም ሆነ ድርጅትዎን በሚደግፉም ሆነ በሚቃወሙ – ፊት በተግባር የሚፈጽሙበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ እውነተኛ የሕዝብ አገልጋይ መሆንዎን የሚያስመሰክሩበት የታሪክ አጋጣሚ ይህ ጊዜ ነው፡፡ የእርስዎን ሃሳብ፣ ፖሊሲ፣ አስተዳደር፣ ድርጅት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ … የማይቀበሉ ወይም የሚቃወሙትን ሁሉ “አሸባሪ ነው፣ አስገባው፣ ከርችመው፣ እሰረው፣ አሰቃየው፣ አስወግደው፣ …” የሚሉ ሳይሆን እንደ ቃልዎ “ለሕዝብ የሚታዘዙ”ና “ማንንም የማይጨቁኑ” “የሕዝብ አገልጋይ”ና መሪ እንዲሆኑ ሕዝብ እየጠበቅዎ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በቃለምልልስ እንደተናገሩት “አንድ ጥፋትሰው ላይ ከሚደርስ ብዙ ጊዜ ራሴን ብጎዳ እመርጣለሁ” ባሉት መሠረት ራስዎን እስከመጉዳት የሚያደርስ ቅንነትንና ሐቀኝነት የተሞላበትና በድፍረትና በግልጽ ክፋትን፣ ተንኮልን፣ መከፋፈልን፣ ወገንተኛነትን፣ ሥርዓት አልበኝነትን … የሚቃወምና ከሕዝብ ጋር የሚቆም አስተዳደር የኢትዮጵያ ሕዝብ – ደጋፊዎም ተቃዋሚዎ – ይጠብቅብዎታል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ታሪክና ፈጣሪዎ ያለአንዳች ማዛባት እርምጃዎችዎን ይከታተላሉ፡፡ ይህ ሁሉ በጊዜ ሒደት ውስጥ የሚታይ ቢሆንም የጋራ ንቅናቄያችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ካለው ቀጥተኛ ግንኙነት አንጻር የሕዝብ ወገን በመሆን ለዘመናት በልጅ ልጆቻችንም ሆነ በታሪክ ድርሳናት “ደጉ መሪ” በመባል ለመወሳት የሚችሉበትን ምዕራፍ ጀምረዋል፡፡ በየትኛው መንገድ እንደሚሄዱ የድርጅትዎ ውሳኔ ሳይሆን በቅድሚያ የሚያምኑት እውነትና የኅሊናዎ ውሳኔ ነው፡፡ እርስዎ “ታላቁ መሪ” ከሚሏቸው አቶ መለስ የሚያንስ ስብዕና ስለሌለዎ እርስዎም ከ“ታላቁ መሪ” በላይ “ታላቅ” ተብለው ለመጠራት የሚያስችልዎትን ፈጣን የተሃድሶ፣ የዕርቅና የፍትሕ ታሪክ በመሥራት “አዲሲቷ ኢትዮጵያን” የመመስረቻው ጊዜ አሁን ነው፡፡
ፈጣሪ እርስዎንም እኛንም ይርዳን፡፡
ኦባንግ ሜቶ
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
ዋና ዳይሬክተር፤
አድራሻ፤
910-17th St. NW, Suite 419
Washington, DC 20006 USA
Phone: 202 725-1616

No comments:

Post a Comment