Translate

Thursday, September 13, 2012

ክብርት አና ጎሜዝ አቶ መለስ የሞቱት በሐምሌ ወር እንደሆነ ተናገሩ


መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ክብርት አና ማሪያ ጎሜዝ ይህን ያሉት፤ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክተው ማክሰኞ ለአውሮፓ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው።
አና ጎሜዝ  በዚሁ ንግግራቸው  ኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈፀመው ከፍ ያለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ -የአውሮፓ ህብረት ያሳየውን ቸልታ አጠንክረው ኮንነዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ እርዳታ ተቀባይ እና ከአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ሁለተኛ በሆነችው ኢትዮጵያ፤ ባለፈው ሐምሌ ወር መለስ ዜናዊ ከሞቱ ወዲህ በውል የታወቀ መንግስት አለመኖሩንም ጠቅሰዋል።
እንዳጋጣሚ  በመለስ ዜናዊ  ታስረው የነበሩ ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች በመጨረሻ ትናንት ተፈተዋል ያሉት አና ማሪያ ጎሜዝ፤ሆኖም የ አውሮፓ ህብረት እነሱን ለማስለቀቅም ሆነ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት ምንም ያደረገው ጥረት እንደሌለ ተናግረዋል።

ከነዚህ የፖለቲካ እስረኞች መካከልም አንዱ ፤ የፔን 2012  የመፃፍና ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ሽልማት አሸናፊ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንደሆነ አና ጎሜዝ አውስተዋል።
በ ኢትዮጵያ እየተፈፀመ ላለው የዚህ ዓይነቱ አፈናና ጭቆና የአውሮፓ ህብረት ለምን ዝምታን መረጠ?ሲሉም በአጽንኦት ጠይቀዋል፦ በ 1997 የ ኢትዮጵያ ምርጫ የአውሮፓ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ  የነበሩት ፖርቱጋላዊቷ ክብርት አና ማሪያ ጎሜዝ።
በቀጣይስ ህብረቱ በኢትዮጵያ ገዥውን ፓርቲና  ሁሉንም ተቃዋሚዎች ያሳተፈ የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ማመቻቸትን ጨምሮ በአገሪቱ እመቃ እንዲያበቃና ሀቀኛ ዲሞክራሲ  እንዲፈጠር፤ ምን ለማድረግ አስቧል? ሲሉም አና ጎሜዝ ማሣሰቢያ አዘል ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል።
አና ጎሜዝ የሰነዘሩት ጥያቄ በመድረክ መሪዋ በኩል  የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባልና በህብረቱ  የጋራ ፓርላመንታዊ ጉባኤ ተባባሪ ፕሬዚዳንት ወደ ሆኑት ወደ ሉዊስ ሚሼል የተመራ ቢሆንም፤ ሉዊስ ሚሼል መልስ ሳይሰጡበት ለአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ለካተሪና አሽተን መርተውታል።
ሉዊስ ሚሼል በቅርቡ  አዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀብር ሥነ ስርዓት ላይ  ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ አቶ መለስን በከፍተኛ ደረጃ ማድነቃቸውና ማወደሳቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል  አና ጎሜዝ በኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ  መብት ዙሪያ ህብረቱን በነቀፉበት በዚህ ንግግራቸው መካከል፤ አቶ መለስ ዜናዊ በሐምሌ ወር እንደሞቱ መጠቆማቸው፤ በተለየ መልኩ  የኢህአዴግ አባላትንና ሌሎች የስርዓቱ ደጋፊዎችን  ስለመንግስታቸው ማንነት  ጥያቄ  እንዲያነሱ የሚያስገድድ ነው ሲሉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ተናግረዋል።
እኚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መድረክ አመራር አባል፤ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ፦”መለስ ነገ ከነገ ወዲያ ይመጣል” እያሉ  ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩት፤  በእርግጥ አና ጎሜዝ እንዳሉት አቶ መለስ ሐምሌ ወር በሞቱበት ሁኔታ ከሆነ፤  ያጭበረበሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ሊጠይቃቸው ይገባል ብለዋል።
ኢሳት በዓለማቀፍ የግጭት ተንታኝ ቡድን ውስጥ ያሉ ምንጮቹን በመጥቀስ አቶ መለስ በሐምሌ ወር እንደሞቱ መዘገቡ ይታወሳል።
ኢሳት ይህን ከዘገበ ከሳምንታት በሁዋላ  በነሐሴ ወር መግቢያ አውስትራሊያ ከሚገኘው ኤስ ቢ ኤስ ራዲዮ ጋር በስልክ ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖን ፦”አቶ መለስ ለ አዲስ ዘመን በጤና ተገኝተው ለ ኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ያስተላልፋሉ ብለው ያስባሉ?” በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ እንዲያውም ከ አዲስ ዘመን በፊት ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ መናገራቸው አይዘነጋም።
ቢሯቸው አቶ መለስ ህክምና ሲከታተሉበት በነበረው በብራሰልስ የሆነው የአውሮፓ ህብረት አባሏ ወይዘሮ አና ጎሜዝ፤ አቶ መለስ የሞቱት በጁላይ እንደሆነ በአደባባይ  ያደረጉት ንግግር ፤ስብሰባውን ሲመሩ በነበሩት የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናትም ሆነ በሌሎች ተሳታፊዎች አልተስተባበለም።
<የኢህአዴግ ባለስልጣናት አቶ መለስ በህይወት አለ እያሉ ያታለሉት ብዙሀኑን የ ኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፤ የራሳቸውን የቅርብ ሰዎችና የመከላከያ ሠራዊት አዛዦችን  ጭምር ነው> ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ፤ ይህን ገለልተኛ ምስክርነት የሰሙ የህሊና ሰዎች ሁሉ ፦”ለምን ዋሻችሁን?እስከ መቼ ነው በውሸት የምትመሩን ?”የሚል ደፋር ጥያቄ ሊያነሱ ይገባል ብለዋል።
አና ጎሜዝ የሰጡት ምስክርነት  ስህተት ይሆናል ብዬ አልጠረጥርም ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩ፤ ከዚህ አኳያ ፤ አስከሬኑ አዲስ አበባ የገባ ዕለት እነ ወይዘሮ አዜብ እንደ ትኩስ ሞት እንዲያ ያለቀሱት፤ ለነሱም ሳይነገራቸው ቀርቶ ይሆንን? ወይስ ሀዘናቸውን አፍነው እንዲቆዩ ከተደረጉ በሁዋላ ማልቀስ ሲፈቀድላቸው የወጣ የታመቀ ስሜት ይሆን?”የሚል የግርምት ጥያቄ ተፈጥሮብኛል ብለዋል።
ፓርላማው ከተበተነ በሁዋላ የ 2005 በጀትን እንዲያጸድቅ  የተጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ ያስታወሱ ወገኖች ግን፤ በዕለቱ ወይዘሮ አዜብ በስብሰባው የተገኙት በአንገታቸው ላይ ጥቁር የሀዘን ጨርቅ አድርገው እንደነበር ያወሳሉ።
ኢሳት ሬዲዮ በበኩሉ በዚያ ሰሞን ሊካሄድ የነበረ የወይዘሮ አዜብ እህት ሰርግ -ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን ከምንጮቹ ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ መዘገቡ አይዘነጋም።
ጋዜጠኛ ሢሳይ አጌና ፦”በ እርግጥ አቶ መለስ በህይወት አሉን?”በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው የህወሀቱ መስራች አቶ ስብሀት ነጋም፤ ከት ከት ብለው መሳቃቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

No comments:

Post a Comment