መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አቶ ስዬ ይህን ያሉት መድረክ በሲያትል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
<ነፍሱን ይማረውና ከ እንግዲህ አቶ መለስ አርፏል፤አልፏል> ያሉት አቶ ስዬ፤ ከ እንግዲህ የሚቋቋመው መንግስት የ አቶ ሀይለማርያም ወይም ከሌሎቹ የ አንዱ ይሆናል እንጂ የመለስ አይሆንም>ብለዋል።
<ተወደደም ተጠላም የምናውቀው ኢህአዴግ ከ እንግዲህ አይኖርም>ሲሉም አቶ ስዬ አክለዋል።
<የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀያ ዓመታት ያገኘውን ተነፃፃሪ ሰላምና ይብዛም ይነስም በዚህ ወቅት ያፈራቸውን ቁሳዊ እሴቶች ሊያጣ አይፈልግም> ያሉት አቶ ስዬ፤በማያሻማ መልኩ ሁኔታዎች ለሰላማዊ ሽግግር እንዲመቻቹለት ይፈልጋል>ብለዋል።
ኢህአዴግ ለዚህ ሁኔታ ከተለመደው የ እኛ እናውቅልሀለን ፖለቲካ የተለየ መንገድ ማሰብ አለበት ያሉት የመድረክ አመራሩ፤የ ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም እውነታውን በጥሞና መመርመር ይገባቸዋል ብለዋል።
“አለ የሚሉትን የ አቶ መለስን <ሌጋሲ>፤መፈክር እና ፎቶ በማንጠልጠል አለያም ዜማ በማዜም ሊያስጠብቁት አይቻላቸውም”ያሉት አቶ ስዬ፤ሁሉንም እንዳለ እናስቀጥላለን ብሎ መሞከር ሁሉንም ማጣት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ መክረዋል።
አክለውም፦”ነገሩ የ እልህና የቁጭት ሳይሆን የብልህነትና የ አስተዋይነት ጉዳይ ነው፤ለውጥ መኖሩን መገንዘብ እና ይህን የተገነዘበ ሁሉን የሚያሳትፍ መንገድ መቀየስ አስፈላጊ ነው”ብለዋል።
<አሁን በኢትዮጵያ ብቅ ያለው የለውጥ ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የተፈጠረ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንችላለን> ያሉት የመድረኩ አመራር፤ለውጡን በዚህ ሁኔታ እንቀበለው ካልን መንገዱ የይቅርታ፣የመመካከር፣የፍቅርና የ አንድነት መንገድ ብቻ ነው>ብለዋል።
በስብሰባው የተገኙት ሌለኛው የመድረክ አመራር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የመድረክን ዓለማና እያከናወናቸው ያላቸውን ተግባራት በስፋት አብራርተዋል።
No comments:
Post a Comment