Translate

Friday, October 19, 2012

‹‹ለእኔ አንዱዓለምና (አንዱዓለም አራጌ የተባሉ የፓርቲያቸው አባል) ጓደኞቹ አሸባሪ ሳይሆኑ ለዚች አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደክሙ የነፃነት አርበኞች ናቸው፤›› ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ (መድረክ) ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ‹‹እነዚህ ለእኛ አርበኞች ሳይሆኑ አተራማሾች ናቸው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም


የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የዘንድሮ ዓመት የሥራ ዘመንን ለመጀመር መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ባደረጉት የጋራ ስብሰባ ላይ የአገሪቱ

ሲሆን፣ በዚሁ ንግግራቸው መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በበጀት ዓመቱ ሊያከውናቸው ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችም አብራርተው ነበር፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራር ደንብ መሠረት የምክር ቤቱ አባላት ፕሬዚዳንቱ በቀረቧቸው ሐሳቦችና ቅድሚያ ትኩረት ሊያገኙ ይገባቸዋል ባሏቸው ነጥቦች ላይ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ አስተያየት እንዲሰጡ ይፈቅዳል፡፡ በሥነ ሥርዓት ደንቡ መሠረት የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የተባሉት ነጥቦች ላይ ለሚቀርብ ተቃውሞ፣ እንዲሁም ትኩረት ሊያገኙና ሊካተቱ ይገባቸዋል በሚል ለሚቀርቡ ሐሳቦች የአገሪቱ ጠቅላይ ማኒስትር አስተያየትን ካዳመጠ በኋላ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ተሻሽሎ አልያም ባለበት ሁኔታ እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡
በዚሁ መሠረት በፕሬዚዳንት ግርማ ንግግር ላይ ከስድስት የምክር ቤቱ አባላት አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ አስተያየቶች የቀረቡት በኢሕአዴግ አባላት ሲሆን የማብራሪያ እንጂ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ጥያቄ የላቸውም፡፡
ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ (መድረክ) ተወካይ በሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የቀረቡት ሐሳቦች ግን ሁለት ዓይነት ይዘት አላቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ያነሷቸው ነጥቦች በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ ሊካተቱ አይገባም ያሏቸውን ሲሆን፣ በመቀጠል ደግሞ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ ሊካተቱና መንግሥትም ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ያሏቸውን ነበር፡፡
ፖለቲካዊ ይዘት ካላቸውና በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ ሊካተቱ ይገባል በሚል የጠቀሷቸው ነጥቦች የአንድ ፓርቲ የበላይነት በአገሪቱ መስፈን፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝባዊ ምርጫ እንዲሳተፉ በሕግ የተፈቀዱ ሥርዓቶች መከበር ይገባቸዋል የሚል ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡

politics_330_228አቶ ግርማ መንግሥት በቅርቡ ለሕግ ታራሚዎች ያደረገውን ምሕረት በተመለከተም ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ደረቅ ወንጀል የሠሩትን ታራሚዎች በመፍታት ሳይሆን የአሸባሪነት ታፔላ ተለጥፎ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ ቢቀመጥ ጥሩ ነው፤›› የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
ይህ የአቶ ግርማ ሐሳብ የ2005 ዓ.ም. ዘመን መለወጫን ተከትሎ በፌዴራል ደረጃና በክልል መንግሥታት ምሕረት የተደረገላቸው በርካታ ሺሕ ታራሚዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በእነዚህ ታራሚዎች መለቀቅ ላይ ተቃውሞ ባይኖራቸውም ምሕረት ሊያገኙ የገባቸዋል ብለው የሚያምኑባቸው ግለሰቦች አለመካተት ግን ተገቢ አለመሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡
ይህንኑ ሐሳብ ሲያጠናክሩም፤ ‹‹ለእኔ አንዱዓለምና (አንዱዓለም አራጌ የተባሉ የፓርቲያቸው አባል) ጓደኞቹ አሸባሪ ሳይሆኑ ለዚች አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደክሙ የነፃነት አርበኞች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
ለዚህ የአቶ ግርማ አስተሳሰብና በአፅንኦት ላነሱት ሊፈቱ ይገባል የሚል ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምላሽ መስጠት የጀመሩት በጥያቄው እንደተገረሙ በመግለጽ ነበር፡፡
‹‹በጣም የሚገርም የአርበኝነት ጥያቄ ነው›› በማለት ምላሻቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ላይ መቼም እንደማይደራደር በመግለጽ ነው፡፡
ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጐት ካላቸውና በተግባርም በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር፣ የፓርቲ አመራርነት ወይም የጋዜጠኝነት ሽፋን ይኑረውም አይኑረውም ግንኙነት እየፈጠረ አገሪቱን ለማተራመስ የሚፈልግን ኃይል ወደ ሕግ ለማቅረብ መንግሥታቸው የሚፈልገው በበቂ ጥርጣሬና ማስረጃ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
‹‹እነዚህ ለእኛ አርበኞች ሳይሆኑ አተራማሾች ናቸው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ መንግሥት የተጠቀሱትን ግለሰቦች ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ወንጀለኛ እንዳላለ ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤት ቀርበው ማስረጃ በማቅረብ ራሳቸውን ነፃ ማድረግ ያቃታቸውና የተፈረደባቸው ግለሰቦች አርበኞች ከሆኑ ወይም አርበኛ የማድረግ ፍላጐት መኖሩ የሚያመላክተውና በመንግሥት ላይ የሚጭረው ጥያቄ፣ በሕግ የበላይነት ላይ ጥርጣሬ ወይም አለመተማመን አሁንም መኖሩን ነው ሲሉ አመላክተዋል፡፡
ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች ጋር ኢሕአዴግ የሚደራደረው የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውም ይህ ብቻ እንደሆነ ስለሚያምን መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በተሳሳተ ጐዳና ላይ ያለ ቆም ብሎ ማሰብና መታረም አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡
አንዳንድ ተቃዋሚዎች በውጭ ኃይል ላይ የተማመነ ተፅዕኖ በማድረስ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት እነዚህን ሰዎች እንዲፈታ ጥረት እያደረጉ መሆኑን እንደሚያውቁ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወዳጅ መንግሥታት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ መኖሩን ጠቁመው የመንግሥታቸው መልስ ግን ተመሳሳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህ እኛ የአገራችንን ሕዝብ ደኅንነት ለማስከበር ኃላፊነት ወስደን የምንሠራው ሥራ ነው፤›› በማለት ጠንከር ያለ አቋማቸውን አሳይተዋል፡፡
አቶ ግርማ ካነሷቸው ነጥቦች ሌላኛውና ከፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ መውጣት አለበት ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የሚመለከቱ ሐረጐችን ነው፡፡
‹‹ፕሬዚዳንቱ በየዘርፉ ባቀረቡት ሪፖርት መግቢያ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የሚመለከቱ ሐረጐች መንግሥት (ገዥውን ፓርቲ) በቀጣይ በሚደረግ የአፈጻጸም ግምገማ በሚፈጠር ጉድለት፣ ይህ ዕቅድና ሐሳብ የእኛ ሳይሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር በማለት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ያስመስላል፤›› በማለት አቶ መለስን የሚጠቅሱ ሐረጐች እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በዚህ ጥያቄ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ጥያቄው ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሁም ከሚመሩት ፓርቲና መንግሥት እምነት ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ነው፡፡
‹‹ዛሬም፣ ነገም፣ ለዘመናትም፣ እስከወዲያኛውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በዚህች አገር ላይ ያሳረፉት አሻራ እየታወሰ፣ እየተዘከረ እንደሚኖር ከዚህም በላይ ማድረግ ቢቻል እንደሚደረግ፤›› በመግለጽ ለአቶ መለስ ያላቸውን ክብር አስገንዝበዋል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ከመጠቀሳቸው አግባብነት ጋር ተያይዞ ለቀረበው ‹‹የተጠያቂነት ሽሽት›› ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጥያቄውን ለመመለስ በተወካዮች ምክር ቤት ከመገኘታቸው ጋር አያይዘው ነው፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትራችን የመንግሥትን ተጠያቂነት አስፍነው ነው ያለፉት፡፡ ዛሬ እኛ አዲስ የመጣነው አመራሮችም ብንሆን ተጠያቂ ነን፡፡ የመጀመሪያው ጠያቂ ይህ ምክር ቤት ነው፡፡ ዛሬ ይህንን ንግግር ከፊታችሁ ሆኜ የምናገረው ይህ የተጠያቂነት መርህ ስለተተከለ ነው፤›› በማለት፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሥራ አስፈጻሚውን የተለያዩ እንቅስቀሴዎች የሚከታተሉና የሚገመግሙ ከ13 በላይ ቋሚ ኮሚቴዎች ሲኖሩ የመንግሥትን ሀብትና በጀት አጠቃቀም የሚቆጣጠረው ቋሚ ኮሚቴ አንዱ ነው፡፡
በምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚል መርህ ይህ ቋሚ ኮሚቴን በምክር ቤቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም ከገዥው ፓርቲ ውጪ ያሉ አባላት እንዲመሩት ቅድሚያ እንዲሰጥ ይደነግጋል፡፡
በምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አቶ ግርማ ሲሆኑ፣ ይህንን ቋሚ ኮሚቴ የሚመሩትም ራሳቸው አቶ ግርማ መሆኑን የተገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህንኑ እውነት ለአቶ ግርማ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ተጠቅመውበታል፡፡
‹‹ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነው አቶ ግርማ የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴን ጨምሮ ተጠያቂ ያደርገናል፤›› በማለት አቶ ግርማ በተጠያቂነት ላይ ሥጋት እንዳይኖራቸው ጠይቀዋል፡፡
መንግሥት መሣሪያ አንስተው ከሚፋለሙት ተቃዋሚዎችና ከጐረቤት አገር ኤርትራ ጋር ጭምር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ማድረግ እንደሚፈልግ፣ ከዚያም አልፎ የተናጠል በጐ ዕርምጃዎችን ለምሳሌ ምርከኞችን መልቀቅ እያደረገ ባለበት ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ አገር ውሰጥ ከሚንቀሳቀስ ሕጋዊ ፓርቲ ጋር ውይይት ለማድረግ አለመፈለግ ተገቢ ስለማይሆን፣ አሁንም የዚህ ዓመት የቅድሚያ ተግባር መሆን አለበት ሲሉ አቶ ግርማ ጠይቀዋል፡፡ በተለይ እርሳቸው ከሚወክሉት ፓርቲ (መድረክ) ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ውይይት ለማድረግ ገዥው ፓርቲ ዝግጁነቱን ቢያሳይ ተገቢ ነው ብለው፣ ይህ ሐሳብም በፕሬዚዳንቱ ንግግር ውስጥ መካተት አለበት ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ኃይለ ማርያም ፓርቲያቸው እንዲሁም የምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡን የፈረሙ ሌሎች ፓርቲዎችም ጭምር በዚህ የመድረክ ጥያቄ ላይ ቀደም ሲል ውሳኔያቸውን እንዳሳለፉ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው የምርጫ ዝግጅት ወቅት በዲሞክራሲ ከኢትዮጵያ የላቁ ናቸው ተብለው ከሚታወቁ አገሮች የተወሰደን የሥነ ምግባር ኮድ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና ለመተግበር በሚቻለበት ሁኔታ ላይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውይይት እንደተደረገ፣ በወቅቱ መድረክ ተሳታፊ የነበረ ቢሆንም ገና ከጅምሩ ኢዴፓ ከተባለ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር አልወያይም ብሎ ረግጦ መውጣቱን አስታውሰዋል፡፡
በውይይት የማያምን ፓርቲ የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት ሊኖረው የሚችለውን ሚና ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚከተው የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የመድረክ ፓርቲ ጥያቄ በወቅቱ በቅድመ ሁኔታ የተዘጋ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የሥነ ምግባር ኮዱን በመቀበል በዚሁ መስመር ለመንቀሳቀስ ፓርቲው ፊርማውን ሲያኖር ብቻ ውይይትና ድርድር ሊኖር ይችላል ከዚያ ባለፈ ግን ያበቃለት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ግርማ ያነሷቸው አስተያየቶች በምክር ቤቱ ተቀባይነትን ሳያገኙ ውድቅ ሆነዋል፡፡

No comments:

Post a Comment