በቁጥር 1 መቀመጫ የአቶ ሃይለማርያም የመጀመሪያው ውሎ
“ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል” እንዲሉ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፓርላማ ተራ ቁጥር አንድ መቀመጫ ላይ ተሰይመው ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ አዲስ ክስተት ተስተውሏል። የቅናት፣ የተንኮል፣ የንቀት፣ ያለመታዘዝ፣ ተቃውሞን የማሳየት… ይሁን የሌላ እስካሁን በውል አልታወቀም። በመጀመሪያ ንግግራቸው መዛለፋቸውን ግን ብዙዎች ከእርሳቸው የጠበቁት ባለመሆኑ ተገርመውባቸዋል። በሌላ በኩል ግን ገና ከጅምሩ አክርረው የመጡት “ተለሳላሽ” ናቸው የሚባለውን ለመስበር እንደሆነም አስተያየት ተሰጥቷል።
የህወሃት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደኢህዴን ሰዎችና ወ/ሮ አዜብ አቶ መለስ ንግግር ካላቸው ማታ እንኳን አያመሹም። ሲያንቀላፉ እንዳይታዩ በጊዜ ተኝተው ጠዋት ፓርላማ ናቸው። ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዳቸውም አይቀሩም። በሽተኛ እንኳን ቢሆኑ እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ወሳኝ ተጫዋች ደረቅ መርፌ ተወግተው መለስን ከማጀብ ወደኋላ አይሉም። ድርድራቸውን አሳምረው ይኮለኮላሉ። አቶ መለስን በሳቅና በማድነቅ አጅበው ይውላሉ።
በሳምንቱ መጀመሪያ አካባቢ አቶ ሃይለማርያም የተናገሩበት ፓርላማ ምክንያቱ ባይታወቅም እነዛ ሁሉ የመለስ አጃቢዎች አልነበሩም። አፈ ጉባኤው ያዛጉ ነበር። የደቡብ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ አማኑኤል አብርሃም ማስቲካ እያላመጡ ሲያሽሟጥጡ ይታዩ ነበር። አቶ ሃይለማርያምን “እሳቸው የሚሾሟቸው ካቢኔዎች” ወደፊት ያጅቧቸው ካልሆነ በቀር ለጊዜው ለጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እምነት የመስጠትና እሳቸውን በማጀብ ክብር መስጠቱ ላይ ችግር እንዳለ የሚያሳብቅ ድባብ እንዳለ በብዙዎች ዘንድ ስምምነት አለ።ከሁሉም በላይ “ብቸኛ የግል ተወዳዳሪ” የሚባሉትና ስብሰባ የሚወዱት የቦንጋው ሰው ዶ/ር አሸብር አለመገኘታቸው አስገራሚ ሆኗል። ባላንጣቸውን ብርሃኑ አዴሎን “በዝረራ” አሸንፈው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር አሸብር ያልተገኙበትን ምክንያት ለማጣራት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።
አቶ ሬድዋን ብቻቸውን ከጎናቸው ተቀምጠው ዓይናቸውን ሲያገለባብጡ ኢቲቪ በተደጋጋሚ ማሳየቱ “እሳቸው በቂ ናቸው” እንደማለት ስለመሆኑ ማስረጃ ባይቀርብም የአቶ ሃይለማርያም ውሎ “ብቸኛነት ተኮር” ነበር – በራሱ በኢህአዴግ ቋንቋ!!
አቶ ሃይለማሪያም ፓርላማ ቀርበው ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ በያቅጣጫው በመዛወር በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ ወሬ ቃርሜያለሁ። ተናግሬ አናግሬያለሁ። ከሁሉም ያስፈገገኝ “አደገኛ ኮራጅ ናቸው” መባላቸው ነው። አዎ! ልብ ብሎ ለተመለከታቸው አቶ ሃይለማርያም ተረት ሞክረዋል ተራ ሆነ እንጂ፣ የእጃቸው እንቅስቃሴም የራሳቸው አይመስልም። ወደ ጎን እይታቸውና ኢትዮጵያን ከማይመጥኑዋት ጋር በማወዳደር … ብቻ ምን አደከማችሁ አቶ መለስን ለመሆን ሲታገሉና ሲለማመዱ የከረሙ ይመስላሉ። ያልኮረጁት ነገር ቢኖር በንግግር መካከል ውሃ ፉት የማለትን አስፈላጊነት ነው። ላንቃቸው እየደረቀ አላናግር ሲላቸው ተስተውሏልና በቀጣዩ ያሻሽሉታል ተብሎ ይገመታል። አቶ መለስ በሃረር ቋንቋ ውሃውን ፉት ሲሉት “ሉሉ ቀቻ” ያስመስሉታል። ይችሉበታል ለማለት ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና።
አቶ መለስ በበረሃ አስራ ሰባት ዓመታትን፣ የአርነት ድርጅትን በመወከል አርነታቸውን የከለከለችውን አገር በመምራት ሃያ አንድ ዓመት፣ በዚችው አገር ስም በዓለምና በአህጉር አቀፍ መድረኮች ብቻቸውን እያወሩ ሲናገሩ ኖረው ኖረው ስለሞቱ አቶ ሃይለማርያም እንደሳቸው መናገር አይጠበቅባቸውም የሚሉ ብዙ ናቸው።
መለስን በንግግር ከማድነቅ አልፎ የሚያመልኳቸው ፓርላማው ማዕረጉ መገፈፉን ይናገራሉ። መከራከሪያቸው ከልክ ያለፈ፣ ሙግታቸው ለመጻፍ የማያመች የንጽጽር ዘለፋ በመሆኑ አልፌዋለሁ። በመለስ ንግግር የሚመሰጡ በፈረንጆቹ ቋንቋ “we miss him – መለስን ከሰርነው” ሲሉ ይሰማሉ። መለስ ከሞቱ ማንን አደምጣለሁ ብሎ ራሱን ከፎቅ ከስክሶ ሞተ ስለተባለው ወጣት ያነሱም አጋጥመውኛል። ተከትለውት የሙታን መንደር ለመውረድ ስለመወሰናቸው ግን በቀልድም አልተነፈሱም።
“ለኔ ተናጋሪ ማለት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ናቸው” ሲል በቡድን ክርክር የሚጨቃጨቀውን ሰማሁት። አንድ ተናጋሪ ጥሩ ተናጋሪ ለመባል የሚያስችለው ንግግሩ አጭር፣ ዋናውን ነጥብ የማይለቅ፣ ያልተንዛዛ፣ ቀላል በሆነ መንገድ መግለጽ ወይም ማስረዳት የሚችል… ሲል ዘረዘረ፤ መለስ ግን ይህንን አያውቁትም። መለስ ያወራሉ። ወሬያቸው ግን ሲጨመቅ ጭማቂው ብርጭቆው ውስጥ አልታይ ይላል። እንደ መሪ ነገ ምን እባላለሁ አይሉም። የሚናገሩት ለዕለቱ ነው። ለቀኑ ነው። የሚፈሩት ፓርላማ ስለሌለ እንዳሻቸው ቢሉ ከልካይ የላቸውም። … አወዛጋቢው መለስ የተናገሩት ንግግር ቢሰበሰብና ገበያ ላይ ቢውል ስል ተመኘሁ። መለስን እንዲያመልኩ የተወሰነባቸው ህጻናት ምናልባትም በራሳቸው ህሊና ነጻ ይወጡ ይሆናል። “ቅስቀሳውን ራሳቸው መለስ አንዴ ቀና ብለው ቢያዩት ስለ ማን ነው የምታወሩት?” በማለት እንደሚገረሙ አንድ የኢቲቪ ባልደረባዬ እያፈረ አጫውቶኛል።
አቶ ሃይለማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ ለረጅም ሰዓት አደባባይ ወጥተው በወሳኝ የአገሪቱ ጉዳዮች ግምት ውስጥ የሚጥል፣ ለትችትና ለአስተያየት የሚያጋልጥ ንግግር አድርገዋል። ዘርፎችን እየለያዩ የፓርቲያቸው ሰዎች ተዘጋጅቶ የተሰጣቸውን ጥያቄ በንባብ ሲያቀርቡላቸው እሳቸውም በመለሳዊ እንቅስቃሴ የተዘጋጁበትን መልስ ሰጥተዋል። አገሪቱን የሚመራውን ቡድን ወክለው ሲናገሩ መጠነኛ ላብ ቢጤ የታየባቸው ለመሳደብ ሲሞክሩ ነው።ብቸኛው የህብረት ተወካይ አቶ ግርማ “መለስን ደጋግሞ መጥራት…” ሲሉ ላቀረቡለት “የገደል ማሚቱ አትሁኑ” ጥያቄ ፍጹም ታማኝነታቸውን ለማሳየት፤ ከመቀመጫቸው ወደ ግራ በመመልከት የሰጡት አስተያየት አቶ ሃይለማርያም እምነታቸውን ስለመጠበቃቸው የሚያጠራጥር ሆኗል። በክርስቲያናዊ ቋንቋ “… ዛሬም፣ ነገም እስከ ዘላለም …” አመልከዋለሁ የሚሉትን አምላክ በአቶ መለስ ስም በመተካት መለስን ሰማያዊ ክብር አጎናጽፈዋቸዋል። ይህንን አለማድረግ ከህዝብ ጋር የሚያጋጭ እንደሆነም አስረድተዋል – ማን ያውቃል በቅርቡ በዚሁ ጉዳይ በሽብርተኝነት የሚከሰሱ … አይ ይቅር አልጨርሰውም።
በየዘርፉ ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት ሲቸገሩ ያልታዩት አቶ ሃይለማርያም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለይም የመድረክ አመራሮችን ዘልፈዋል። ከቀረበላቸው ጥያቄ ጋር ባልተገናኘ መልኩ ዘለፋ የሰነዘሩት አቶ ሃይለማርያም፣ “መተካካት የማያውቁ ሽማግሌዎች ሲሉ” የተሳደቡት ስም ባይጠሩም የመድረክን አመራሮች ነው። ራሳቸውን ትክክለኛ የመተካካት ውጤት፣ ስልጣናቸውን በአግባቡ እንደሚጠቀሙበት ማስመሰላቸው ላይ ከመሳሳታቸው በስተቀር በተለያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ አዳዲስ አመራሮች አለመታየታቸው ቀደም ብሎም የሚወሳ ችግር ነው። በነገራችን ላይ አቶ ሃይለማርያም አውቀውም ይሁን፣ ከልምድ ማነስ ኢዴፓን በማሞገስ ፓርቲውና የቀድሞው የፓርቲው መሪ የሚታሙበትን የኢህአዴግ ወዳጅነት አደባባይ እንደ ብቅል አውጥተው አስጥተውታል።
መድረክን በመለየት ሲያወግዙ የነበሩት አቶ ሃይለማርያም “የመድረክ ሰዎች አንዴ የስነምግባር ኮዱን አንቀበልም ብለው ድርድር ረግጠው ስለወጡ ዳግም ለመመለስ ፈርተው ነው። ችግራቸው ይገባናል። ሰው ምን ይለናል ብለው ነው” በማለት የተናገሩት ንግግር የቅንጅትን “የይሉንታ ፖለቲካና ክስረት” ያስታወሰ ነበር። አቶ ግርማ በጨዋ መልክ ያቀረቡት ከኤርትራና መሳሪያ ካነሱ ሃይሎች ጋር ለመደራደር የሚወተውተው ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊና ሰላማዊ ከሆነው መድረክ ጋር መደራደር የላስቻለውን አቋሙን በመቀየር ወደ ድርድር እንዲመጡ ለማሳሰብ ሆኖ ሳለ አቶ ሃይለማርያም በማያገባቸው ሰው ቤት ውስጥ ገብተው መዘባረቃቸው ንግግራቸው ክፉ ጎን ተደርጎ ተወስዷል።
ስለፕሬስ አፈናና ስለ እስረኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “ዲሞክራሲ ባህል ነው። የሚያድግና የሚሻሻል ሂደት ነው” ማለታቸው ለዚህ ሪፖርት አቅራቢ አይዋጥለትም። ለምሳሌ አሁን በሚሰራበት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ላይ ነጻ ሆኖ መጻፍ አይችልም። ሪፖርት የሚያደርገው በድብቅ ነው። ከተያዘ ይፈረድበታል። አሸባሪ ይባልና የዋስ መብት ይከለከላል። ያለውና ወደፊት ሊኖረው ይችላል የሚባለው ንብረቱ በሙሉ ይዘረፋል፡፡ በአገር ቤት የሚታተሙ ጋዜጦች ቆመዋል። ስርዓቱን የሚደግፉና በስርዓቱ የሚደጎሙ ካልሆኑ በስተቀር ገበያ ላይ ያሉ ፍጹም ገለልተኛ ሚዲያዎች እንደሌሉ ዝርዝር በማቅረብ ይከራከራል። አቶ ግርማ እንዳሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ልሳናቸውን ማሳተም አቅቷቸዋል። አቶ ሃይለማርያም እንደ ግንድ ዓይናቸው ውስጥ የተገተረ እውነት በመተው “ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ተከብሯል” ማለታቸው ወደፊትም የመዋሸት ዓላማ እንዳላቸው የሚያመላክት ይሆናል። እንደ እሳቸው አባባል ዴሞክራሲ በሂደት የሚዳብር መሆኑ ቢያስማማም፣ በተግባር በአገራችን እየሆነ ያለው የዴሞክራሲ ፍሬዎችን የሚያቀጭጭና የሚያጠፋ ነው። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የነበረውን ጅማሮ እየገደለ አውራ ፓርቲ መሆኑንን ሲያውጅ፣ የተለያዩ ህጎችን በማውጣት ዜጎች እንዲሸማቀቁ በማድረግ ነው፤ እናም አቶ ሃይለማርያም ይህንን አጥተውት ነው ወይስ ተሸውደው?
ስለ ኤርትራ ሲናገሩ፣ ኤርትራን አቶ መለስ እንዳሉት “አተራማሽ” ሲሉ ፈርጀዋታል።ለትግል ኤርትራ የገቡትን የተቃዋሚ አካላት ልጆቻቸው እዛው ተወልደው ማደጋቸውን ሲገልጹ ለአፍታም በቀበሮ ጉድጓድ ስለሚኖሩት ምስኪን ወታደሮች አላነሱም። ከጠላት ጋር ተፋጦ ምሽግ ውስጥ የተቀመጠው ሰራዊት ለምን ያህል ዓመታት ቤተሰቡን፣ ቀዬውን፣የሰላምና የነጻነት ኑሮ እየናፈቀው ይኖራል? የአገሪቱ ኢኮኖሚስ እስከመቼ ይህንን የድብብቆሽ ድራማ ተሸክሞ ይቆያል? “ኢትዮጵያዊው የትግራይ” ህዝብስ እስከመቼ በስጋት የቆቅ ኑሮ ይኖራል? የሚሉትን ጉዳዮች የሚያብራራና ቁርጥ ያለ መልስ የሚሰጥ አልተገኘም። አቶ ሃይለማርያም ብቻ ሳይሆኑ ኢህአዴግ፣ በተለይም ህወሃት በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ አቋሙን ግልጽ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚሉ ወገኖች የመብዛታቸውን ያህል፣ ሰራዊቱም ሆነ አመራሩ ይህንን ጥያቄ ባለማንሳታቸው ይወቀሳሉ። ኢትዮጵያ በኤርትራ ጉዳይ የጠራ መንገድ አለመከተሏ ሃብቷንና ንብረቷን፣ ብሎም ውድ ልጆቿን አላስፈላጊ ለሆነ ግንኙነት መገበሯ የሚያንገበግባቸው ወገኖች ኢህአዴግና መለስ በኤርትራ ላይ የሚከተሉትን የተንሸዋረረ አቋም እንዲያስተካክሉ በተደጋጋሚ የሚጠይቁት ውድ ጉዳይ ነው።
ስለሃይማኖት አጠንክረው የተናገሩት አቶ ሃይለማርያም፣ ሁሉም ሃይማኖቶች “በአምልኮ” ስም ፖለቲካ እንደሚያራምዱ ወቅሰዋል። የሃይማኖት ነጻነት እንዳለ አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል። እምነትን ወደ ስራና ወደ ፖለቲካው ማጠጋጋት ይቅርታ እንደማያሰጥ አሳስበዋል። ሙስሊም ኢትዮጵያዊ በዲሞክራሲው ተጠቃሚ ለመሆን በመቻላቸውና መሪዎቻቸውን ለመምረጥ በመታደላቸው “እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉ ፈገግ እንኳ አላሉም። በዚሁ ምስጋና ባቀረቡበት ስሜታቸው “ቀዩን መስመር” የሚለውን ቃል ቢዘነጉትም በሃይማኖት ከለላ ህገ መንግስቱን ለመናድ ሙከራ ቢደረግ በእሳት የመቃጠል፣ እሳትን ሆን ብሎ የመጨበጥ ያህል እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
“ኢህአዴግም አለ። ኢህአዴግም የሚመራው መንግስት አለ። የሚነገዳገድ ነገር የለም” በማለት በመመጻደቅ ተናገሩት የውጪ ግንኙነትን አስመልክቶ ነበር። “ወዳጆቻችን ያውቁናል። ተቃዋሚዎች ናቸው የማያውቁን … ” ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ በአቋራጭ ስልጣን መከጀል ህዝብን መናቅ እንደሆነ ተናግረዋል። በህዝብ ውክልና፣ በነጻ ምርጫ ኢህአዴግም ሆነ እሳቸው ስልጣን ላይ መቀመጣቸውን አመልክተዋል። አቶ ሃይለማርያም ህዝብ የሰጣቸውን ክቡር አደራ ፓርቲያቸውም ሆነ እሳቸው በብቃት እንደሚወጡ ያስታወቁት በሁሉም መድረክ የኢትዮጵያን ጥቅም ልክ አቶ መለስ ሲያደርጉት እንደነበረው በማስከበር ነው። አቶ መለስ ቅድሚያ በመስጠት ሲያስከብሩዋቸው የነበሩዋቸውን የአገሪቱን ጥቅሞች ወደፊት ካላብራሩ በስተቀር ምን እንደሆኑ እስካሁን አልገለጹም።
አባቶቻቸውን በመልካም አውራሽነት፣ በአልበገርም ባይነት ያስታወሱት አቶ ሃይለማርያም ድህነትን ለመቀነስ፣ ግሽበትን በመቀነስ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ሲያስታውቁ፤ የውጪ ምንዛሪ ችግር እንደሌለም አውስተዋል። የኩላሊት በሽተኞች ችግር አሳሳቢ በመሆኑ ቅድሚያ እንዲሰጠው ከመድረክ የቀረበውን እቅድ “ችግሩ ከፍተኛ ነው መታከሚያ ማዕከል ለማሰራት አቅም ግን የለም” ነው ያሉት።
ስለቴሌኮም አገልግሎት ጥራት አስቂኝ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም፣ የሞባይል ሞገዶችን በአዲስ አበባ የሚገነቡትና የተገነቡት ረዣዥም ህንጻዎች እየጋረዱዋቸው አገልግሎቱን ደካማ እንዲሁን አድርገዋል ብለዋል። “ቅድሚያ ለጥራት” የሚል መፈክር ተዘጋጅቶ “ሰማይ ጠቀሶቹ” ፎቆች አገልግሎቱን እንዳያውኩ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።ብሮድባንድን በተመለከተ ኬብል ከተቀበረበት እያወጡ የሚሰርቁ ዋና ችግር መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሃይለማርያም “የኢንተርኔት ብሮድባንድ ኬብሎችን በኤሌክትሪክ ምሶሶ ላይ ለማስኬድ ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል” ካሉ በኋላ መልሰው ስለ አሌክትሪክ ችግር ለተጠየቁት ሲመልሱ “ምሶሶ እየሰረቁ አስቸገሩን” ነው ያሉት። እዚህ ላይ አቶ ሃይለማርያም አወሳስበዋል። በተለይም ለሞባይል የጥራት ችግር ፎቆችን ተጠያቂ ማድረጋቸው ግምት ውስጥ ጥሏቸዋል። ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እንደ ችቦ በተገጠገጡባቸው አገሮች ተሰምቶ የማያውቅ ችግር ጀነራሎችና ውስን ልማታዊ ፖለቲከኞች የገነቡዋቸው ድርድሮችን መውቀሳቸው ፌዝም አስከትሎባቸዋል።
አቶ ሃይለማርያም በጋለ ምጣድ ላይ እንደተቀመጡ የሚናገሩ ወገኖች ምንም ይሁን ምን ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በሌላ በኩል መኖሪያቸውን እንኳ መረከብ ያልቻሉ ጠ/ሚኒስትር እንደሆኑ የሚገልጹ ደግሞ ከሃይለማርያም ምንም አይጠብቁም። ሃይለማርያምን ጉዳይ አስፈጻሚና ከመጋረጃው ፊት የሚቀመጡ አገልጋይ አድርገው ይስሏቸዋል።
No comments:
Post a Comment