Translate

Wednesday, October 10, 2012

ሳስበው ሳስበው ኢህአዴግ ታሟል!


Abe Tokchaw
ሰላም ወዳጄ.. እንዴት አሉልኝ? ተጠፋፋን አይደል…? ምን ላድርግ ብለው ነው የሰው ሀገር ሰው እንግዲህ ጣጣው ብዙ ነው…! ብዬ አማርሬ በአዲስ መስመር ቀደዳችን ይጀመራል።
እኔ የምለው ዘድሮ ባለ ስልጠኖቻችንን ነገር እየታዘባችሁ ነው…? ኩብለላን እኮ የስራቸው አካል አደረጉት… እኛ አቀርቅረን ኮብል ስቶናችንን ስንጠርብ እነርሱ ደግሞ ኮብልል “ስቶን” እያሉ እየነኩት ነውኮ!
ባለፈው ግዜ የአዲሳባ ምክትል ከንቲባ ከሀገር ኮበለሉ የሚል ወሬ ሰምተን ደንግጠን ሳንጨርስ አሁን ደግሞ በቅርቡ በህውሀት ውስጥ ደጎስ ያለ ስልጣን ያላቸው ሰውዬ ሽርሽር ብለው ሄደው ተመለሱ እንጂ ሲባሉ “አፍንጫቹን ላሱ” ብለውናል። ምንድነው ጉዱ!?
ሳስበው ሳስበው ኢህአዴግ ታሟል። በተለይ ጠቅላዩን በሞት ከተነጠቀ በኋላ አያያዙ ምንም ደስ አይልም። አባላቱ በተለያየ ምክንያት ከእለት እለት እየሳሱ ድርጅቱም እየከሳ መጥቷል። መጨረሻው ምን ይሆን…!?

የኦህዴዱ አቶ ጁነዲን ሳዶም አብዮታዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል። የአቶ ጁነዲን ነገር ደግሞ አንጀት የሚበላ ነው። የቅጣት አስተያየት የሰጡባቸው እነ ሚሚ ስብሐቱ እንጂ አቃቤ ህግ አልነበረም። እነ ሚሚ እንዳሉት አቶ ጁነዲን መጀመሪያ ከስልጣናቸው መወገድ አለባቸው ከዛም ባለቤታቸው ዘንድ መሄድ ይኖርባቸዋል። እንደዋዛ ባለቤታቸው ዘንድ ይሂዱ ሲባል ለጥየቃ ይመስላል ግን አይደለም እንደባለቤታቸው እንዲታሰሩ እንጂ!
አንድ ወዳጃችን የነ ሚሚን ፍርድ ቤት “የፍልውሃው ችሎት” ብሎ ሰይሞት ነበር… ፍልውሃ አጠገብ የሚገኘው የወሮ ሚሚ ራዲዮ ዛሚ እውነትም የችሎት ያህል ነው። ይታሰሩ ያለው የሚታሰርለት ይወገዱ ያለው የሚወገድለት። “ችሎቱ” አቶ ጁነዲን ሳዶ ላይም ከወራት በፊት ፈርዶባቸው ነበርና ይኸው ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።
እውነቱን ለመናገር ኢህአዴግ ታሟል። የታመመው አመንምን የተባለውን ህመም ይመስላል። “አመንምን” በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ይበልጥ የሚታወቅ ህመም ሲሆን ብዙ ግዜ የበሽታው መንስኤ ምን እንደሆነ አይታወቅም እንደው ዝም ብሎ “የቤት ጣጣ” ነው የሚባለው።
በአመንምን የተጠቃ ግለሰብ እያደር ተክለሰውነቱ እየመነመነ እየመነመነ ከሰውነት ጎዳና ይወጣል። አንዳንዶች ይህንን በሽታ ከኤድስ ጋር ሲያመሳስሉት በገጠር ያሉ አዋቂዎች ግን በፍጡም ከኤድስ ጋር አይገናኝም ባይ ናቸው።
እናም ኢህአዴግ እያደር ተክለሰውነቱ እየመነመነ እየመነመነ መንሰኤው ባልታወቀ “የቤት ጣጣ” ህመም የተጠቃ ይመስለኛል።
ሰሞኑን አንድ መግለጫ “ኢህአዴግ ዲ” በሚል ስም ተልኮልኝ አይቼው ነበር። ኢህአዴግ ዲ በሚል የተሰናዳው ይሄው መግለጫ፤ “በሀገሪቱ ውስጥ ኢህአዴግ ስላመጣው እድገት” ይገልፃል ወረድ ብሎ ደግሞ ስላመጣው እብደት ያወራል። በእብደቱም “የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ድርጅታችን በጥቂቶቹ የህውሃት ሰዎች ቁጥጥር ስር ነው እና ለውጥ ያስፈልገናል” ይላል።
ይሄው “ኢህአዴግ ዲ” በቅርቡ መሪውን እና “ዲ” አልባውን ኢህአዴግ የሚዋጋበትን የፓርቲ ፕሮግራም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።
እውነት እውነት እላችኋለሁ ኢህአዴግ ታሟል። እግዜር እንደሚሆን ያድርገው! ብለን እንመርቅ! አሜን!

No comments:

Post a Comment