Translate

Wednesday, October 10, 2012

ከሞት በፊት እውነተኛ ክብር


“… ከሁሉ አስቀድሞ ማሸነፍ የሚኖርብን በውስጣችን ያለውን ፍርሃት ነው። ለህወሃት/ኢህአዴግ ታማኝ ሊሆኑ የሚችሉት የጦርና የፀጥታ ኃይሎቹ እንዲሁም የስለላ ተቋሙ የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው የጥቂት ዘረኞች ስብስብ በመሆኑ የሕዝብ እምቢተኝነት ሲጠናከር በቀላሉ ይመክናሉ። አመራሮቹ አስተሳሰባቸው በጣም ጠባብ፤ ብቃታቸውም እጅግ ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም እነዚህ ኃይሎች ሁሉንም ነገር እንደተቆጣጠሩት አድርጎ ማሰብ ራስን ማዋረድ ነው። ስለዚህም መሸሽ ሳይሆን በየጊዜው ልንፈታተናቸው፣ ልንጎነትላቸውና ልንፋለማቸው ይገባል። ስለሆነም ካሁን በኋላ ሥራው ህወሃት/ኢህአዴግን ከውስጥ ሆኖ የመበታተንና የማፍረስን ሥራ ነው። የነጻነት ኃይሎችም መዋቅራቸውን በማስፋትና በርካታ ህዋሶችን በመፍጠር በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ። የህወሃት/ኢህአዴግን የመዋቅር ስፋት በነፃነት ኃይሎች የመዋቅር ስፋት መጋፈጥ ይቻል ዘንድ ትግሉ ተፋፍሟል…
“… ስለዚህ ፍትሕ፣ ሰላም፣ አንድነትና ዕርቅ የሚሰፍንባትን “አዲሲቷን ኢትዮጵያ” በጥቅም ተደልለው ወይም በፍርሃት ነፃነታቸውን አሳልፈው በሚሰጡ ሰዎች መገንባት አይቻልም። የሕዝብ እግዚኦታ፣ ለቅሶና ምሬት ወደ ተግባር ሲለወጥ የማሳሰቢያ፣ የንሰሃ ወይም የጥሪ ጊዜ አይኖርም፡፡ ከላይ እንደጠቆምነው አሁን እየቀረበ ያለው ጥሪ የኢትዮጵያ መሆኑን ልብ ይበሉ:: ይህንን ጥሪ ንቆ ነገ “እኔኮ ትዕዛዝ ፈጻሚ ነበርኩ” የሚሉ ሁሉ ይህ ጥሪ ራሱ የወንጀላቸው ማስረጃ ሆኖ እንደሚቀርብባቸው መገንዘብ አዋቂነት ነውና ይህንን እየራደ የሚገኝ ሥርዓት “እንቢ!” ያሉ ወገኖቻችን የሚኖራቸውን ሞገስና ክብር፤ ከማይቀረው የኢህአዴግ ውድቀት በኋላ ተባባሪዎቹ ላይ ከሚደርስባቸው ውርደት ጋር በማነጻጸር ዛሬ ለእውነት እንቁም፡፡ ወደ ልባችን እንመለስ!! ለጥሪውም ምላሽ እንስጥ!!”

ይህ ከላይ የተቀመጠው መልዕክት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “ደወል” በሚል ርዕስ ለስርዓቱ ታዘዦች በተከታታይ ካስተላለፈው መልዕክት ሁለተኛው ቁጥር ላይ የተቀነጨበ ነው። ሃሳቡን ቀንጭበን የወሰድነው ነገር ለመድገም ፈልገን ሳይሆን የወቅቱን ሁኔታ ለማሳሰብ ያህል ነው። ስጋታችንን ለመጠቆም ነው።
ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት እንዴት ኖረ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ በስለላ፣በወታደራዊ ሃይል፣ በድርጅታዊ አቅም ግዝፈቱ ሳይሆን የተቃዋሚው ጎራ ቁልፍ ድክመትና ራዕይ አልባነት እንዳለ ሆኖ፣ በ“የነጻነት ተፋላሚዎች” የተሸናፊነት ስሜትና በውስጣቸው ባለ ፍርሃት ሳቢያ ነው። ዛሬ ኢህአዴግ ያለበትን ትክክለኛ ትኩሳት መረዳት ለሚችሉ ስርዓቱ “በስብሷል፣ ሸትቷል” በማለት ከቁጥር በላይ ማስረጃዎች ራሳቸውን መጥቀስ ይቻላል። ስጋታችን የሚነሳው ከዚሁ ከመበስበስ አደጋ ላይ ይሆናል።
ኢህአዴግ ባለስልጣናቱ በሙስና የገለሙ፣ ከድሃ ህዝብ ላይ በመዝረፍ አጥንቱን የሚግጡ፣ አገርን ከመምራት ይልቅ በተራ ዝርፊያና በረከሰ ወንጀል የተጨማለቁ፣ የስብዕናቸው እድፈት ሊደበቅ የማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰባቸው፣ የሸተተ ስርዓትና አመራር አገርናና ህዝብን ተቆጣጥረው እንደሚኖሩ አድርጎ ማሰብ ከላይ እንደተገለጸው ራስን የማዋረድ ያህል ቢሆንም ከሁሉም በላይ እኛን የሚጨንቀን የአገራችን የወደፊት ጉዳይ ነው።
አሁን ባለው የመቧደንና የመሰነጣጠቅ አዝማሚያ፣ ስርዓቱና ባለስልጣኑ ከደረሱበት የመሞሻለቅ አፋፍ ላይ እንደ ቆምን ይሰማናል። ባለን መረጃና በያቅጣጫው ከሚታዩት ምልክቶች አንጻር የሚፈርስ ስርዓት ስለመኖሩ መጠራጠር አቁመናል። ይህንኑ የመፈራረስ አደጋ ለማስታገስ እንደተለመደው ስታሊናዊ ርምጃዎች በቅርቡ እንደምንሰማም አይታበልም። በዚህ ሁሉ መደነባበር ውስጥ አገራችንን የሚሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ከወዲሁ ዝግጅታቸውን ሊያደርጉ ይገባል እንላለን።
ታሪክ ሰርቶ ማለፍ በደልን ሁሉ ያስረሳልና ለአገራችን ሲባል፣ ለህዝብ ሲባል፣ ለራስ ሲባል፣ ለራስ ልጅ ልጆች ሲባል፣ ማለፍም ስላለ ኢህአዴግ በቅድሚያ አገራችንን የሚታደግ ርምጃ ቢወስድ ሁሉንም ያቀለዋልና አገርና ህዝብ ደስ እንደሚላቸው ጥርጥር ለውም። ተቃዋሚዎችም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ትግልንና ዓላማን ወደ መሬት ለማውረድ ሊረባረቡ የሚገባቸው ወቅት ላይ እንደ ሆኑ ቢያውቁትም ልናስታወሳቸው እንወዳለን። በየደረጃው ያለን የኢትዮጵያ ልጆች ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ በማስተዋል ልናደርግ ይገባልና አገርን ለሚጠቅም አጀንዳ ሁሉ በመነዳት ሳይሆን አስተዋይነት በተሞላው መንገድ ተባባሪነትን ማሳየት እንደሚጠበቅ እንጠቁማለን። ለማንኛውም የፖለቲካ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል። ባለሙያዎቹ የንስሃን ጊዜ ሲያበጁ ከሞት በፊት ንስሃን ይፈጥን ይሆናል!! ህዝብ ይቅር ካለ አገርም ትጠቀማለች። መጪው ትውልድም ባለው ለመቀጠል ይታደላል። ግን ባስቸኳይ ይሁን!!

No comments:

Post a Comment