Translate

Wednesday, October 3, 2012

“መንግስት ከንግዱ ዘርፍ እጁን ጨርሶ ይሰብስብልን” ሲሉ ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ ጠየቁ


ኢሳት ዜና:-ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት፤ በኮምቦልቻ ከተማ  የሚያሠሩትን የጦሳ ብረታብረት ፋብሪካ  ለመገንባት ኮንትራቱን ካሸነፈው የጣሊያን ኩባንያ ጋር  ሲፈራረሙ  ባደረጉት ንግግር ነው።
 ‹‹መንግሥትን የምለምነው የንግዱን ነገር ለእኛ እንዲተውልን ነው፤ መንግሥት በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ሰላምና ፀጥታ በማስከረበር ላይ ቢበረታ መልካም ነው >>በማለት ነው ልመናቸውን ያቀረቡት።
አል-አሙዲ መንግስት ጨርሶ ከንግዱ እንዲወጣ  ጥያቄ ያቀረቡት፤ በአዲሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በትምህርት ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እየተመራ በስፍራው ለተገኘው የመንግስት ልዑክ ነው።
ከባለሥልጣናቱ መካከል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጐበዜ፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ስብሐት ነጋና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡
ላለፉት 21 ዓመታት አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ዓለማቀፍ የንግድና የገንዘብ ተቋማት ይህን ጥያቄ ቢያቀርቡም  ፤በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ውድቅ ሲሆንባቸው ቆይቷል።

ሼህ መሀመድ ሁሴን አል አሙዲ  ፦የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ይህን ጥያቄ ማንሳታቸው፤ ብዙዎችን ከማስገረሙም አልፎ የተለያዩ አስተያየቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል።
አንዳንድ ወገኖች የሼሁ ጥያቄ  አዲሱ አመራር በኢኮኖሚ ፖሊሲው ዙሪያ ሊያደርግ ያሰበው ለውጥ እንዳለ የሚጠቁም ነው ሲሉ፤ሌሎች ወገኖች ግን፦<<አል-አሙዲ ይህን ጥያቄ በአቶ መለስ ጊዜ ያላነሱት መለስን ይፈሩዋቸው ስለነበረ ችግር እንዳይፈጥሩባቸው በመጠንቀቅ ነው።ቀሪዎቹን ባለሥልጣናት ግን  በገንዘብ እንደፈለጉ ሲያሽከረክሯቸው  ቆይተዋል።ከዚህ አንፃር የአል-አሙዲ ጥያቄ፤ ያሉትን ሹመኞች ከመናቅ በዘፈቀደ የቀረበ እንጂ፤ የፖሊሲ ለውጥ መኖሩን አመላካች አይደለም>>ይላሉ።
ከመጋረጃው ጀርባ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው የሚባሉት አቶ በረከት ስምዖን፦< የሁለቱ ምርጫዎች ወግ> የተሰኘ መጽሐፋቸውን ሲያስመርቁ ንግግር ያደረጉት ሼህ አል-አሙዲ፦”በረከትን ደቡብ አፍሪካ እያሳከምኩት ሳለ ለአማራ ልማት ማህበር በዓል ወደ አገሬ ካልሄድኩ ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ እጁን አንጠልጥዬ  ኢትዮጵያ አድርሼ መለስኩት”ማለታቸው ይታወሳል።
አል-አሙዲ መንግስት ከንግዱ እጁን ጨርሶ እንዲያነሳ በጠየቁበት ንግግራቸው፦<<‹‹ነጋዴዎች ስንባል ቀጣፊዎች ነን፡፡ ይህ ባህሪ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ አይደለም፤መንግሥት አንዳንዴ ዓይኑን ቢጨፍንልን ጥሩ ነው፤››ሲሉም ተደምጠዋል።
የአገሪቱ የንግድ ዘርፎችና ታላላቅ ኩባንያዎች በህወሀት ቁጥጥር ስር በወደቁበት ጊዜ ሼህ አል-አሙዲ ይህን ደፋር ጥያቄ መሰንዘራቸው፤  የህወሀት ቁንጮዎችን ሊያስቆጣ እንደሚችልም እየተነገረ ነው።

No comments:

Post a Comment