Translate
Tuesday, October 30, 2012
ኢትዮጵያ ለግብጽ አንድ ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር መሬት ልትሰጥ ነው
ኢሳት ዜና:-እየተገነባ ባለው የህዳሴው ግድብ ሳቢያ ግብጽ ችግር ልትፈጥርብን ትችላለች የሚል ስጋት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊ ሚዲያዎች ሲስተጋቡ ቢሰሙም፤ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን በተቃራኒው በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለው የልማት ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን ነው ይፋ ያደረጉት።
የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሺም ካንዲ በቅርቡ በአልጀሪያ ባደረጉት የሁለት ቀናት ጉብኝት ላይ ፤አገራቸው ፤ በአልጀሪያና በኢትዮጵያ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖችን ለመገንባት ማቀዷን አስታውቀዋል።
የግብጽ የማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳለው ፤ግብጽ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2014 ዓም ከመድረሱ በፊት በ አልጀሪያ 2 ጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ይፋ አድርገዋል።
<<አህራም ኦንላይን>>የተሰኘው የግብጽ ተነባቢ ድረ-ገጽ በፎቶ አስደግፎ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ለግብጽ 1 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር መሬት እንደምትሰጥ አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ መንግስት መሬቱን የሚሰጠው ግብጽ በኢትዮጵያ ለምትገነባው የኢንዱስትሪ ዞን እንዲውል ሲሆን፤ይህም በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ወደተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሏል።
የግብጽ የኢንዱስትሪና የውጪ ንግድ ሚኒስትር ሀቲም ሳላህ ባለፈው ረቡዕ፦ ግብጽ በኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ 50 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ሥራቸው በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፎች ድጋፍ የሚካሄድ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለግብጽ ያዘጋጀው 1 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር መሬት በምን መልክ እና በምን ያህል ዋጋ እንዲሰጥ በዘገባው አልተገለጸም።
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸውና ግማሽ ሄክታር ከማይሞላ ማሳቸው <በልማት ስም>ያለ ካሳ እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ከሱዳንና ከግብጽ በኩል ከፍ ያለ የደህንነት ስጋት እንደተጋረጠበት በደጋፊ ድረ-ገጾቹና ጋዜጦቹ አማካይነት ሲወተውት ይሰማል።
ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን-ኢሳት ከግብፅ ድጋፍ እንደሚደረግለትና ከአገር ጠላት ጋር እንደሚሰራ በመወትወት የቴሌቪዥን ጣቢያው በአጭር ጊዜ በሚሊዮን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የገነባውን መልካም ገጽታና ምስል በሀሰት ለማጠልሸት ተደጋጋሚ ክሶችን ሲያሰማ ይደመጣል;
የኢህአዴግ መንግስት ከጎረቤት አገሮች በተለይም ከግብጽና ሱዳን ጋር ስጋት እንደተጋረጠበት በሚያስነግርበት ወቅት፤ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው ሀቅ 1 ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር መሬት ለግብጽ ለመስጠት እየተዘጋጀ እንደሆነ መገለጹ፤ዜናውን የሰሙ ወገኖችን ሁሉ ያስገረመ ሆኗል።
<<በጎረቤት አገሮች ስጋት ተጋርጦብኛል>> የሚለው ውትወታ፤ ከመጋረጃው ጀርባ በልማትና ኢንቨስትመንት ስም በአገር ላይ እየተፈጸመ ካለው ደባ የህዝብን ትኩረት ለማሳት እንዲሁም ሊመለሱ ያልቻሉ አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን እና የተፈጠረውን ፖለቲካ ውጥረት ለማዳፈን ነው>>ብለዋል-አንድ በዜናው የተገረሙ የመድረክ አመራር።
ኢህአዴግ ቀደም ሲል የአማራ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሆነ ሰፊ መሬትን ለሱዳን መስጠቱ ይታወሳል።
ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ህዝቡ የከፋ ምሬት ማሰማት በጀመረበትና መንግስት በህዝብ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት በድንገት የታወጀው የዓባይ ግድብ ግንባታ፤ከጅማሬው ዋዜማ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከልማታዊ ትርጉምነቱ ይልቅ ፖለቲካዊ ፍጆታው እንደጎላ፤ ብዙዎች ይስማማሉ።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment