Translate

Wednesday, October 10, 2012

የኢሕአዴግ ታጋዮች ጡረታ ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ሊሰላ ነው


ኢሳት ዜና:-የቀድሞውን ወታደራዊ አገዛዝ የመገርሰስ ትግል ውስጥ የተሳተፉና በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች ጡረታ (ማኅበራዊ ዋስትና) ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እንዲሰላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ  ማሳሰቡን ሪፖርትር ዘገበ
ለመንግሥት ተቋማት የተሰራጨው ደብዳቤ ከሰኔ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል፡፡  ከአምስት ወራት በፊት፣ ሰኔ 18 ቀን 2004 ዓም ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ኢሳት የሚከተለውን ዘገባ አቅርቦ ነበር ።
በነፍጥ ትግል የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረውና በአሁኑ ሰዓት ግን በትጥቅ ትግል ለውጥ ለማካሄድ የተደራጁ
የተቃውሞ ኃይሎችን በአሸባሪነት የሚፈርጀው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ለቀድሞ ታጋዮቹ ላሳለፉት የትግል ዘመን ልዩ
የጡረታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ደንብ አወጣ፡፡

በዚሁ ደንብ መሰረት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች ታጋይ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰኔ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀድሞ ታጋዮች የትግል ዘመን
የጡረታ አገልግሎትን በተመለከተ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በአቶ ሙክታር ከድር የጠ/ሚ ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ሚኒስትር ፊርማ ሰሞኑን የወጣው ሰርኩላር ደብዳቤ እንደሚለው
በሹመትና በሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛነት በመንግስት መ/ቤቶች በመሥራት ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች የአገልግሎት
ዘመንን አስመልክቶ ጥያቄ መቅረቡን ያሰታውሳል፡፡ በዚሁ መሠረት በጉዳዩ ላይ የሚኒስትሮች ም/ቤት ሰኔ 1 ቀን
2004 ተወያይቶ በመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ በሚሸፈኑ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግስት መ/ቤቶች
በቋሚነት በመቀጠር ወይም በሹመት በመመደብ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋይ አባላት ቀደም ሲል በመከላከያ
ሠራዊት፣በፌዴራል ፖሊስና በማረሚያ ቤቶች ለተመደቡት የቀድሞ ታጋዮች በተወሰነው መሰረት አገልግሎቱ ወደ ትግሉ
ከተቀላቀለበት ጊዜ አኳያ ሶስት ዓመት እየተቀነሰ እንዲያዝላቸው ያዛል፡፡
በተጨማሪም ከመንግስት ሠራተኞች ማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ታጋዮቹ ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ
አንስቶ እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከፈጸሙት አገልግሎት ሶስት ዓመት እየተቀነሰ እንደአገልግሎቱ
ዓይነት በወታደራዊ ወይም በሲቪል በየወሩ መከፈል የሚገባው የአሰሪ መ/ቤትና የሰራተኛ ድርሻ የጡረታ መዋጮ ታሰቦ
በመንግስት እንዲሸፈን ደንግጓል፡፡
እያንዳንዱ የክልል አስተዳደር ካቢኔ ወይም የፌዴራል መ/ቤት ከፍተኛ ኃላፊ በዚሁ ውሳኔ መሰረት በትግል ላይ
ያሳለፉትን ጊዜ ለጡረታ ሊታሰብላቸው የሚገባቸውን የቀድሞ ታጋዮች ዝርዝር መረጃ በማጠናቀርና በማረጋገጥ
ለመንግስት ሠራተኞች ማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እንዲያሰተላልፍ በጥብቅ አዟል፡፡
በዚሁ ደንብ መሰረት በአሁኑ ሰዓት ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ ያሰቆጠሩትና ወደጡረታ እያዘገሙ የሚገኙትን
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ እነአዲሱ ለገሰ፣ተፈራ ዋልዋ፣በረከት ስምኦን፣ስብሃት ነጋና ሌሎች ከፍተኛ
ባለሥልጣናት በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤውን ያሰራጨው በሕግ ላይ ተመሥርቶ ይሁን አይሁን በእርግጠኝነት ለመናገር እንደማይችሉ የሪፖርተር ምንጮች የገለጹ ቢሆንም፣ ምናልባት ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ መመርያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ሊሆን እንደሚችልና ደብዳቤውም በዚህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን መግለጻቸውን ጋዜጣው በዛሬ ዘገባው አመልክቷል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁሁ የምክር ቤቱት አባላት የመረጃውን ትክክለኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ማንነታቸውን የሚገልጽ፣ ትግሉን የተቀላቀሉበትን ወቅትና በአሁኑ ጊዜ የሚያገለግሉበትን የመንግሥት ተቋምና ሌሎች ጉዳዮችን በተዘጋጀ ቅጽ ላይ መሙላታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ቅጽ ከሞሉ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ በድጋሚ ማስታወቂያ እንዳወጣ፣ ማስታወቂያውም የተሞላውን ቅጽ ተንተርሶ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምላሽ እንዲሰጥበት የላከው ደብዳቤ በመኖሩ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ የሚያቀርብ ነው በማለት ለጋዜጣው ዘጋቢ ገልጠዋል።

No comments:

Post a Comment