Translate

Saturday, October 13, 2012

ወያኔ የብጫ ትርጉም አይገባውም፤ ምሱ መገደድ አሊያም መወገድ ነው!!!


ዓርብ መስከረም 25 ቀን 2005 ዓም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለወያኔ አገዛዝ ብጫ ካርድ አሳዩ። ብጫ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ብዙ ትርጉሞችን ያለው ቀለም ነው።
1ኛ.         ብጫ የሰንደቅ ዓላማችን ቀለም ነው። እንደሚታወቀው የሰንደቅ ዓላማችን ሶስቱ ቀለማት የየራሳቸው ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው። አረንጓዴው ተስፋ፣ ልምላሜና ሀብት፤ ብጫው ሃይማኖት፣ አበባና ፍሬ፤ ቀዩ ፍቅር፣ መሥዋዕትነትና ጀግንነትን ይወክላሉ።
2ኛ.        በእግር ኳስ ጨዋታ ህግ ብጫ ማስጠንቀቂያ ነው። አንድ ተጫዎች የጨዋታ ህግ ክፉኛ ሲተላለፍ ብጫ ካርድ በመጨረሻ ማስጠንቀቂያነት ይሰጠዋል። ተጫዋቹ “ደግመህ ብታጠፋ ትባረራለህ” መባሉን አውቆ ህግን አክብሮ ተጠንቅቆ መጫወት ይጀምራል ደግሞ ካጠፋ ከጨዋታዉ እንደሚባረር ያውቃል።
3ኛ         በትራፊክ ህግ ብጫ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ምልክት ነው። ህግን የሚያከብር አሽከርካሪ ብጫ የትራፊክ ምልክት ሲያይ ራሱንም ሊሎችንም ከአደጋ ለመታደግ ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርጋል።
መስከረም 25 ቀን 2005 ዓም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብጫ ካርድ ማሳየታቸው ከላይ በዘረዘርናቸው ሶስቱ ትርጓሜዎች አንፃር ካየነው ትልቅ መልዕክት ያለው ተግባር ነው።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብጫ ካርድ በማሳየት ወያኔን “ሃይማኖታችንን እንወዳለን፤ ጣልቃ አትግባብን” ብለውታል። ኢትዮጵያዊያን ለእምነታችን ያለን ክብር በሰንደቅ ዓላማችን ውስጥም የሰፈረ ጉዳይ ነው። እላይ እንደተገለፀው ብጫ የሃይማኖት፣ የአበባና የፍሬ ምሳሌ ነው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብጫ ወረቀት፣ ፊኛና ጨርቅ በማሳየት ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ክብር በማሳየት ወያኔ ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ብጫ የማስጠንቀቂያም ምልክት ነውና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብጫ ካርድ በማሳየት ወያኔን “የምትሠራው ሥራ ህገወጥ ነው። ከዚህ ተግባር ታቀብ፤ አለበለዚያ ወዮልህ!”  የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብጫ ካርድ ሲያሳዩ “ወያኔ ሆይ በያዝከው መንገድ መጓዝ ከቀጠልክ በራስህም፣ በእኛም በአገራችንም ላይ አደጋ ይደርሳልና ታቀብ!” ማለታቸው ነው።
ዘረኛውና አምባገነኑ ወያኔ ግን ማሳሰቢያውንም ሆነ ማስጠንቀቂያውን አልተቀበለም። ወያኔ የሰንደቅ ዓላማችንን ክብር የሚያውቅ አይደለምና በብጫው ቀለም ስለተወከሉት ሃይማኖት፣ አበባና ፍሬ ደንታ የለውም። ወያኔ ለህግ የበላይነት ደንታ የለውምና ብጫ የማስጠንቀቂያ ካርድ ምኑም አይደለም። ወያኔ ለአገርና ሕዝብ ደህንነት ደንታ የለውምና እንኳንስ በብጫ ሊታቀብ ቀዩንም ቢሆን ጥሶ ያልፋል።
ወያኔ ማሳሰቢም ሆነ ማስጠንቀቂያ የማይገባው ግብዝ መሆኑ እሁድ መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም. በግልጽ ታይቷል።  አዛውንቶችንና ደካሞችን በማስገደድ ወደማይፈልጉት ምርጫ ሄደው በመራጮች መዝገብ ላይ እንዲፈርሙ አደርጓል። ወያኔ ግብዝ በመሆኑ ነው በትህትና የቀረበለትን አቤቱታና ማስጠንቀቂያ መቀበል ተስኖታል።
በወያኔ ግብዝ አስተሳሰብ መሠረት ለቴሌቪዥን ካሜራ የሚሞላ ሰው ከተገኘ በቂ ነው። ገለልተኛ ታዛቢ በሌለበት ቁጥሮችን  መሙላት ቀላል ነው፤ ወያኔ ይህንን ከመፈፀም የሚያግደው ይሉኝታ አልፈጠረበትም። እሁድ መስከረም 27 ቀን 2005 ዓም የተደረገው ይህ ነው። ጥቂት ሰዎች ተገደው ወጡ፤ የብዙ ሰዎች ስም መዝገብ ላይ ሠፈረ።
በመሠረቱ በወያኔ የተስተናገዱ ምርጫዎች ሁሉ እንደዚሁ ነበሩ። ወያኔ ጥቂትም ቢሆን የተቸገረው በ1997 ምርጫ ብቻ ነበር፤ ያኔም ቢሆን ችግር ገጥሞት የነበረው ታዛቢዎች በርከት ባሉባቸው ከተሞች ውስጥ ብቻ  ነበር።
ለወደፊቱም ወያኔ ምርጫ እንዲያስተባብር ከተፈቀደለት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። በምርጫ ማጭበርበር የወያኔ ተፈጥሮዓዊ ባህርይ ነው።
አንደኛ ዓመቱን ሊያከብር የተቃረበው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እንቅስቃሴ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን አሳይቶናል። የዓርብ መስከረም 25 ቀን 2005 ዓ.ም.ቱ የብጫ ካርድ ማሳየት ሥነሥርዓት በመልዕክቱ ይዘትም ሆነ በአደረጃጀቱ ታሪካዊ ለመባል የሚበቃ ነው።
ሆኖም ግን ወያኔ ብጫ ቀለም የሚያይበት ዓይን የለውም። ወያኔ የሕዝብን ጩኸት የሚሰማበት ጆሮ የለውም። ለሁላችንም የሚበጀው ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ የምንችልበት አቅምና መንገድ ማዘጋጀት ነው። ለዚህ ታላቅ ግብ ጠንክረን እንሥራ።
               ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

    No comments:

    Post a Comment