“ምርጫ ግም አለ፡፡ አለም አቀፍ ሰላምም ታወጀ፣ ተኩላዎችም የጫጩቶቹን እድሜ ለማስረዘም ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ፡፡” ጆርጅ ኢሊየት
“ኢህአዴጎ ኢህአዴጎ፤
ገና ትበላለህ ወተትና እርጎ፡፡”
ኢህአዴግ ንዑስ ከበርቴ ከሚለው ከተሜው ይመንጭ ወይም ከአርሶ አደሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስነ-ቃሉ ተረት ተረት ሊመስል ይችላል፡፡ እውነታው ግን ወዲህ ይመስለኛል፡፡ “እናንተስ ማን ትመስሉ፡፡” የሚል መሰረታዊ ጥያቄን ያቀፈ መሆኑ ግን ጥርጥር የለውም፡፡
በሕዝብ ጥቅም ስም ተደራጅተናል፣ አምላክ ቀብቶናል፣ በወታደሩ ተወክለናል በማለት ሕዝብን ነጻነቱን ለይስሙላ አረጋግጠው ሚሊኒክ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ እራሳቸውን ተግተው የሚያገለግሉ በርካታ አምባገነኖችንን መታዘቡ የፈጠረበት ስጋት እንደሆነ አምናለሁ፡
ከሃያ አንድ ዓመት በኋላ ጥርጣሬው ጥርጣሬ ሆኖ ቀረ ወይስ የተጠረጠረው ደረሰ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ወቅታዊ ነው፡፡ እውነቱና እውነቱን ብቻ መዳሰስ አስፈላጊም ግድም የሚል ነው፡፡ በመረጃና በእውነታ ላይ ሳይመሰረቱ መተቸት ሮሮ ከመሆን አይዘልቅም፡፡ መፍትሔም አያመጣም፡፡
ሃያ አንድ ዓመት ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ለውጥ ታጥቆ ለተነሳ ቀላል የሚባል ጊዜ አይደለም፡፡ በሃያ ዓመታት ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ በማካሄድ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካም ሆነ የኤስያና የካረቢያን ሃገሮች በኢህአዴግ የሚጠቀሱትን ጨምሮ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ማስፈን ችለዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ እድገትንና ልማትንም ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ሃያ አንድ ዓመት በትውልድ ሚዛን ሲለካ ሙሉ ሰውነትንና ሕይወትን ለመምራት ብቁ መሆን የሚቻልበት ጊዜ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስንመዝነው ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት ተወልዶ በጫካ ትጥቅ ትግል ጎልብቶ ሃያ አንድ ዓመት በስልጣን መንበር ላይ ቢቆይም ዛሬም እልህ አስጨራሽ ሰላማዊ ትግል የሚካሄድበትና፣ አዝጋሚ ልማታዊነት የሚሰበክበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ የብዝሃነትና የመድብለ ፓርቲ መገለጫ የሆኑት የተለየዩ ሃሳቦችን በነጻ የማንሸራሸር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡ በኢትዮጽያ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ሕገ-መንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ከማግኘትም በላይ ለአፈጻጸሙ ሕጎች የተደነገጉ ቢሆንም ዛሬም አፈጻጸሙ ከእቅድና ከሕግጋት አልፎ ወደ ተግባር መለወጥ አልተቻለም፡፡ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት አማራጭ የማዳመጥ /የማቅረብ / ሕዝባዊ መብት መሆኑ ላይ ብዥታ ባይኖርም፣ ተጠቃሚው ሕዝብ በጥርጣሬ ስለሚታይና የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት በሕዝብ ከሚታመነው ከመንግስት ውጭ የማንም እንዲሆን አልተፈለገም፣ አልተፈቀደም፡፡
መብቶች ዛሬም በመታመንና ባለመታመን መካከል እየተመዘኑና እየተቆጠቡ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሕዝብ መብቱን መጠቀም ይችላል ወይም አይችልም የሚሉ መቆጣጠርያ ተቀጽላዎች ተበጅተውለታል፡፡ ሕገ-መንግስቱ የሰብአዊ፣ የዴሞክራሲያዊና የነጻ አስተሳሰብ መገለጫዎችን በተሟላ መልኩ ቢያጎናጽፍም መብቶቻችንን በተግባር ለመተርጎም እንዳይቻል በየእለቱ በሚጸድቁ ጎታች መመርያዎችና ደንቦች አይነተኛ ደንቃራዎች ሆነዋል፡፡ ያለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ከዴሞክራሲና ከመልካም አስተዳደር አኳያ አድሮ ጥሬ ሆነው ቢያልፉም ሰሞኑን ከኢህአዴግ በኩል ተከታታይነት ያላቸው ጥሪዎችና ጅማሮዎችን እየሰማንና እያያን ነው፡፡ እሰየው ያስብላል እንበል ይሆን? ኢዴፓ ለረጅም ጊዜ የታገለለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስራ ዘመን የመገደብ ጉዳይ ጆሮ አግኝቷል፡፡ ኢዴፓ ላለፉት አስራ አምስት አመት ሲጮህለት የኖረው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስልጣን ዘመን የመገደብ አስፈላጊነት፤ ሕገ-መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ ውጤቱ የማያዳግም መተማመኛ ስለሚሆን በቅጡ ሊታሰብብት ይገባል፡፡
ሕገ-መንግስታዊ መብቶቻችን እንዲከበሩና በተግባር እንዲውሉ ስንጮህ ኖረን ዛሬ ሰሚ ጆሮ በማግኝታችን ጥሪው የሚወደስ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ጅማሮው እንዳይደናቀፍ የዴሞክራሲ ጠላቶች ጆሮ ይደፈን በሚል መፈክር ሁሉን ዘግቶ ወደ እንቅስቃሴ መሸጋገር ግን የተሟላ መፍትሔ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ መላው ሕብረተሰብ በችግሮቻችንን መንስኤዎቻቸውንና መፍትሄዎቹ ላይ ዘለቅ ብለን፣ ከተቻለ በጋራ ካልሆነም የተገኘውን መገናኛ ብዙሃን ተጠቅመን መፈተሽ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በችግሮቹ ላይ መግባባት ሳይፈጠር በመፍትሔዎቹ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ መጣር መፍትሔውን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ ከመሆን አያድነውም፡፡ በመልካም አስተዳደር አማካኝነት ፍትሕና ርትእ የማግኘት፣ ያለአድሎ የመዳኘት፣ ያለመገለልን አስመልክቶ በመብትና ነጻነት ዙርያ የሚነሱ እንደ መደራጀት፣ መሰብሰብ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመቃወም፣ የማምለክ፣ በሰላም የመኖር፣ በኢኮኖሚያዊ መብቶች ዙርያ ሃብትን ያለገደብ የማፍራት፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣በስጦታ የማስተላለፍ፣ የማውረስና ሌሎችም መሰረታዊ ጥያቄዎች የዴሞክራሲ ሀ ሁ መሆናቸውን በሁላችንም ዘንድ በቅጡ መግባባት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህን ሁለንተናዊ መብቶች መሰረት ያላደረገ ዴሞክራሲ ሌላ ነገር እንጂ ዴሞክራሲ ሊሆን አይችልም፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትና በሂደት እያደጉ የመጡትን ሰብአዊና ተፈጥሮአዊ መብቶች ባለቤት የሌላቸውና በተፈጥሮ የተሰጡ ጸጋዎች ናቸው ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ በመነሳት ፍልስፍናቸውን ከሚያራምዱት ዓለም አቀፍ ምሁራን ጀምሮ፣ መብቶች ከሕግ ማዕቀፍና ከስርዓት ብቻ የሚመነጩ የስምምነት ውጤቶች ናቸው የሚሉትን በርካቶችን አካትቶ፣ መብት የግለሰብ ሳይሆን ከቡድንና ከማህበረስብ ወይም ከብሄሮች ማህበራዊ ግንኙነት ነው የሚሉትን ኮሚኒስቶች ይዞ የዘለቀው የፍልስፋና ግብግብ ዛሬም ነባራዊ ግጭቱን ይዞ እንደቀጠለ ነው፡፡
ፍልስፍናዊ እሰጣገባው ከላይ የቀረበውን ቢመስልም በሁለንተናዊ መልኩና ቅርጹ የሕግ ውጤት የሆነው ናዚዝም ጥሎልን ያለፈው እጅግ አሰቃቂና አሳፋሪ፤ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መብትን፣ ነጻነትን፣ እኩልነትን ከሞራልና ከተፈጥሮ ዘለግ ካለም ከሃይማኖት ለማፋታት ያለሙ በርካታ ፍልስፍናዎችን በከባዱ ጥያቄ ውስጥ ጥሎ አልፎአል፡፡ በዚህም ምክንያት የመብት፣ የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎች መነሻ ፍልስፋና ሃይማኖታዊም ይሁን ሞራላዊ አሊያም ሕጋዊ ቢያንስ ቢያንስ ግን የሰው ልጆችን እኩልነት ከማክበርና ከማስከበር አኳያ ሚዛናዊነት ከጎደለው ከጅምሩ ትርጉም የሌለውና አደገኛ ዝንባሌ ከመሆን እንደማይድን ከናዚዝም በተጨማሪ በርካታ የታሪክ ሂደቶች አረጋግጠዋል፡፡
ለዚህ የሚመጥኑና የሚያግዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዎና ማህበራዊ በላኤ ሰቦችን (bogeyman) የሃያኛውና የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመናት በበቂ መጠን መቀፍቀፍ ችለዋል፡፡ እንደ አለም አቀፍ ሽብርተኝነት፣ ብሔራዊ ጥቅም (national Interest) የመሳሰሉት የተጋነኑ ማስፈራሪያዎች ለአምባገነን መንግስታት መብትን ለማፈንና በጥቅሉ ለመንፈግ መነሻ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ ታቅደውና ተቀነባብረው የሚገባባቸው ጦርነቶች፣ በነዳጅና በከበሩ ማዕድናት ፍለጋ ስም የሚቀነባበሩ ግጭቶች፣ ልማትን ታከው ነባር ነዋሪዎች የሚያፈናቅሉ የመሬት ወረራዎች፣ አገር በቀል ሕዝባዊ ድጋፍ መሰረት ያደረጉ እምቢተኛ ንቅናቄዎችን፣ መንግስታትንና ስርአቶችን ለማስፈራራትና ለማሸማቀቅ የሚመሰረቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአፈናውና ለረገጣው አይነተኛ መሳሪያ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ያቆጠቆጠው አለም አቀፍ ኢምፔርያሊዝም የወለዳቸው የቀድሞው ኮንጎ መሪን ሞቡቶ ሴሴኮን፣ “ምንም ያህል ብትሮጥ ከጥይት አታመልጥም” በሚል መፈክር የተቃወሙትን የፍትሕ አካላትና አስፈጻሚዎችን ለቅሞ የበላውን ኢዲ አሚንን አይነት አለም አቀፋዊ ሶሻሊዝም የወለዳቸው አምባገነኖች “እያንዳንዱ የፈጸምኩት ድርጊት ለሃገሬ ስል ነው” በሚለው መፈክር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቹን እያጋዘ የገደለውን የካምቦዲያው ፖል ፖት ሃሳብ “ከጦር መሳርያ በላይ አደገኛ ነው፡፡ ጦር መሳርያ የከለከልናቸውን ጠላቶቻችንን ሃሳብ እንዲኖራቸው አንፈቅድም፡፡”በማለት በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ የቀድሞዋን ሶቪየት ሕብረት ዜጎችን እስረኞቹና ምርኮኞቹ ያደረገውን ጆሴፍ ስታሊን አለማችን አስተናግዳለች፡፡
የዘመናችን ኢ-ሊብራሎች መሪዎች (illibrals) ደግሞ ሕዝቦች ምርጫ መኖሩንና ዴሞክራሲ በሕግ መደንገጉን ካወቁ በቂያቸው ነው የሚሉ ናቸው፡፡ መራጩ ሕዝብ ስለምርጫና ስለመብቱ ከማወቁ ውጭ አንዳችም የሚወስነው ነገር የለም፡፡ ምርጫን አስመልክቶ ውጤቱን የሚወስነው ቆጠራውን የሚያደርገው ሃይል ነው፡፡ የመብት ጥያቄ ከሆነ ደግሞ ሽብርተኝነትን የመሳሰሉ “በላኤ ሰቦችን” መደርደር ነው፡፡ መብታችንን ለመግፈፍና መጠቀሚያ ለማድረግ ያሰፈሰፈው ሃይል ቁጥር ጨምሯል፡፡ ሕገ-መንግስቱ ላይ ብናሰፍርልህም አጠቃቀሙ ግር ስለሚልህ ለአጠቃቀሙ መመርያ ያስፈልግሃል፡፡ ስለዚህ መብትህን መጠቀም እስክትችልና የጋራ ጠላቶቻችን እስኪጠፉ ድረስ መብቶቻችን በቁጠባና በገደብ ሆነዋል፡፡ የዘወትር ጥሪውም ይሄው ነው፡፡
በተለያየ ምክንያት የሚቀፈቀፉ የገዢዎች ጥቅምን ያማከሉ ጎታችና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ከያሉበት ተቀድተው ከአምባገነንነትና ከስልጣን ጥም ጋር ተዳቅለው በማደግ ላይ ወዳሉ አገራት ሲዛመቱ መላ ቅጥ የጠፋው፣ ልክና መስፈርት የሌለው አፈናና የመብት ረገጣን አርግዘው እንደሚወለዱ በተለይ እኛ አፍሪካውያን ቋሚ የታሪክ ታዛቢዎች ነን፡፡ የዚምባቡዌውን “የእድሜ ልክ” ገዢ ሮበርት ሙጋቤን፣ የግብጹና የቱኒዚያውን ዘመናዊ አምባገነኖችና ሌሎቹንም እልፍ አእላፍ የአፍሪካ መሪዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ወደ ሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ፣ የዴሞክራሲያና የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎች ከ1987 ዓ. ም. ጀምሮ ሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈሩበት ልክ ቆመው የቀሩ አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ አንዳንዶቹም ጭራሽ ተሸርሽረዋል፡፡ እነዚህ በሕገ- መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና የመብት ድንጋጌዎች ከሃያ አንድ አመት ጉዞ በኋላ ዛሬም ወደ መሬት መውረድ አልቻሉም፡፡ አፈጻጸማቸውና ትርጓሜያቸው ከባድ እክል ገጥሞታል፡፡ በተከታታይ የሚወጡ እንደ ፀረ-ሽብርተኝነት፣ የፕሬስና የመያዶች ሕግጋት በነጻነት የማሰብን፣ የመደብ ጀርባ ሳያጠኑ በነፃነት የመወያየትና መረጃ የመለዋወጥን፣ የመደራጀትንና የመቧደንን መብቶች ጥርጣሬና ጥያቄ ላይ ጥለውታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አጣዳፊና መጠነ ሰፊ የልማት ጥያቄዎች፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶቻችንን ሕገ-መንግስታዊ ከለላ እንዲያጡ አድርገውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ጥረን ግረን ባፈራነው ሃብት የገዛነው ነባር የመሬት ይዞታችንና በላዩ ላይ ያሰፈርነው ሃብትና ንብረት ማጋራትና ማከፋፈል በሚል ስም “በፍትሐዊ አከፋፋይነት” አጀንዳ የመንግስት ሃብት ሆኗል፡፡ ቀሪ ሃብታችንንም የኔ ነው ብለን ለመናገር መድፈር አቅቶናል፡፡
ምርጫዎች ከሃያ አንድ ዓመት እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረድ በኋላ ውጤታቸው መድብለ ፓርቲን የማይወክሉና ዴሞክራሲዊ ተግዳሮቶች የወጠራቸው ሆነዋል፡፡ በእርግጥም ገዢው ፓርቲ ደጋግሞ እንደሚለው “ተመራጭ ፓርቲ” ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሃገር አሸናፊ ወይም ተሸናፊ ፓርቲ መሆን በችግርነት ሊነሳ አይችልም፤ ነገር ግን 99.9 ፐርሰንት ማሸነፍ ሌላው ቢቀር የሚነገርለትን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ትዝብት ላይ መጣሉ አይቀሬ ነው፡፡ የተቃዋሚዎች ድክመት እንዲሁ በባዶ ሜዳ የሚፈጠር ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው አለም ስለማትለይ፣ ችግሩ የጋራ መሆኑን መጠራጠር ለፈተናው አይነተኛ ማነቆ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የመንግስት እዳ ከሃላፊነትም ሆነ ከስልጣን አልያም ከተገባው ቃለ መሃላ ጋር ተዳምሮ እዳው ታሪካዊና የትየለሌ ነው፡፡ የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ተቃዋሚን መውለድ እንጂ ማሳደግ ለምን አልቻለም ሲባል ሕዝባዊ አጀንዳ ስለሌላቸውና ጠንክረው ስለማይሰሩ የሚለውን ጉንጭ አልፋ ክርክር ማንሳት ዘመን ያለፈበት ይመስለኛል፡፡ ጠንክሮ ለመስራት ቢያንስ ምህዳሩ አማራጭ ሃሳብን ለመፈተሽ በቂ እድል የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሃ መጮህ በመንፈሳዊው ዓለም መልስ ያስገኛል፣ ውጤትም አለው፡፡ በፖለቲካ አለም ግን ፍየል ወድያ ቅዝምዝም ወዲህ ከመሆን አያልፍም፡፡ ተቃዋሚዎች በምርጫ ታሪክ ቀላል የማይባል መራጭ ድምጽ እንደሰጣቸው አሌ ሊባል የማይችል እውነታ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ቢያንስ እንኳን በተመረጡ ሰሞን በሙስናና በአቅም ማነስ ተገምግመው የሚባረሩትንና በሕዝብ ተቀባይነት ያጡትን የገዢ ፖርቲ ተመራጮች ማሸነፍ እንዳቃታቸው ለማሳመን መሞከር፣ በሆድ ይፍጀው ብቻ ሊታለፍ የሚችል አይደለም፡፡ የሚቀሰቅሰውም ጥያቄ የቼኮዝሎቫኪያ ተወላጅና እንግሊዛዊ ጸሐፊ ተውኔት ቶም ስቶፓርድ “የዴሞክራሲ መለኪያው መመረጡ ላይ ሳይሆን ቆጠራ ላይ ነው፡፡” ያለውን ነው፡፡
ሕገ-መንግስታዊ መብቶቻችን እንዲከበሩና በተግባር እንዲውሉ ስንጮህ ኖረን ዛሬ ሰሚ ጆሮ በማግኝታችን ጥሪው የሚወደስ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ጅማሮው እንዳይደናቀፍ የዴሞክራሲ ጠላቶች ጆሮ ይደፈን በሚል መፈክር ሁሉን ዘግቶ ወደ እንቅስቃሴ መሸጋገር ግን የተሟላ መፍትሔ ነው ብዬ አላምንም፡፡ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ መላው ሕብረተሰብ በችግሮቻችንን መንስኤዎቻቸውንና መፍትሄዎቹ ላይ ዘለቅ ብለን፣ ከተቻለ በጋራ ካልሆነም የተገኘውን መገናኛ ብዙሃን ተጠቅመን መፈተሽ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ በችግሮቹ ላይ መግባባት ሳይፈጠር በመፍትሔዎቹ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ መጣር መፍትሔውን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ ከመሆን አያድነውም፡፡የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት አካባቢ ተከታታይ ሽንፈቱን ተከትሎ ጥርጣሬ፣ ስጋትና ፍርሃት የገባውን የደርግ ሽለላና ፉከራ አሸንፎ ኢህአዴግ ስልጣንን ከደርግ እጅ ሲረከብ የተገጠመ የማስታውሰው ስነ-ቃል አስታውሳለሁ፡፡
“ኢህአዴጎ ኢህአዴጎ፤
ገና ትበላለህ ወተትና እርጎ፡፡” መባሉን
“ኢህአዴጎ ኢህአዴጎ፤
ገና ትበላለህ ወተትና እርጎ፡፡” መባሉን
http://www.maledatimes.com/2012/10/02/%E1%89%B0%E1%8A%A9%E1%88%8B%E1%8B%8E%E1%89%BD%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8C%AB%E1%8C%A9%E1%89%B6%E1%89%B9%E1%8A%95-%E1%8A%A5%E1%8B%B5%E1%88%9C-%E1%88%88%E1%88%9B%E1%88%B5%E1%88%A8%E1%8B%98%E1%88%9D/
No comments:
Post a Comment