Translate

Saturday, October 6, 2012

አዲስ ድምጽ ራዲዮ ሲፈተን


ክንፉ አሰፋ
Addis Dimts Radioአንድ የሜዲያ ተቋም ስኬታማ ስለመሆኑ የሚመሰክረው የስራው ውጤት ብቻ ነው። በመገናኛ ብዙሃን ስራ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ስራቸውን የሚገመግሙት ከሚደርሳቸው በጎም ይሁን መጥፎ ምላሽ አንጻር ይሆናል።
ስለ ዋሽንግተን ዲሲው አዲስ ድምጽ ራዲዮና ስለ ዋና አዘጋጁ አበበ በለው ተግባራት እንዲሁም እንቅፋቶች በአንዲት ገጽ ለመመስከር ያስቸግራል። የስራው ውጤትም የሚገመገመው እኛ የሚድያው ደጋፊዎች በምንሰነዝረው ሙገሳ ሳይሆን – ከተቃራኒው ጎራ ከሚመጡት ምለሾች ነው።
አበበ በለው በሽብር ወንጀል ተከሶ ተፈርዶበታል። አበበ በዚህ ከወንጀሎች ሁሉ በከፋ ወንጀል መከሰሱ አዲስ ድምጽ ራዲዮ ‘ሙት ሜድያ’ እንዳልሆነ ይመሰክርልናል።

በአበበ ላይ የተከፈተው ሁለ-ገብ የስም ማጥፋት ዘመቻ በቅርቡ በሚንስቴር ደረጃ ደርሷል። ለዚያውም በፍትህ ሚኒስቴር። ይህ አዲስ ዘመቻ ከቀድሞው ከሽብር ውንጀላ የከፋ ባይሆንም፣ ደጋፊውን እንኳን ሳይቀር በማያሳምን መልኩ የተሰራ አሳፋሪ ድራማ ነው። የ’ሽብርትኛው’ ባለቤት በአዲስ አበባ ያሰራችው ቪላ ቤት እንደሚወረስ ነግረውናል። የአለማችን ቀንደኛው ሽብርተኛ – ኦሳማ ቢን ላደን እንኳን ሲታደንም ሆነ ሲገደል በቤተሰቦቹ ላይ የደረሰ ነገር አልነበረም። ወንጀል በውርስ! ፈረንጆቹ ድርጊቱን ማህበራዊ ጥፋተኝነት (guilt by association) ይሉታል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያው የፍትህ ስርዓት የት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያሳየናል። እውነታው ግን አበበ በለውም ሆነ ባለቤቱ በአዲስ አበባ ያሰሩት ቪላ ቤት የለም። ቢኖርማ ኖሮ ካድሬው የሰው ቤት ውስጥ ገብቶ አይደነፋም ነበር።
ድራማው ከተራ ካድሬዎችና ልማታዊ ጋዜጠኞች አልፎ በሚኒስቴር ደረጃ መድረሱ ግን ተመልካችን ከመናቅ፣ የሃገሪቱን የፍትህ ሂደት ደረጃ ከማሳየት ውጪ በአዲስ ድምጽ ላይ የሚያመጣው አንዳች ጉዳት የለም።  ከተመክሮ እንደምናየው እንዲህ አይነቱ ድርጊት ራዲዮውን ይበልጥ ተወዳጅ – አበበንም ጠንካራ ያደርገዋል እንጂ አያሸማቅቀውም። አዲስ ድምጽ ራዲዮ ‘ኢትዮጵያ አፍጋኒስታን ናት’፣ ‘ወደ ኢትዮጵያ አትሂዱ!’ ብሎ አንድም ግዜ ሲናገር አልተደመጠም።
በሜዲያ ስራ ሁሉንም ወገን ማስደሰት ወይንም ማስከፋት ፈጽሞ አይቻልም። የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት እና አስተሳሰብ ባለበት ህብረተሰብ መካከል ሁሉን ማስደሰት የሚቻለው ሁሉንም ወገን በማሳተፍ ሲቻል ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የተሳታፊዎችን ሁሉ መልካም ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። አዲስ ድምጽ ራዲዮ እንደአብዛኛው ነጻ ሜዲያ ወገንተኛ ነው የሚሉ ወገኖች ቢኖሩ አልተሳሳቱም።   ይህ ደግሞ ከሁሉም ወገኖች የሚጠየቅው ትብብር ባለመኖሩ የመጣ ችግር ነው። በራስ ካለመተማመን የተነሳ የተሳትፎ ጥሪን ሳይቀበሉ ይቀሩና – ይህ ሜዲያ ወገንተኛ ነው ብሎ መክሰሱ የተለመደ ነገር ሆኗል።  ከሁሉም ወገን የተሳትፎ ትብብር ሳይኖር እንደ ነጻ ጋዜጠኛ እንዴት ይቻላል?
አበበ በለው የጥበብ ሰው ነው።  ጥበብ ደግሞ ህብረተሰብን ከመቅረጽ አልፎ -  ትውልድን በበጎም ይሁን በክፉ የመቀየር ሃይል አለው።  ይህንን የጥበብ ተሰጥኦ ከጋዜጠኝነት ስራው ጋር በማዋሃድ አበበ የተሳካ ስራ ለመስራቱ ለአመታት ያከናወናቸው ስራዎቹ ራሳቸው ይመሰክራሉ። ብዙዎች ሲነሱ እና ሲወድቁ አዲስ ድምጽ ራዲዮ ግን ከነ መልካም ስራው እስካሁን አለ። አዲስ ድምጽ ጥንካሬው ችግርን ሁሉ ተቋቁሞ ለአመታት መዝለቁ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ መገናኛ ብዙሃን መመስረት አርአያ ለመሆን መብቃቱም ጭምር ነው።
ከዋሺንግተን እና አካባቢው ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ባሻገር በአለም ዙርያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሳምንታዊውን አዲስ ድምጽ ራዲዮ ለመስማት በጉጉት ነው የሚጠብቁት።
አበበ በለው ከአዲስ ድምጽ ራዲዮ ስራው ጎን ለጎን የፖለቲካውና ማህበራዊ ኑሮ ዙርያ ጉልህ እንቅስቃሴም ሲያደርግ ይታያል። በፖለቲካ እምነታቸውና ሃሳባቸውን በነጻ በመግለጻቸው የታሰሩ እንዲሁም የተሰደዱ ወገኖችን በገንዘብ እና በሞራል በመርዳት ግንባር ቀደም ሰው ነው።  የተቃውሞ ሰልፎችን በማስተባበር – በተለይ ደግሞ በሰሜን አሜሪካው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ከገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች እጅ እንዳይገባ በተጫወተው ትልቅ ሚና በሌላው ወገን የፕሮፓጋንዳ ኢላማ ለመሆን መብቃቱ አይደንቅም።
በእርግጥ የሜዲያ ስራ እጅግ ከባድ ነው። ከሙያው ፍላጎት፣  እውቀት እና ግዜ ባሻገር፤  ብዙ መውጣትና መውረድ፣ መወደስና መዋረድ፣ መሞገስና መሰደብ፣ .. ወዘተ የመሰሉ ተቃርኖዎችን የመሸከም ጫንቃ እና ጠንከር ያለ ቆዳ ይጠይቃል።  ይህንን ሁሉ መስፈርት አሟልቶ ስራውን ለመስራት የሚዘጋጅ ሰው ደግሞ ሌላ ጉልህ ችግር ጋር መጋፈጡ አይቀርም።  የፋይናንስ ችግር።  ሙያዊ እውቀቱም፣ ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ኖሮ ያለ በቂ ፋይናንስ ስራው ከቶውንም ሊታሰብ አይችልም።
እንግዲህ አበበ በለው በሙያው ምክንያት ይህንን ሁሉ ችግር በጫንቃው ተሸክሞ በሬዲዮ ላይ የሚያደርገው የጋዜጠኝነት ተግባር የሚያኮራ ነው። እኛ ደግሞ በርታ ከማለት ባሻገር ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ ይኖርብናል እላለሁ። ስለዚህ ከመስዋእትነት ሁሉ ትንሽዋን መስዋእት እንክፈል። አዲስ ድምጽን በገንዘብ እንርዳ!
– ክንፉ አሰፋ –

No comments:

Post a Comment