በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሙስሊም እምነት ተከታይ ወገኖቻችን በትናትናው ዕለት ዓርብ መስከረም 25 ቀን በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞአቸውን ለማሰማት በሰላማዊ መንገድ ወጥተው ከነርሱ ፈቃድ ውጪ የእምነቱን መሪዎች በየቀበለው ለማስመረጥ የሚደረገው ጥረት የከፋ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ለማስገንዘብ ለዘረኛውና አምባገነኑ ወያኔ አገዛዝ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ማሳየታቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢ አጠናክሮ ከላከልን ዜና ለመረዳት ተችሎአል።
በአገራችን ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ታላቅ ትንግርታዊ የተቃውሞ ሥነሥርዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው አንዋር መስጊድ ብቻ ቁጥሩ ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ተገኝቷል ተብሎአል። ቢጫ ካርድ የማሳየት ሥነሥርዓት የተካሄደው ከጅሙዓ ሶላት በኋላ ሲሆን በርካታ የተቃውሞ መፈክሮችም ሲደመጡ ውለዋል። የሙስሊሙ ህብረተሰብ ላለፉት 11 ወራት እያካሄደ ባለው የመብት ጥያቄ የዚህ አይነት የከረረ ተቃውሞ አሰምቶ እንደማያውቅ የዘገበው ዘጋቢያችን፤ በጊዜያዊነት የተመረጡ የመፍተሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በታሰሩበትና ከፍተኛ ወከባ በሙስሊሙ ላይ እየተፈጸመ ባለበት በአሁኑ ሰዓት ይህ በሃይል እንዲካሄድ የታሰበው ምርጫ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንዳበሳጨና ውስጥ ለውስጥ በተደረገ ግንኙነት አብዛኛው ተሳታፊ ቢጫ ጨርቅ ይዞ በመውጣት ተቃውሞው በተካሄደባቸው ከተሞች የሚገኙትን የአገዛዙን ሹሞችና ካድሬዎች አንገት ሲያስደፋ እንደዋለ ለማወቅ ተችሎአል። በዚህም የተነሳ አዲስ አበባችን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ይዞት በወጣው ቢጫ ካርድ ተጥለቅልቃ ውላለች።
ከአዲስ አበባ ወጪ ለወያኔ የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ የሰጡ ከተሞች ደሴ፣ ከሚሴ፣ ሻሸመኔ፣ አዳማ፣ ወልቂጤ፣ ጅማ፤ በደሌ እና ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደሆኑ የዘገበው ዘጋቢያችን የክርስቲያኑ ህብረተሰብ በሙስሊም ወንድሞቹ ድፍረትና ወኔ እጅግ ከመደሰት አልፎ “ ሙስሊም ወገኖቻችን አኩርተውናል “ እያለ መሆኑን ገልጾአል።
አዲስ አበባ ውስጥ በአንዋር መስግዲ የተደረገውን ተቃውሞ የተከታተለው የግንቦት 7 ዘጋቢ ያነጋገራቸው አቶ ሃምዛ ሸምሱ የሚባሉ የ75 ዓመት አዛውትና የ11 ልጆች አባት “እኔ በኢትዮጵያዊነቴና በሙስሊምነቴ እንደዛሬ የኮራሁበት ቀን የለም” በማለት ምክንያታቸውን ሲያስረዱ “ቢጫ ካርድ የምናውቀው በኳስ ሜዳ ነበር። እሱን በቴሌቪዥን እንጂ እኔ ኳስ ሜዳ ሄጄም አላውቅም። ዛሬ ግን እኔ የ70 ዓመቱ ሽማግሌ መንግሥትን ‘ተጠንቀቅ’ ለማለት አላህ አበቃኝ። አላሁ አክበር። ከእንግዲህ ኢህዴግ ለራሱ ሲል ይወቅ። እንቢ ካለ በላ ይወርድበታል። አላሁ አክበር” በማለት የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው አስተያየታቸውን ሰጥተውታል።
ወጣት መሃመድ ተማም ደግሞ “መንግሥት ድምፃችን ይስማ!!!! ጮኸን፣ ጮኸን ካልተሰማን የሚከተለውን መገመት እኮ ቀላል ነው። እኔ ለዲኔ ሕይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብላል።
ወይዘሮ ዘይነባ ከዲር ደግሞ “እኔ ቢጫ ካርድ ያወጣሁት በመጀመሪያ ደረጃ ለኢቲቪ ነው። በአላህ ይዘናችኋል ኢትቪዎች አትስደቡን!!! አትዋሹ!!! ሰለቸን” ብለዋል።
ሪፓርተራችን ያነጋገራቸው ሰዎች ሁሉ በደስታ ሲቃ ውስጥ ነበሩ። ብዙዎች “ይህ ታላቅ ቀን ነው፤ ይህ ታሪካዊ ቀን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የፓለቲካ ተንታኞች የዛሬው እለት ትዕይንት የሙስሊሙ ትግል የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃ ያመለክታል ይላሉ። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ “ከእንግዲህ የሙስሊሙን ትግል የሚገታው ኃይል አይኖርም። ሁላችንም ከዚህ ሃቅ ጋር መታረቅ አለብን። የሙስሊሙን ትግል መደገፍና በአገራችን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ አለብን” ብለዋል።
ዘረኛው አምባገነኑ ወያኔ ግን የሙስሊሙን ጥያቄ ወደ ጎን ገፍቶ በፊታችን እሁድ በሚያካሄደው የይስሙላ ምርጫ ካድሬዎቹን ሊሾም ተዘጋጅቷል። እሁድ አስመራጩም መራጩም ተመራጩም ወያኔ ብቻ የሆነበት ምርጫ ይካሄዳል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና የአፋር ክልላዊ መንግሥት የእሁዱ ምርጫ በመስኪጆች ውስጥ እንዲካሄድ ፈቀደ። ሆኖም ግን ኮሚቴዎቻችን፣ ኡለሞቻችን እና ዱአቶቻችን በእስር ላይ ሆነዉ ምርጫ የማይታሰብ ነዉ ብለዋል። በዓርብ ሶላት በኋላ ይኸው ተቃውሞአቸውን በከባድ ተክቢራ አሰምተዋል። በሀረር ከተማም በታላቁ ኢማን መስጂድ ህገ ወጡን ምርጫ በመቃወም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የከተማዎ ሙስሊሞች ከጁምአ ሰላት ቡሀላ ተቃዉሟቸዉን እንዳሰሙ የደረሰን ዜና ያረጋግጣል።
No comments:
Post a Comment