Abe Tokchaw
ከዚህ በፊት ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ 99.6% በሆነ ውጤት ምርጫውን “ሲያሸንፍ” ዳኛው ህዝብ ፍርድ ሰጥቷል። ያንን አክብሮ መንቀሳቀስ የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ብለው ተናግረው ነበር።
“ዳኛው ህዝብ የሚለውን አክብሮ መንቀሳቀስ የሁላችንም ሃላፊነት ነው” የምትለውን ቃል መንፈስ ቅዱስ ነው ያናገራቸው ብለን እናስብ እና እንቀጥል፤ አሁን “የመለስን ራዕይ ማሳካት ዋናው አላማዬ ነው” እያሉ የሚነግሩን ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ አጠቃላይ ኢህአዴግ አባላት እና አባታት እንዲሁም ልጆች እና ቀኝ እጆች… ዳኛውን ህዝብ መስማት እንዳለባቸው እመክራለሁ።
ዛሬ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለመንግስት ቢጫ ካርድ ሰጥተውት አይተናል። ይሄ ፍፁም የሰለጠነ ጨዋነት የተሞላበት ሰላማዊ ተቃውሞ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል።
መንግስት እና የመንግስት ዋና የስራ ሂደት ባለቤቶች የተቃወማቸውን በሙሉ “ጫካ ለምን አትገቡም!?” እያሉ ቢመክሩም እንዲህ ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞም እንዳለ ማሳየቱ በጣም ጥሩ ነው የሚሉ አስተያየቶች ከየቦታው እየተሰነዘሩ ነው።
ዳኛው ህዝብ ላለፉት በርካታ ወራት ለኢህአዴግ ፊሽካ ሲያሰማ ቆይቶ አልሰማ ቢልም ዛሬ ቢጫ ካርድ አሳይቶታል። ቀጣዩ ምን ይሆን አብረን የምናየው ይሆናል።
እኔ ኢህአዴግን ብሆን ግን ሰላማዊውን ጥያቄ በሰላማዊ መልኩ ቀልቤን ሰብሰብ አድርጌ እመልስ ነበር። “ውድ ባለስልጣኖቻችን ሆይ ቀለብ መሰብሰብ ብቻ ዋጋ የለውም መጨረሻችሁ ያምር ዘንድ ቀልባችሁን ሰብሰብ አድርጉ!” ብንላቸውስ…!?
No comments:
Post a Comment