ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ከዚህ በፊት ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ የሴራ ምርጫ አዘጋጅቶ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ትግል ውስጥ ውሃ ሊቸልስ ተዘጋጅቷል።
እንደ እቅዱ ከሆነ አገዛዙ በሚቆጣጠረው የሴራ ምርጫ አማካይነት ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የካድሬ መሪዎች ሊመረጥ ነው። ምርጫውን ተከትለው ስለሚመጡ ነገሮችም መገመት ከባድ አይደለም። እንደተለመደው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ ስለ ምርጫው ህጋዊነትና ፍትሃዊነት ተግተው ይደሰኩራሉ። ቀጥሎም አዲሱ አመራር በቀድሞው መጅሊስ የተጀመሩትን ወያኔያዊ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ ተግባራት ለማስቀጠል ቃል ገብቶ ሥራውን ይጀምራል። በአዲሱ የመጅሊስ አመራር ከለላ ወያኔ በሙስሊሙ ላይ የሚያደርሰውን አፈና፣ እስርና እንግልት አጠናክሮ ይቀጥላል።
የሴራ ምርጫዎች የአምባገነኖች መሣሪያዎች ናቸው። መስከረም 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ሊደረግ የታቀደው የሙስሊም አመራሮች ምርጫም ከዚህ ቀደም በወያኔ አስፈፃሚነት ሲደረጉ እንደነበሩ ምርጫዎች ሁሉ የሴራ ምርጫ ነው፤ ዓላማውም አምባገነንነትን ማጽናት ነው። ለምርጫው እየተደረጉ ያሉት ዝግጅቶችም የሚያመለክቱት ይህንኑ ሃቅ ነው።
- ወያኔ ካድሬዎቹን በምርጫ አስፈፃሚነት መድቧል፤
- የምርጫው ታዛቢዎችም የወያኔ ካድሬዎች ናቸው፤
- ለቁጥጥር እንዲያመችም ምርጫው የሚካሄደው በቀበሌዎች ነው፤
- ሙስሊሙ ባይወድም በግድ እንዲመርጥ እየተገደደ ነው።
በዚህ ሁኔታ የሚፈፀም ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
ብዙሃኑ የሙስሊም ማኅበረሰብ ይህንን የሴራ ምርጫ በመቃወም ድምጹን ያሰማ ቢሆንም ሰሚ አላገኘም። ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ ተቃውሞዓቸውን ቢገልጹም ወያኔ በቀበሌም በእድርም እያስገደደ ጥቂት ካርዶችን በትኗል። የቀረው ቀኑ ሲደርስ ቁጥሮችን በፎርም ሞልቶ ሊሾማቸው የሚፈልጋቸውን ሰዎች “ተመረጡ” ብሎ ማሳወቅ ነው።
የወያኔን የሴራ ምርጫ ተውኔት ኢትዮጵያዊያን በተደጋጋሚ የተመለከትነው በመሆኑ ሰልችቶናል። ወያኔ ሥልጣንን በጉልበቱ ከያዘ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሴራ ምርጫዎችን አይተናል። በመጠኑም ቢሆን ከሌሎቹ የተሻለ የነበረው የ1997ቱ ምርጫም እንደምን ባለ አሳዛኝ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ሁላችንም የምናውቀው ነው።
በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እምነት ወያኔ በሥልጣን ላይ እያለ እና እሱ እየተቀጣጠረው የሚደረግ ምርጫ እውነተኛ የሕዝብ ፍላጎት የሚገለጽበት ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ሊሆን አይችልም። በወያኔ አስተባባሪነትና አስፈፃሚነት የሚደረጉ ምርጫዎች ሁሉ የሴራ ምርጫዎች ናቸው። የሴራ ምርጫዎች ዓላማ ለአንባገንነት ሽፋን መስጠት ነው።
እውነኛ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲኖር ሕዝብ ሃሳቡን በነፃ የሚገልጽበት ሥርዓት መገንባት ይኖርበታል፤ እንዲሁም ምርጫውን የማስፈፀም ብቃት ያላቸው ገለልተኛ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል። ነፃነትና ገለልተኛ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ የሚደረግ ማናቸው ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ሊሆን አይችልም። ስለሆነም መስከረም 27 ቀን 2005 ዓም በቀበሌዎች የሚደረገው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መሪዎች ምርጫ ተቀባይነት የለውም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በምርጫ ስም በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ የሚጫንበትን አገዛዝ በጽኑ ይቃወማል። የእምነት ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ የተከበሩባት እና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትኖረን የወያኔን የሴራ ምርጫዎችን ማክሸፍ ይኖርብናል ብሎ ያምናል። ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሚያደርጉትን የመብት ማስከበር ትግል ይደግፋል፤ የክርስትያኑ ማኅበረሰብም በዚህ የመብት ጥያቄ ከሙስሊም ወንድሞቹና እህቶቹ ጎን እንዲቆም ጥሪ ያደርጋል።
የግንቦት 7 ዓላማ ወያኔን በማስገደድ ወይም በማስወገድ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ የተከበረበት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሚገኝበት፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረበት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረበት ሃገር እንዲኖረው ማድረግ ነው።
ለዚህ ክቡር ዓላማ የሃይማኖት ድንበር ሳይከልለን ሁላችንም በአንድነት እንነሳ!!!
No comments:
Post a Comment