የሳኡዲ ዜግነት ያላቸው ባለሀበት፤ ሼክ አላሙዲን ትልልቅ የሊሙ ቡና መሬቶችን፤ የሕዝብ ንብረቶችን ወደግል ይዞታ ከሚያዛውረው የፕራይቬታይዜሽን ባለስልጣን በጨረታ አሸንፈው መውሰዳቸው ታወቀ።
የባለስልጣኑ ቃላ አቀባይ፤ አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ እንደገለጹት፤ በቀድሞዋ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፤ በኦህዴዷ ወ/ሮ አስቴር ማሞ የሚመራው የባለስልጣኑ ቦርድ፤ የስድስቱን ለም የቡና እርሻዎች ጨረታ አሸናፊነት ብቸኛውን ዋጋ ላቀረበው የአቶ አላሙዲን ኩባንያ ሰጥቷል።
ለተወሰኑት እርሻዎች ሌሎች ተጫራቾችም ዋጋ መስጠታቸው የታወቀ ሲሆን፣ የአላሙዲን ኩባንያ 1.184 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር በማቅረብ 6ቱንም የቡና እርሻዎችና፤ የለሙ ቡና እርሻዎች ዋና ጽ/ቤትን ወስዷቸዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የሼክ አላሙዲን ኩባንያዎች፤ የኢትዮጵያ እብነ በረድ ፋብሪካ፣ የጎጀብ እርሻን፣ የላይኛው አዋሽ የግብርና ኢንዱስትሪንና የአቦቦ እርሻን በ1.3 ቢሊዮን ብር መውሰዳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አቶ አላሙዲን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ጊዜ ጀምሮ የለገደምቢ ወርቅ ማዕድንን ጨምሮ አያሌ የሕዝብ የንግድ ድርጅቶችን ያለ ጠንካራ ተፎካካሪ ማሸነፋቸው ይታወቃል።
አቶ አላሙዲ የለገደንቢ ወርቅ ማዕድንን በ1989ዓ.ም. በ172 ሚሊዮን ዶላር ለ10 አመት መግዛታቸው የሚታወቅ ሲሆን የወርቅ ማዕድን ማምረቻም በ10 ዓመት ብቻ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማምረቱንና፤ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ንጹህ ትርፍ ማትረፉን በአስረኛ ዓመት ሪፖርት መጥቀሱ ይታወሳል።
ጎማ አንድ፣ ጎማ ሁለት፤ ጨለለቂ፤ ጉመር፤ ሱንቱ እና ሶቃ የተሰኙ 6 የለሙ ቡና መሬቶችንና፤ የለሙ ቡና እርሻዎች ዋና ጽቤቱን በ1.184 ቢሊዮን ብር የገዙት አቶ አላሙዲ፤ የዋጋውን 35 ከመቶ ወይም 414ሚሊዮን ብሩን በቅድሚያ፤ የተቀረውን 65 ከምቶ ወይንም 769 ሚሊዮን ብር ደግሞ በ5 ዓመት እንደሚከፍሉ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ንብረትነቱ የአቶ አላሙዲን የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለሚያስገነባው የአፍሪካ ህብረት አምስት ኮከብ ሆቴል ማሰሪያ 850 ሚሊዮን ብር መፍቀዱ የሚታወስ ሲሆን፤ የባንኩ ቦርድ ብድሩን ለጊዜው እንዳገደው ኢትዮጵያን ሪፖርተርስ ባለፈው ዘግቧል።
አቶ አላሙዲን ወደኢትዮጵያ ብዙ ካፒታል ይዘው እንደገቡ ቢነገርም፤ ከኢትዮጵያ ባንኮች በብዛት መበደራቸውና ለመበደሪያነት የሚያስይዟቸው መያዢያዎችም በብድር የሚያሰሯቸው ድርጅቶች መሆኑ ብዙ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
No comments:
Post a Comment