Translate

Thursday, October 4, 2012

በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ካሚል ሸምሱ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትንና የኡላማዎች ምክርቤትን ከሰሱ


ኢሳት ዜና:-”መንግስት የአህባሽ አስተምህሮን ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያቁም፣ የሀይማኖት መሪዎቻችንን በነጻነት እንምረጥ፣ መሪዎቻችን ይፈቱ” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው ተቃውሞአቸውን ካለፈው  አመት ጀምሮ በማሰማት ላይ ያሉት የኢትዮጵያውን ሙስሊሞች ተወካይ የሆኑትና በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ካሚል ሸምሱ ሲራጅ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትንና የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤትን በጠበቃቸው አማካኝነት ከሰዋል።
ከሳሹ ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ልደታ ምድብ ችሎት ባቀረቡት የእግድ አቤቱታ ላይ ያቀረቡት ክስ በመጪው እሁድ ሊደረግ የታቀደውን የመጅሊስ ምርጫ የተመለከተ ነው። አቶ ከሚል በክስ ማመልካቻቸው ላይ ” መስከረም 27 ቀን 2005 ዓም ቀነ ቀጠሮ በመቁረጥ በመገናኛ ብዙሀን እያስተላለፉ ከመሆኑም በላይ አስመራጭ ኮሚቴ መምረጣቸውም በእለቱ ምርጫውን እንደሚፈጽሙ አቋም መያዛቸውን ” እንደሚያሳይ ገልጠዋል።
አቶ ካሚል ምርጫው እንዳለ ቢቀጥል በከሳሾችና በወከላቸው ህዝብ እንዲሁም በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ላይ ሊተካና ሊካስ የማይችል ጉዳት እንደሚያስከትል አቶ ከሚል ሸምሱ በክስ ቻርጁ ላይ አመልክተዋል።

በፍርድ ቤት የቀረበው ክርክር የመጨረሻ እልባት እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በተከሳሾች በኩል ሊደረግ የታቀደው ምርጫ እንዳይካሄድ ታግዶ እንዲቆይ እንዲታዘዝላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
በርካታ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በመጪው እሁድ በገዢው ፓርቲ አቀነባባሪነት የሚደረገውን ምርጫ ለመቃወም በነገው እለት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሀን እየገለጡ ነው።
በተመሳሳይ ዜናም ባለፈው ቅዳሜ በመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና በመንግስት በሚደገፈው የመጂሊስ አባላት መካከል በግዮን ሆቴል በተደረገ ስብሰባ፦<የሙስሊሞችን ተቃውሞ እንዴት አድርገን እንግታው?>በሚል አጀንዳ ሰፊ ውይይት መደረጉን፤ በስብሰባው የተገኙ የ ኢሳት ምንጮች ጠቁመዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፦”የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችን በተዋረድ ያሉ ካድሬዎች በሙስሊሞች ጉዳይ በመጠመዳቸው የልማት ሥራዎች ቆመዋል>ብለው ሲናገሩ፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተወካይ የሆኑት ግለሰብ፦<ግዴለም እስከ ሰኞ ብቻ ታገሱን፤ከሰኞ በሁዋላ ወደ ልማታችን እንገባለን> በማለት በዛቻ መልክ አስተያዬት ሰጥተዋል።
ሆኖም እስከ ሰኞ ምን እርምጃ ለመውሰድ እንደታሰበ የብሔራዊ መረጃና ደህንነቱ ተወካይ በግልጽ አላብራሩም።
የስብሰባው ተሳታፊዎች የሆኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሀላፊዎች በተለየ መልኩ፦< የመጂሊሱ ምርጫ ቢራዘም፤ መጂሊስንና መንግስትን እየተቃወሙ ያሉትን ከጀርባቸው ማን እንዳለ ለማወቅ እንችላለን> የሚል ጥያቄ አስከመሰንዘር መድረሳቸውም ተሰምቷል።
ይሁንና መንግስት አካሂደዋለሁ ባለው ምርጫ ለመመረጥ የቋመጡ የቀድሞው መጂሊስ አባላት፦<በፍጹም!ምርጫው መራዘም የለበትም! እየተደበደብንም ቢሆን ምርጫውን እናካሂዳለን!> በማለት ከመስተዳድሩ ሀላፊዎች የቀረበውን ሀሳብ አጠንክረው ተቃውመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገሪቱ ባሉ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  ስብሰባዎች እያካሄደ ነው::
መንግስት በየዩኒቨርሲቲዎቹ እያካሄደ ባለው ስብሰባ በርካታ ሃሳቦች ተነስተው ውይይት እና ማብራሪያ እየተካሄደባቸው ሲሆን፤ ለውይይት ከቀረቡት አጀንዳዎች መሀከል ዋነኛው የአክራሪነት ጽንሰ ሀሳብ የሚለው ነው።
በተለይ < የሀይማኖት አክራሪነት በኢትዮጵያ እና ስጋቱ >በሚል ርዕስ በቀረበ የመወያያ ጽሁፍ  ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ክርክር  ተደርጓል።
የሀይማኖት አክራሪነት ሀሳብ በቅጡ እንዲብራራ ተደጋጋሚ ጥያቄ ከተሰብሳቢዎቹ  የቀረበ ሲሆን፤< የሀይማኖት አክራሪነት ምንድነው ? በኢትዮጵያ የሀይማኖት አክራሪነት አለ ወይ?  በሚሉት ጭብጦች ዙሪያ ሰፊ ክርክሮች ተደርገዋል።
ስብሰባዎቹን የሚመሩት የመንግስት ተወካዮች< በኢትዮጵያ የሀይማኖት አክራሪነት አለ >ብለው ሲከራከራሉ፤  በርካታ ተሰብሳቢዎች ግን ፦< አክራሪነት በኢትዮጵያ እናንተ በምትሉት መልኩ የለም ፤ሃሳቡን አላግባብ እና ያለ አውድ ተርጉማችሁታል ብለው ተከራከረዋል::
መንግስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራንን ለማወያየት የነበረውን እቅድ መሰረዙን መግለጻችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment