Translate

Sunday, September 2, 2012

አቶ መለስና የዴሞክራሲ ተቋማት


ኢ/ር ዘለቀ ረዲ
ኢ/ር ዘለቀ ረዲ
 አቶ መለስ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጻር ከመሰረቷቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡አቶ መለስ ዜናዊ በወጣትነታቸው ጊዜ በሀገራችን የዲሞክራሲ ያለመኖርና የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ ያለው ሂደት ስላልተመቻቸው እነዚህ ተቋማት ይጎለብቱ ዘንድ ትግላቸውን እንደጀመሩ ይታወቃል፡፡ በዚህም የአምባገኑን የደርግ መንግስት ከ17 ዓመታት ትግል በኋላ ከድርጅታቸው  ጋር በመሆን እንደገረሰሱ ስልጣን በመያዝ ስራቸውን ህገ መንግስት እንዲፀድቅ በማድረግ ጀመሩ፡፡ አቶ መለስ በዚህ ረገድ በርካታ ስራዎችን የመስራት ዕቅድ ይዘው ቢንቀሳቀሱም የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታን በተመለከተ ግን የሰሩት ስራ ያለፈውን መንግስት ከወቀሱበትና ከታገሉበት አንጻር ሲታይ ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር›› አይነት ነው የሆነባቸው፡፡

1. የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፡- ይህ ተቋም ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በተለይም ለመድበለ ፓርቲ ሥርአት ወሳኝ ተቋም ነው፡፡ እንደ ህዝብ ተቋምነቱ መመረጥ የነበረበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር፡፡ ምክንያቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚወከሉት በህዝብ ስለሆነ እነዚህን ተቋሞች በሚያደራጀው የጋራ ኮሚሽን ነበር፡፡  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወከላቸው የምርጫ ቦርድም ህዝብ ወከላቸው ማለት ነው፡፡  ነገር ግን ጠ/ሚንስትሩ የምርጫ ቦርዱን አባላት ለእሳቸውና ለድርጅታቸው ታዛዥና ታማኝ ግለሰቦችን መልምለው ለማሳመን ያህል ብቻ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያፀድቃሉ፡፡ የሚመርጡት ራሳቸው ሆነው ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ በዚህም ማንም የመረጠውን የማገልገል ግዴታ ስላለበት የሀገራችን የምርጫ ቦርድ ማንን እያገለገለ እንደሆነ ማስረዳቱ ጉንጭ እንደማልፋት ነው፡፡  የምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለፓርላማው አለመሆኑና በፓርላማው መሾም መሻር አለመቻላቸው በራሱ በኢትዮጵያ የነጻ ምርጫ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡  ኢህአዴግ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት (vertical hierarchical ) ማዕከላዊነትን የጠበቀ ነው፡፡ ይህ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ማእከላዊነት የጠበቀ የእዝ አስተዳደር ወደ ምርጫ ቦርድ አምጥተው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ከመገንባት አንጻር ብቻ ሳይሆን የመንግስትና የህዝብ አገልግሎት እንዳይለይ አድርጎ የተዘበራረቀ አሰራርን ያበረታታል፡፡  CSIS  (CENTER FOR STRATEGIC AND INTERNATIONAL STUDIES ) የተባለ የአሜሪካን ቲንክ ታንክ ግሩፕ ገዥው ድርጅት በመንግስት ገንዘብ በተለይም የምርጫ ቅስቀሳዎች ማድረግ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡ ይህንንም የመንግስት አሰራር ምርጫ ቦርድ መቃወም ሲገባው ገለልተኛ እንዲሆን አድርገው ባለመመስረታቸው የህዝብ ወገንተኝነትን ከማሳየት ይልቅ ዝምታን እንዲመርጥ አድርጎታል፡፡
2. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፡- ይህ ተቋም በተለይ በእጅጉ ነጻ ሆኖ በራሱ መቋቋም ሲገባው በመንግስት በኩል ተቋቁሞ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ ይገርማል፡፡ በዓለም ነባራዊ ሁኔታ ሰብአዊ መብት የሚጣሰው በአብዛኛው በመንግስት አካላት መሆኑ እየታወቀ መንግስት ይህን ተቋም ማቋቋሙ ለራሱ በዳይ ለራሱ ከሳሽ እንዲሆን ሲያደርገው በሰብአዊ መብት ጥሰቱ በኩል ከፍተኛ የሆነ በደል እየተፈፀመ በቁርጠኝነት ይህንን መቃወም እንዳይችል ጥርስ የሌለው አንበሳ አድርጎታል ሲል ከላይ የጠቀስኩት የአሜሪካን ቲንክ ታንክ ግሩፕ በjune 2011  ባወጣው ሪፖርት ነቅፎታል፡፡ ከዚህ አንጻር የቀድሞው ኢሰመጉ ያሁኑ ሰመጉ በራሱ ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሳይኖረው ስለተቋቋመ መንግስት የሚሰራውን ስህተት ነቅሶ ከመረጃ ጋር ሪፖርት በማውጣት ብዙ ስራ የሰራ ቢሆንም ጠ/ሚ/ር መለስ እንደ ሌሎች ሲቪክ ማህበራት ሁሉ ሌላ በማቋቋም ስሙን ከመቀማት ጀምሮ ሥራን በአግባቡ እንዳይሰራ አድርገውታል፡፡ ለተነሱለት ዓላማ ቆመው ቢሆን ኖሮ በነጻ የተቋቋመውን ድርጅት ከማጠናከር ይልቅ ሌላ ተመሳሳይ ድርጅት ማቋቋም ባስፈለገ ነበር፡፡ በዚህ አንጻርም ጠ/ሚ/ር መለስ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ተከራካሪ ድርጅት አኳያ የሰሩት ስራ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡
3. ፀረ – ሙስና ኮሚሽን ፡- ይህ ተቋም በመንግስት ባለስልጣናት የሚሰሩ የሙስና ተግባሮችን እያጋለጠ የሚከስ ድርጅት ነው፡፡ ይህን ድርጅት የአሜሪካን ቲንክ ታንክ ግሩፕ CSIS (CENTER FOR STRATEGIC AND INTERNATIONAL STUDIES ) በjune 2011  ባወጣው ሪፖርት  ነቅፎታል፡፡ በተጨማሪም ይህ የጥናት ድርጅት በሙስናው ዙሪያ መንግስት በፖለቲካው ዙሪያ እስካልመጡበት ድረስ ባለስልጣናት ለሚሰሩት ሙስና ብዙም ደንታ የለውም ሲል በሪፖርቱ ለመውቀስ ሞክሯል፡፡ እውነትም ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለተነሱለት ዓላማ በቁርጠኝነት ቆመው ቢሆን ኖሮ ይህ ድርጅት በፓርላማው ተሰይሞ ተጠሪነቱ ለፓርላማው መሆን በተገባው ነበር፡፡  ይህ ከሆነ በዴሞክራሲያዊ ግንባታው ላይ እንቅፋት እንደሚሆንና አሁን ባለው ሁኔታ ለራሱ አነስተኛና ጥቃቅን ሙሰኞችን ከመክሰስ ባሻገር ቱባ ባለስልጣናት በሙስና ዙሪያ ለመክሰስ እየተቸገረ ያለበት ሁኔታ እንዳለ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
4. የሲቪክ ማህበራት ፡- ጠ/ሚር መለስ ዜናዊ በተለይ ውጤታማ ያልሆኑበትና በዴሞክራሲው ግንባታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረው የሲቪክ ማህበራት አመሰራረት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ራሳቸውን ችለው የተመሰረቱትን የሚቀናቀኑ ማህበራትን በመፍጠር በራሳቸው ጸንተው እንዳይቆሙ አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ ግን በራሳቸው አገዛዝ ዘመን ተመሳሳይ ማህበራት ተቋቁመው ሌሎቹን እንዲቀናቀኑ የተደረገበት ሁኔታ አንዱ ነበር፡፡ በዚህም በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት ማህበራት እንዲፈጠሩ በማድረግ ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ እርስ በርስ በመካሰስና በመጋጨት ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ በሚደረገው ጉዞ ላይ ትልቅ እንቅፋት መፍጠራቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ትልቁ ምሳሌ ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዴሞክሲያዊ ተቋማት አንጻር የሰሩትን ስራ የሚመለከት ሲሆን ከእሳቸው ሞት ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ እሳቸው የጀመሩትን ልማት እንደሚያስቀጥል እየወተወተ ይገኛል፡፡ ይህ የኢህአዴግ ድርጅት ፕሮፖጋንዳ ከጠቅላይ ሚ/ሩ ሞት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ገበያ ውስጥ የገባ አስመስሎታል፡፡ እኔ ግን እንደ አንድ ግለሰብ አሁን ኢህአዴግ ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳለ  ይሰማኛል፡፡ በዚህም ውሳኔው የኢህአዴግና ኢህአዴጋውያን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ለድርጅት ሳይሆን ለሐገር በማሰብ ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ኢህአዴጋውን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ለድርጅት ሳይሆን ለሐገር በማሰብ ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በመወያየት መሪው ከምርጫ 2002 ማግስት በመስቀል አደባባይ እንደተናገሩት ቃላቸውን ሊጠብቅላቸው ይገባል፡፡ ‹‹ተቃዋሚዎች ቢመረጡም ባይመረጡም በሐገራቸው ጉዳይ እንዲወስኑ እናደርጋቸዋለን፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የገቡትን ቃል ተከታዮቻቸው በመፈፀም ሀገሪቱን ለመታደግና ወደ ልማትና ዴሞክራሲ የመምራት ኃላፊነት በኢህአዴጋውን እጅ ነው፡፡  በአጠቃላይ በአንድም ይሁን በሌላ ከወጣትነታቸው ጀምረው ያለ እረፍት በመስራት ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን የጠ/ሚ/ር መለስን ነፍስ ይማር እላለሁ፡፡ 

No comments:

Post a Comment