የዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ሞት ተከትሎ “በአገሪቱ ውስጥ የሥልጣን ክፍተት ተፈጥሯል፤ ለዚህ ሁኔታ ዝግጅት ያደረጉ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሉም” የሚሉ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው።
በሕዝቧ ሙሉ ፍላጎትና ተሳትፎ የምትመሠረተዉን ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ በአሁኑ ሰዓት ግንቦት 7 በመተግበር ላይ ያለውን የስትራቴጂያዊ ሰነድ በከፊልም ቢሆን ይፋ ማድረግ እና ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ያለው ድርጅት መኖሩ ማሳየት በሕዝብ ውስጥ ያለውን ስጋት ይቀንሳል፤ ሕዝብንም ለትግል ያነሳሳል ብለን በማመናችን የስትራቴጂ ሰነዳችንን በአጭሩ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስትራቴጂያዊ ግቦች ሁለት ናቸው። እነዚህም
ግብ 1: ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ የሕዝብ ምርጫ ብቻ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበት ሥርዓት ማስጀመር
ግብ 2: ሰላማዊ፣ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ ሂደት ብልጭ ብሎ እንደገና በአምባገነንነት ግርሻ መልሶ እንዳይጠፋ ጠንካራ መሠረት ያለው የዲሞክራሲ ተቋማትንና ባህልን መገንባት
ይህ ስትራቴጂያዊ ሰነድ፣ ግብ 1 እውን እንዲሆን አራት መለስተኛ ግቦች መሳካት አለባቸው ይላል። እነዚህም:
መ ግ 1. ወያኔንና ግብረ አበሮቹን ከላይ በግብ 1 ለተቀመጠው የመንግሥት ሥልጣን አያያዝ ተገዢ እንዲሆኑ ማስገደድ ካልሆነም ከሥልጣን ማስወገድ
መ ግ 2. ለፍትህና ዲሞክራሲ ከቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመርህ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ትብብር መፍጠርና በጋራ መታገል
መ ግ 3. መላዉን የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ እና በሕዝብ አመኔታ ያገኘ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም፤ እና ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ወቅትን በትብብር መምራት
መ ግ 4. ነፃ፣ ፍትሃዊና ሁሉን ዓቀፍ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድና ሥልጣንን ለተመራጭ ማስረከብ
ከስትራቴጂያዊ ሰነዱ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ግብ 1 ተፈጸመ የሚባለው ወያኔ ተወግዶ፤ ኅብረት ተፈጥሮ፤ የሽግግር ወቅት ታልፎ፤ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የተመረጠ አካል የመንግሥት ሥልጣን ሲረከብ ነው።
ወያኔን የማስገደዱ አልያም የማስወገዱ መለስተኛ ግብ 1 እንዲሳካ መተግበር የሚገባቸው ስልቶች በሰነዱ ውስጥ በዝርዝር ተብራርተዋል፤ ተግባራዊ እየተደረጉም ነው።
ግንቦት 7 የሽግግሩ ወቅት ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር አጥንቶ የተነሳ ንቅናቄ ነው። ይህም በመለስተኛ ግብ 3 ውስጥ ተመልክቷል። ሰነዱ ተግባራዊ ሥራዎችን በምን ያህል ጥልቀት እንደመረመረ ለማሳየትም ጭምር በሽግግሩ ጊዜ ውስጥ መከወን ስለሚኖርባቸው ተግባራት የሚዘረዝራቸውን ከዚህ በታች ለአብነት እናቀርባለን።
ስ 1. በመንግሥት ለውጥ ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ችግሮች በቅድሚያ ማጤንና መፍትሄዎችን ማዘጋጀት
ስ 2. ብቃትና ጥራት ያለው መላውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያካትተ ጊዜያዊ ም/ቤት መመሥረት
ስ 3. የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ብቃት ያለው ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት መመሥረት
ስ 4. የሽግግር መንግሥቱ የሚመራበትን መንግሥታዊ መዋቅር መንደፍና መዘርጋት
ስ 5. በሃገሪቱ የፖለቲካና ማኅበራዊ ችግሮች ላይ ሰፊ ውይይትና ምክክር በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲደረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ቋሚ መፍትሄ መፈለግ
ስ 6. በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የሚገኙ የተመዘበሩ የሕዝብ ንብረቶችን ማስመለስ
ስ 7. በኅብረተሰቡ ውስጥ የሰላምና እርቅ ተግባሮች እንዲካሄዱ ማድረግ
ስ 8. በሃገርና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል የፈጸሙ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ለፍርድ ማቅረብ
ስ 9. የሃገሪቱን ደህንነት የሚፈታተኑ ውሎችን መመርመርና ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት
ስ 10. አዲስ ዲሞክራሲያዊ ህገ መንግሥት ማርቀቅ፤ ለሕዝብ ውይይት ማቅረብ፤ ማሻሻልና ለሕዝበ ውሳኔ ማቅረብ
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በጥንቃቄ የተዘጋጀና የተሟላ ስትራቴጂያዊ እቅድ ነድፎ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆኑ በጨረፍታ ቀንጭበን ካቀረብነው መረጃ መረዳት ይቻላል።
ይህንን ስትራቴጂያችንና እቅዳችንን በትክክል በሥራ ላይ ካዋልን አንዳንዶች ይደርሳል ብለው የሚፈሩትን የፓለቲካ ቀውስም ሆነ የአመራር ክፍተት ሳይደርስ አገራችን ኢትዮጵያን እጅግ በጣም ወደ ተሻለ አመራር የማሸጋገር እድል አለን። ኢትዮጵያችንን ፍትህና እኩልነት የሰፈኑባት፤ የሃይማኖቶችና የማኅበረሰቦች ነፃነት የተከበረባት እና ልማት የተፋጠነባት አገር ማድረግ እንችላለን። ለዚህ ግን ሁላችንም በጋራ በመነሳት መታገል ይኖርብናል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ብሩህዋን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን ስትራቴጂ ነድፎ እየታገለ ነው። ድርጅታዊ ብቃቱንም በየእለቱ እያጎለበተ ነው። ትግሉ በመርህ ላይ በተመሠረተ የድርጅቶች ኅብረት መመራት አለበት ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment