ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሳዑዲ ኤምባሲ ምንጮች አንዳንድ ሁኔታዎችን ለማጣራት ለተወሰኑ ቀናት ቪዛ መስጠት ከማቆም ውጪ እገዳ አልነበረም ሲሉ መንግስታቸው ጥሎአል የተባለውን እገዳ አስተባብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ እስልምና ም/ቤት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን እገዳው ለተወሰኑ ቀናት ተጥሎ ከቆየ በኃላ በጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃ ገብቶ በተደረገ ውይይት ቪዛ የመስጠቱ ሥራ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ እስልምና ም/ቤት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን እገዳው ለተወሰኑ ቀናት ተጥሎ ከቆየ በኃላ በጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃ ገብቶ በተደረገ ውይይት ቪዛ የመስጠቱ ሥራ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ጉዞው የታገደበት ምክንያት በግልጽ የተነገረ ባይሆንም የሳዑዲ መንግስት የኢትዮጵያን ጉዞ በሚያስተባብረው መጅሊሱ ላይ እምነት በማጣቱ ነው ተብሎአል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቀኑ ባለው የበረራ ፕሮግራም ጉዞው እየተከናወነ መሆኑን የኤምባሲው ምንጮች ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመንግስት የሚደገፈው የእስልምና ምክር ቤት ( መጅሊስ) መሰከረም 27 ቀን በየቀበሌው ለሚካሄደው ምርጫ ታዛቢዎችንና የምርጫ አስፈጻሚዎችን ትናንት አስመርጧል።
የዜና ዘጋቢያችን ያናገራቸው የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት እንደገለጹት ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ መንግሥት በተጠናከረ ሁኔታ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ወደ ወረዳ እየሄዱ የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ ቢጠይቅም ፣ ፈቃደኛ የሆኑ ሙስሊሞች በመጥፋታቸው ባለፈው እሁድ የእድር ዳኞችን አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠሩ ትዕዛዝ አስተላልፎ የመጡትን ሙስሊም እናቶችንና አባቶችን በቤተሰቦቻቸው ቁጥር ካርድ ይዘው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የሃይማኖት ነፃነት የጠየቁ ሙስሊሞች በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በታሰሩበት ወቅት የመጅሊስ ምርጫ በኢህአዴግ ቀበሌ አናደርግም ያሉት ዘጋቢያችን ያናገራቸው የሃይማኖት አባቶች፣ የኢህአዴግ መንግሥት እንደ ልማዱ ካርዱን ራሱ በካድሬዎቹ ወደ ኮሮጆ ከቶ የፈለገውን ሰው ያስቀምጥበታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላለፈው አንድ ዓመት በተጠናከረ ሁኔታ ዘወትር ዓርብ በመስኪዶች በመሰብሰብ ከስግደት በኋላ መጅሊስ አይወክለንም፣ መንግሥት የአህባሽን ዶክትሪን በግድ አይጫንብን እና የሃይማኖት መሪዎቻችንን እኛው በነፃነት እንምረጥ በማለት የሚያደርጉት የነፃነት የመብት ጥያቄ ተካሮ የሙስሊሙ መሪዎች ለእስር ተዳርገዋል።
በ1997 ዓም ምርጫ የሙስሊሙ ጠበቃ ነኝ በማለት ክርስቲያኑን እና ሙስሊሙን ለመከፋፋል ሙከራ አድርጎ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት፣ አሁን ደግሞ ሙስሊሙን ከሁለት በመክፈል እርስ በርስ ለማጋጨት እየሰራ ነው በማለት የሀይማኖት አባቶች ተናግረዋል።
መንግስት የሀይማኖት ነጻነትን አከብራለሁ ካለ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የፈለጋቸውን መሪዎች በነጻነት እንዲመርጥ እድሉ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት የሀይማኖት አባቶች፣ መንግስት ራሱ የሚፈልጋቸውን ሰዎች ለማስመረጥ ላይ ታች ሲል መታየቱ፣ አገዛዙ ለሀይማኖት መብቶች ቆሜያለሁ በማለት እስከ ዛሬ ሲያቀርበው የነበረው ፕሮፓጋንዳ ባዶ መሆኑን የሚያመለክት ነው በማለት ያክላሉ።
የሙስሊሙ ማህበረሰብ መስከረም 27 የሚደረገውን ምርጫ ለመቃወም በመጪው አርብ የጁማ ጸሎት ላይ ተገኝቶ ተቃውሞን እንዲያሰማ መልእክቶች በፌስ ቡክ እና በሌሎችም የመገናኛ ብዙሀን እየቀረቡ ነው።
የታሰሩት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በመጪው ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል።
No comments:
Post a Comment