Translate

Tuesday, October 2, 2012

ጎ… ሽ መለስን መለስን መሰሉኝ!


አቤ ቶኪቻው

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ሳምንት ሆናቸው መሰለኝ። ይሁናቸው ገና ድርጅታቸው ከፈቀደ ሃያ አንድ አመት ይሆናቸው የለ…!? ዋናው የእርሳቸው ፀባይ ማሳመር ነው።ጎ… ሽ መለስን መለስን መሰሉኝ!
የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ  ከትላንት በፊት ለአሜሪካ ድምፅ ራድዮ ድርጅት የሰጡትን ቃለ ምልልስ አዳምጬ ነበር። እኔ የምለው አቶ መለስ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም እንዲህ ይመሳሰሉ ኖሯል እንዴ!? የቃላት አጠቃቀማቸው ራሱ ከሟቹ ጋር አንድ አይደል እንዴ…!? ግራ ገባን እኮ የሞተው ማነው…?
አቶ ሃይለማሪያም ደጋግመው እንደነገሩን የመለስን ራዕይ ለማስቀጠል የመጡ አንዳች አካል እንጂ ራሳቸውን የቻሉ ግለሰብ አይደሉም። እኛ “የለም እርሶማ የለውጥ ሃዋርያ ኖት” ብንላቸውም ነጠላ ሰረዝ “የለም እርሶማ የገንፎ ምንቸት ኖት” ብንላቸውም ነጠላ ሰረዝ “የለም እርስዎማ ኃይለማርያም ኖት” ብንላቸውም ድርብ ሰረዝ እርሳቸው ግን “እኔ መለስ ነኝ” እያሉን ነው። አሁን ትምህርተ ስላቅ ትምጣ¡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ “እነ እስክንድር ነጋን ባለ ሁለት ቆብ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሁለት ቆብ ማጥለቅ አይቻልም” ብለዋል። “ቀዩን መስመር ማለፍ ክልክል ነው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። “ብሎግ እና ዌብ ሳይት ዕገዳውም እንደሚቀጥል…” አርድተውናል፤ እርሳቸው መለስ እንጂ ኃይለማሪያም እንዳልሆኑ እያረጋገጡልን ነው።
እኛ  “ጎ…ሽ  መለስን መለስን መሰሉኝ!” ብለን ስናደንቅ ተስፋ ጥለውባቸው የነበሩ ሰዎች ደግሞ “እስከዚህም ፊት” በሚባል ደረጃ ዝቅ አድርገዋቸዋል።
በመጨረሻም፤
ጋሽ ደበበ ሰይፉ ጠብቋት፣ ጠብቋት፣ ጠብቋት ለቀረችው ልጅ የፃፋት ግጥም እንደሚከተለው ትነበባለች!
ጠብቄሽ ነበረ
መንፈሴን አጽድቼ
ገላዩን አጥርቼ
አበባ አሳብቤ
አዱኛ ሰብስቤ
ጠብቄሽ ነበረ
ብትቀሪ ጊዜ
መንፈሴን አሳደፍኩ
ገላዩን አጎደፍኩ
አበባው ደረቀ
አዱኛው አለቀ
ብትቀሪ ጊዜ የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞ ጠፋ
ደበበ ሠይፉ (1962)

No comments:

Post a Comment