Translate

Tuesday, September 4, 2012

በቁማቸው ከገደሉት በሞታቸው የገደሉት

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ


የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሞት በብዙዎች ጉንጭ ለሁለት ወር ሲጉላላ ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግስት ከተረጋገጠ ይኸው ሁለት ሳምንት ሊሆነው ጥቂት ቀናት ቀሩት፡፡ መንግስት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት እስከዕለተ ቀብራቸው በማወጁ ባንዲራም ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ነው፣ መገናኛ ብዙሐንም ሙሉ ትኩረታቸውን በዚያው በሐዘኑ ጉዳይ ላይ እንዳደረጉ ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የጡረተኛ ሚኒስትሮችን ጥቅማጥቅም የሚዘረዝረው የ2001 አዋጅ ላይ [አንቀጽ 11/1/ለ] ብሔራዊ የሐዘን ቀን አንድ ቀን እንደሆነ ይደነገጋል፡፡)

ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን ሐዘን የማክረር ባሕላችን የተጋነነ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሠልስት ሳይቀር እየተሰረዘ የሦስቱ ቀን ሐዘን ወደሁለት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በነገራችን ላይ የሐዘን ቀናት ወደሦስት ቀናት ዝቅ እንዲሉ የተደረገው በአፄ ምኒልክ አዋጅ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ነበር፡፡ እንግዲህ በሰሞኑ፣ ሁለት ሳምንታት የዘለቀ የሐዘን ግዜ መቶ ዓመት ያህል ወደኋላ ተመልሰናል ማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር የሞተበት አገር ሕዝብ ማዘኑ አስገራሚ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በውዴታም ይሁን በግዴታ ይህንን ያህል ቀናት ማዘኑ ወይም እንዲያዝን ማድረጉ ብዙ ጥያቄዎችን ያጭራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምናውራውም ከዚህ ፈር ከለቀቀ የሐዘን ግዜ በስተጀርባ ስላሉ ጉዳዮች ነው፡፡

አንድ፤ ችግር ይኖር ይሆን?

አገሪቱ አሁን እየተመራች ያለችው በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ነው ቢባልም፣ ያንን የሚያስመሰክር ነገር አላየንም፡፡ የመንግስት ልሳን የሆኑት እነ አዲስ ዘመን ሳይቀሩ ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር›› እያሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ከዚያም በላይ አሳሳቢው ግን በቶሎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ማዕረግ በፓርላማ ምርጫ እንዲቀበሉ አለመደረጉ አጠያያቂ ነው፡፡ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በታወቀ በሦስተኛው ቀን ተመርጠው፣ ቃለመሓላ እንደሚፈጽሙ ቃል ተገብቶልን የነበረ ቢሆንም፣ መጀመሪያ ‹‹በአቡነ ጳውሎስ ቀብር›› በኋላም ደግሞ ‹‹የፓርላማ አባላት ሐዘናቸውን ይወጡ›› በሚሉ የማያሳምኑ ምክንያቶች ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ ይሄ ቁርጥ ያለ ቀን ለማስቀመጥ ያለመወሰን ጉዳይ አሁንም በአቶ ኃይለማርያም ተተኪነት ላይ በግንባሩ ውስጥ (ከምስጢር ወዳድነቱ አንፃር) ስምምነቶች አለመኖራቸውን የሚያጠራጥር ነው፡፡

እንደሚታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም በስንት ውትወታ ያመነው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ ሕመሙን አቃልሎ ነበር የተናገረው፡፡ በሌላ በኩል በተለይ በማሕበራዊ አውታሮች ውስጥ የተናፈሱት ወሬዎች ደግሞ ‹‹የሚተኩት ሰው ላይ እስኪስማሙ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞተዋል›› የሚል አንድምታ ነበራቸው፡፡ የዚያን ግዜውን ወሬ ውሸትነት የሚያረጋግጥ ነገር እስካልተገኘ የአሁኑንም በሐዘን የተሸፈነ የጊዜ ክፍተት በጥርጣሬ መመልከቱ ምንም ሊያስገርም አይገባም፡፡ ስለዚህ የመንግስት አካላት ጉዳዩ የሕዝብ መሆኑን በማወቅ ግልጽነት እና ኃላፊነት የተሞላበት አሠራር እንዲከተሉ እመክራለሁ፡፡

ሁለት፤ መተኪያ የላቸውም?

የመለስን ሞት ተከትሎ አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ አብዛኛው የቴሌቪዥን አስተያየት ሰጪ ‹‹እርሳቸውን መተካት አይቻልም›› ለማለት መድፈራቸው ለአገራችን ትልቅ ቅሌት ነው፡፡ ለዚያ ነው የ80 ሚሊዮኖች አገር ‹ከአንድ ሰው ሌላ ብቃት ያለው ዜጋ የላትም› የሚለውን መርዶ ስላሰማን የመለስ ሞት እርሳቸው በሕይወት እያሉ ካደረሱብን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁለ በላይ ገደለን ለማለት የደፈርኩት፡፡ ይሄ አባባል፣ ኢትዮጵያ ከመለስ እጅግ የተሻሉ እልፍ ሰዎች አላት ብለን የምናምነውን ዜጎች ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን የኢሕአዴግ አባላት እና ደጋፊዎችንም ጭምር የሚሳደብ ነው፡፡

የኢሕአዴግ አባላት ‹አንድ መለስን መተኪያ የለንም› ብለው የሚሉ ከሆነ ስልጣኑን ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ማስረከብ ወይም በጥምረት ለመሥራት መወሰን አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እራሳቸው እንደነገሩን እና ‹‹መለስ የጀመሩትን ልማት እናስቀጥላለን›› መፈክር ውስጥ ውስጡን እንደምንረዳው ሁሉ ነገር እርሳቸው ነበሩና ሌሎቹ በሙሉ በእርሳቸው ሽፋን የነበሩ ናቸው ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ከሕዝቡ መካከል የወጡ እና በእኔ አመለካከት ኢሕአዴግን እና ፕሮፓጋንዳውን በቅጡ ያልተረዱ ሰዎችም ይህንኑ ‹መለስ መተኪያ የላቸውም› የተሰኘ ነጠላ ዜማ እያስተጋቡ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች በመለስ 21 ዓመት የዘለቀ የስልጣን ዘመን ምን ዓይነት ስርዓት እንደተፈጠረ ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የቱንም ያህል የሚከበር ታላቅ ሰው ቢሞት ይታዘንለት እንደሆን እንጂ፣ መተኪያ የለውም ምን ይውጠናል የሚል ስጋት አይፈጠርም፡፡

የመለስን ሞት ተከትሎ የተስተዋለው ነገር የአምባገነን ስርዓት ፍሬዎችን ያሳያል፡፡ በአምባገነን ስርዓቶች ውስጥ የማኅበረሰቡ አባላት ከአምባገነኑ መሪ በቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው ተደርገው ይቀረፃሉ፡፡ እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከስልጣን ይውረዱ ሲባል በፓርቲ ውስጥ ስብሰባ እዬዬ ሲባል የተከረመው ለዚያ ነው፡፡

አቶ መለስ በየትኛውም የምርጫ ክርክሮች ወቅት ከተቃዋሚዎች ጋር ፊትለፊት እንዲገጥሙ ተደርጎ አያውቅም፣ ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ጋዜጠኛ ጋር በፖለቲካ ጉዳይ የብቻ ለብቻ የቃለ ምልልስ እንዲሰጡ ተደርጎ አያውቅም፤ ገፅታ ለመገንባት በሚያስችሉ መድረኮች ላይ ብቻ እንዲገኙ እና በጥንቃቄ የተመረጡ ንግግሮችን ብቻ እንዲያደርጉ ሲመቻችላቸው ከመክረሙ አንፃር የማኅበረሰቡ አካላት ላይ ‹ከሳቸው ሌላ የለን ይሆን?› የሚል ውዥንብር መፍጠሩ አያስገርምም፤ የሚያስገርመው ሊተኳቸው ዕጩ ሆነው የቀረቡት ግለሰብም ይህንኑ ማስተጋባታቸው ነው፡፡

ሦስት፤ ሐዘን ወይስ …?

የመለስን አስተዳደር ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በየሳምንቱ በሚታተሙ ጥቂት ጋዜጦች እና በየአምስት ዓመቱ (ለይስሙላ) በሚካሄደው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር እያሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡ በመሰረቱ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን እንጂ በጠበበ ምህዳር እንዳይፈናፈኑ መታሰራቸውን፣ ጋዜጠኞች በጻፉት ነገር መከሰስና መታሰራቸውን፣ ምርጫዎች ከጊዜ ወደጊዜ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ብቻ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ሳይጠቅሱ ያልፋሉ፡፡ እነዚህ ቁምነገሮች ደግሞ የስርዓቱን ዋነኛ ባሕርያት ገላጭ ናቸው፡፡

የመለስ አስተዳደር ‹‹ሕገመንግስታዊ አምባገነን (constitutional dictatorship)›› የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ይህ የአምባገነን ዓይነት መሪዎች ለአደጋ ጊዜ እንዲጠቀሙበት በሕገመንግስቱ ላይ የሚሰጣቸው ስልጣንን ተጠቅመው ለጭቆና ሲያውሉት የሚፈጠር ነው፡፡ የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ‹‹ታላቁ ድብታ (Great Depression)›› በመባል በሚታወቀው የኢኮኖሚ ውድቀት እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አገራቸውን ከውድቀት ለማዳን ይህንን ስልጣናቸውን በመጠቀም ኮንግረሱን ሳያማክሩ እርምጃዎች ወስደዋል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ ግን ምንም ዓይነት ተጨባጭ ችግሮች ባልተመዘገቡበት ጊዜ ፓርላማውን ሳያማክሩ ሶማልያ ገብተዋል፣ ምርጫ 97 የተካሄደ ዕለት የሰራዊቱን ተጠሪነት ወደራሳቸው አዙረዋል፣ የፌዴራል ከተማዋ አዲስ አበባን እና የደቡብ ክልልን ምክርቤቶች በትነዋል፡፡ ከዚያም በላይ ጨቋኝና ከሕገመንግስቱጋ የሚጋጩ አዋጆችን አውጥተው የተፎካካሪዎቻቸውን አቅም አዳክመዋል፣ የተፎካካሪዎቻቸውን ደጋፊዎች ወኔና ተስፋ ቀምተዋል፡፡

እናም ይህንን ሁሉ በውጤታማነት ካከናወኑ በኋላ የሞታቸው ዜና ሲሰማ (በእርግጥ ከብዙሐኑ አንፃር ሲታዩ ብዙ ናቸው ለማለት ቢቸግርም) ለቁጥር የሚያታክቱ ሰዎች አስከሬናቸውን ለመቀበል መውጣታቸው፣ ቤተመንግስት ድረስ ለቅሶ ለመድረስ መሰለፋቸው እና አሁንም በመጪው የቀብራቸው ስርዓት ላይ መገኘታቸው የሚሰጠው ትርጉም አለ፡፡ አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ቢጨቁኑት ምህረት የማይቸግረው መሆኑ፣ ሁለተኛ፤ በአስተዳደራቸው የተፈጠረው የፍራቻ ድባብ አሁንም ለእርሳቸው አላዘንክም በሚል ቅጣት ያስከትልብኛል ብሎ በመፍራቱ፣ ሦስተኛ አጋጣሚውን በመጠቀም ቤተመንግስቱን ለመጎብኘት ወይም የገቢ ምንጭ ለመፍጠር (ፎቶ፣ ፖስተር እና ቲሸርት ሽያጮችን ልብ ይሏል) ነው፡፡

አራት፤ ኪሳራው በማን ነው?

መለስ መሞታቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሐን ከታወጀ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚም በሐዘን እንዲቆዝም የተፈረደበት ይመስላል፡፡ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በሥራ ሰዓት ሐዘን ነው በሚል እንዲሰበሰቡ ይታዘዛሉ፣ በክልሎች የለቅሶ ስነስርዓቶች ይዘጋጁ እና ሰዎች እንዲገኙ ሲባል መሥሪያ ቤቶችም እየተዘጉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በቁመታቸው ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸው ‹ቢልቦርዶች› እየታተሙ ይለጠፋሉ (በአራዳ ሕንፃ ቁመት የተዘረጋውን ልብ ይሏል)፡፡ ሌላው ቀርቶ መስቀል አደባባይ የተተከለውን ድንኳን ለመገንባት የተንቀሳቀሰው ክሬን እና የወጣበት ወጪ አመታዊ በጀቷን በብድር ከምትሞላ አገር የሚጠበቅ አይደለም፡፡

የአሁኖቹ መሪዎች ሕዝቡ ያሳየውን ሰብአዊ ርህራሔ እና ሐዘን እንዳያቆም ይፈልጉ እንጂ ሕዝቦች ሐዘኑ ይቀጥል እስካላሉ ድረስ ለብክነቱ ተጠያቂ መሆን አይችሉም፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ዜጎች ከአፋቸው እየነጠሉ የሚከፍሉት ታክስ ለፖስተር ማሳተሚያ፣ ለመፈክር እና ለፕሮፓጋንዳ ብሎም የፓርቲ አባሎችና የደጋፊዎች ሊግ አባላት እና ሌሎችንም ማመላለሻ ትራንስፖርት ፍጆታ መዋሉ የመንግስትን ማን አለብኝነት (ተጠያቂነት ማጣት) ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

መንግስት በዚህ ግዜ የሚያስፈልገው፣ ይህችን አጋጣሚ ተጠቅሞ እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት እና መፍጨርጨር የነበረ ቢሆንም፣ ‹እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ› የሆነውን ኢኮኖሚያችንን በአልባሌ ብክነት ማባከኑ ጉዟችንን እያደር እንቦጭ ያሰኘዋልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በመጨረሻም
በዓለማችን ለአንድ ሰው ቀብር ብዙ ሰው አደባባይ በማስወጣት ግብጾችን የሚፎካከራቸው የለም፡፡ 5 ሚሊየን የሚገመቱ ግብጻውያን እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 1970 ለፕሬዘንዳንታቸው ጋሜል አብደል ናስር ቀብር አደባባይ ወጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም እሁድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለአቶ መለስ ቀብር እንዲወጡ ይፈልጋሉ፡፡ እርግጥ ለቀብሩ ሊወጡ የሚችሉት የግብጻውያኑን ያክል ባይሆኑም ብዙ እንደሚሆኑ መገመት ከባድ አይደለም፡፡

ነገር ግን ይህ የጎሳ ልዩነት ተደረገብኝ፣ የኢኮኖሚ በደል ደረሰብኝ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ደረሰብኝ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተነፈግኩ ሳይል ሐዘኔታውን በክብር እየገለፀ ያለ ሕዝብ ብዙ የሚገባው መሆኑን መዘንጋት ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በሐዘን ሰበብ ከድንኳኑ ጀርባ ሌላ ደባ የሚሰራበት ዓይነት ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህ ሕዝብ የስርዓት ለውጥ እንጂ የንጉሥ ለውጥ ምንም አይፈይድለትም፡፡

---
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ቢሆንም፣ ጋዜጣው እንዳይታተም በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት በመታገዱ እዚህ አስፍሬዋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment