Translate

Thursday, September 6, 2012

አቶ መለስ እልፈት ስንብት


ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም
ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ
ከ275 ሳምንታት በላይ አንድም ሳምንት ሳላቋርጥ ረጃጂሞችና አስረጂዎች የሆኑ አስተያየቶች በመልካምና ጎጂ ጎኑም ጭምር በኢትዮጵያ ላይ ቁንጮ ባለስልጣን በነበረውና ሁለት 10ት ዓመታት ባሳለፈው ሰው ላይ ጽፌያለሁ፡፡መለስ ዜናዊ አልፏል፡፡ የሞቱ መንስኤ ግን በመንግሥት ጥብቅ ሚስጥርነቱ እንደተቆለፈ ነው ያለው፡፡
መለስ ስለፈጸመውና ስላመለጠው ጉዳይ በሕይወት ዘመኑ እያለ በብቃት ያነሳሁት ስለሆነ አሁን ከህልፈቱ በኋላ ብዙም የምለው የለኝም፡፡ ሕልፈተ ሞቱ ያሳዝነኛል፤ ምክንያቱም፤ ጆን ዶን እንዳለው ‹‹የማንም ሰው ሞት ያሳንሰኛል፤ ምክንያቱም እኔም ቁጥሬ ከሰብአዊያን ጋር ነውና ፡፡ሞት ለሁላችንም በእኩል መንገድ መጪ ነው፡፡ሲመጣም ሁላችንንም በእኩል ደረጃ ያስቀምጠናል፡፡›› እንደ ሃቀኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤የለየለት ፈላጭ ቆራጭ ባለ ስልጣን ቢሞትም ያሳዝነኛል ምክንያቱም በሰብአዊ መብት ጉዳይ፤በፍትሕ ሚዛናዊነት ላይ፤በእኩልነት ላይእና በመሳሰሉት  ላይ ሲጓደሉ ለሙግት በመሰለፌ ነው፡፡
መለስን የምሰናበተው በሃዘን ወይም በክስ ሳይሆን ይልቅስ ያመለጠን እድል በማሰብና የወደፊት ተስፋን በመመኘት ነው፡፡ የወደፊት ኢትዮጵያን ህልውና ግንባር ቀደም በማድረግ ነው፡፡

መለስ ዜናዊ ዕድል ዕጣ ያወጣችለት ሰው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ዕጣ ፈንታ ታሪካዊ ሚና እንዲጫወት መርጦት ነበር፡፡ለ17 ዓመታት ሃገራችንንና ሕዝቦቿን ለግፍና ለመከራ ለስቃይ ዳርጎት የነበረውን ወታደራዊ አገዛዝ ታግሎ ያሸነፈው ጎራ አባል ነበር፡፡ መለስ በድሉ ወቅት ዴሞክራሲን በሃገሪቱ ለማክበርና ልማትን ለመዘርጋት፤ቃል ገበቶ የነበረ ቢሆንም፤ ዓመታት ተቆጥረው ባለፉ ቁጥር የተገባው ቃል መፍረስም እንዲሁ እያለፈና እየተካደ ሄደ፡፡መለስ በዚህ ወቅት ከመልካም ምግባርና ቃል ከማከበር ባህል ጋር ጨርሶ በመለያየት፤የባሰ ጨቋኝ፤ የከፋ ፈላጭ ቆራጭ፤ የለየለት ከፋፋይ፤ ጭርሱን ሃሳብ ላለመቀበልና እኔን ብቻ ስሙኝ የኔን ብቻ ተቀበሉ ማለትን አብሮ ካስወጣው ጨቋኝ አገዛዝ የባሰ የለየለት ደክታተር ሆነ፡፡ በመጨሻው የግዛት ዘመኑ ሃገሪቱን ወደ ፖሊሳዊ አስተዳደር በመለወጥ በሰላዮች የታጠረ መንግስት ፈጥሮ ዘመናዊ  የዋጋው ጣሪያ መጠን ባጣ የቴክኒዮሎጂ ውጤት በመጠቀም፤ሕዝቡን ረገጦ የሃገሪቱን ሃብት አሟጦ በባዶ ካዝና መግዛቱን ቀጠለ፡፡ የፕሬስን ነጣነት አፈነ:: የሲቪል ሶሳዬቲውን ላይፈታ ከረቸመ፤ተቃዋሚዎችን በመላው ተስፋ በማስቆረጥና የትግል ሜዳውን በማጥበብ ብሎም በመዝጋት ሰነከለ፡፡ ፍርሃትና ጥላቻ በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲነግስና መተማመን እንዲጠፋ መረቡን ዘረጋ፡፡ ይህ ደግሞ በከተማዎች ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ ክልሎች በመላው ነበር፡፡ በ1991 ከጫካ ሲመጣ ይዞት የመጣውን የውጊያ ሳንጃውን ወደ አፎቱ ሳይመልስ መለስ መፈራትንና መጠላትን በአንድነት ተላበሰ፡፡ መለስ በተቅናቃኞቹንና ነቃፊዎቹ ያልተወደደና ተቀባይነት የሌለው ሰው ነበር::  ከአጃቢዎቹና በጥቅም ገዝቶ ከሚያሽከረክራቸው ዘንድ ግን መለስ እንደዓምላክ፤ቅዱስ ቅዱስ የሚባል፤ አመራሩ እንከን የለሽ የሆነ፤ የግድያ አፈናና እስራት ትዕዛዙ የተባረከ ነው በማለት ያገዝፉት ነበር፡፡ በመጨረሻውም የግዛት ዘመኑ፤ መለስ በፍጹም አምባገነን ስልጣን የሚገዛ በመሆን በስልጣኑ አለአግባብ የሚጠቀም ጀብደኛ ሆኖ ነበር፡፡ይህንኑ ስልጣኑን ይበልጥ ለማጠንከር ሲዳክር፤ ተወዳዳሪ የሌለው በሌሎችም ሀገራት እንደምሳሌ በመጠቀስ አርአያ ሊሆን የሚችልበት ዕድሉ ጋር ተላለፉ፡፡
ባለፉት 21 ዓመታት ተስፋ ከተጣለበት ዴሞክራሲያዊ አስተዳዳሪ ሊሆን ከመቻል ይልቅ፤ወደለየለት ፈላጭ ቆራጭ ዲክታተርነት የተገለበጠው መለስ ዜናዊ ማን ነበር? በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የምንከሰውና የምንወቅሰው፤ወንጀለኛው የሰው ልጅ ጠላት የሚባለው ማነው?  ሲኤን ኤን በቅርቡ እንደገለጸው ባህሪው በሃገራችን የዴሞክራሲን መወለድ ያጨነገፈውና ‹‹ለአፍሪካዊ ፖሊስ ስረአት አገዛዝ›› ተጠያቂ የሆነው ግለሰብ ማነው? ያንን የምስኪኖች ሃገር ለድህነት ሕዝቡን ለስደትና ለመከራ ተጠያቂ ሆኖ የሚነሳውስ እሱ ብቻውን ነውን? ምናልባትም ይህን ጥያቄ እንዴትና በምን ሰበብ ይህ እስከ መለስ ሕልፈት ድረስ ሲሞግተውና ስህተቱን ነቅሶ እያወጣ ያሳየን ሰው አሁን ከሞተ በኋላ ያነሳዋል እንዴት ነው   ሊባል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ዕውነቱ መነገር ስላለበት ነው፡፡
ላለፉት 21 ዓመታት እኛው ነን መለስን ጉልበት የሰጠነው፡፡ እኛ ፈሪዎች ሆነን ነው እሱን ያጀገነው፡፡የሱ የክፋቱም ሆነ የዘረኝነቱ አበራቾች እኛው ነበርን፡፡ እኛው ነን ለመለስ በርሃባችን፤ በችጋራችን፤ ሰበብ ሆነን በሚሊዮን የሚቆጠረውን ዶላር እንዲያጋብስ ያደረገንውና ብክነቱን ወንጀሉን ኢሰብአዊነቱን እየመዘገብንና እያስመዘገብን፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን በማስረጃ እያስደገፍን በማቅረብም በየዓመቱ መሳርያዎቹ ነበርን:: እኛ ስል እኛ የመለስ ፓርቲ አባላትና ተባባሪዎች ነን::  የፍትሕ መድረኩን የአዞ ፍርድ ቤት እንዲያደርገውና፤ እንዲያስር እንዲፈታ ከዚያም አልፎ 99.6 በመቶ ድል ገጠመኝ ሲል ሆ ብለን አጨብጭበን ማሕተማችንን በመርገጫ አርጥበን ይሁንታውን የሰጠነው፡፡ እኛው ነን በፖሊስነት በስለላው መረብ በማገልገል፤ በጦሩ ውስጥ በመሰለፍ ንጹሃን ዜጎችን እንዲረሸኑ ምላጭ የሳብን፤ እኛው ነን፡፡ እኛው ምሁራኑ አይደለንም እንዴ  መለስን ብቻውን እንዲሆንበትና እንዳሻው በመሰለው ሲያዝበት ምን አገባን ብለንና ጎመን በጤናን መርጠን ልክ አይደለም ማለትን የፈራነውና ለአላማ መቆምን ችላ ያልነው? በብሩሁ የዴሞክራሲ ጎዳና ለመጓዝ የተጀመረውን የተስፋ መንገድ እኛው ተቃዋሚቆች አይደለንም እንዴ እርስ በርስ በመጣላትና ከሃገርና ከሕዝብ እራሳችንን እና የራሳችን ከፍ ከፍ በማስቀደም በሚሊዮን የሚቆጠረው ደጋፊያችን እንድንመራው ሃላፊነት ሲጥልብን ሸብረክ ብለን ከንቱ ያደረግነው፡፡ እኛ በዲያስፖራው ያለን አይደለንም እንዴ ዝምታን መርጠን ሃለፊነት የጥቂት ብለን የግብር ይውጣ አድርገነው ጩኸቱን አንዳንሰማ ጆሯችንን ደፍነን እንዳንናገርበት አፋችንን ሸብበን፤ ጥቂቱ ሲጮሁና ሲደክሙ ብዙዎችችን ገለል ብለን የሕዝቡን ሞትና ስቃይ ያገለልነው፡፡ እኛ ግለሰቦቹስ አይደለንም እንዴ መለስ እንዳሻው ሲፈነጭ ተው ለማለት ብርታቱንና ፈፍቃደኝነቱን አጥተን ሃገርን ለድህነት ሕዝብን ለችጋር ያጋፈጥነው፡፡ ማንኛችንም ከሃጢአቱ ንጹህ ነን ብለን እጃችንን ማጠብ አይቻለንም፡፡መለስ አውቆ ሲሳሳት ለመናገር ሳንፈልግ ከችሮታው ለመቋደስ መርጠን ላለፉት 21 ዓመታት ዝም ያልነውም በምንም መንገድ ከተጠያቂነት መቼም ይሁን መቼ ልናመልጥ ከቶ አይቻለንም፡፡ ስለዚህም ለተፈጠረውና ለተከናወነው ሁሉ ጣታችንን ወደ መለስ ስንቀስር ሶስታ ጣቶቻችን ወደራሳችን ማመልከታቸውን ልንዘነጋው አይገባንም፡፡
መለስ እጅጉን ሲበዛ እራስ ወዳድ የሆነ የሥላጣን ጥመኛ ነበር:: ያውም የሥልጣንን አንድ ጎን ብቻ ያወቀ፡፡ከእውነት ጋር ጨርሶ ያልተግባባ በመሆኑ እውነተኛ ሃቅ ከሕዝብ ፍቃድ የሚገኝና ሕግንም በተከተለ መንገድ ብቻ የስልጣንን ትግበራ ማካሄድ እንደሚቻል ጨርሶ አላወቀም ነበር፡፡ የመኖርና ያለመኖርን ሃይል በጁ የያዘ  ሆኖ አጠቃቀሙ ላይ ግን ባለመኖር ላይ እንዲያደላ ያደረገ፡፡ ፖሊሱም፤ ዳኛውም፤ከሳሹም፤ አቃቤውም ፍትሁም፤ ፍርዱም፤ ሰቃዩም፤ ሁለመናው እራሱ መለስ ብቻ ነበር፡፡መለስ ባለሙሉ ስልጣንነቱ የማይደፈር የማይገረሰስ ዘልአለማዊ እንደሆነ አድርጎ አሳምኖ አጃጅሎት ነበር፡፡ከዕድል ጋር የነበረውን ታላቅ ቀጠሮ ሳተው፡፡
ባይልለት ነው እንጂ መለስ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሪ ሊሆን ይችል ነበር፡፡በታሪክ ያወቅናቸው በርካታዎቹ ዲክታተሮች ታላላቅ መሪዎች ነበሩ፡፡ ታላቅነታቸው የተገኘው በሕዝቦቻቸው ላይ ባሳደሩት ተጽእኖና ክፋት ነው፡፡እንከን የሌላቸው መሪዎች ታላቅነትን የሚያገኙት ሕዝብ ይወዳቸዋልና ነው፡፡ የታላቅነታቸው ምንጭ በልባቸው ግልጽነትና ርህራሄ ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ተወዳዳሪ የሌላቸው እንከን የማይገኝባቸው የተትረፈረፈ የሕዝብ ፍቅር ያላቸው ተወዳጅ  መሪ ናቸው፡፡ ዛሬ ማንዴላ የሰብአዊነት አርማ ሆነው ይታያሉ፡፡ማንዴላን ለዚህ ያበቃቸው  ስብእናቸው፤ የንግግር ችሎታቸው፤የአስተዳደር ብስለታቸውና አመራራቸውም ሳይሆን እሳቤያቸውን ጭንቃቸው የሌት ቀን ጥረታቸው ስለ ሕዝቦች በመሆኑና ስለ ስልጣን አለመጨነቃቸው ነው፡፡ ማንዴላ አንዲት ዘለላ የፍቅር ዘር ከልባቸው አውጥተው የዘር ጥላቻና መለያየት ቂም በቀልን ሊያጠፋ በሚችል መልካም ምግባርና ፈቃደኛነት፤መቻቻልና ትዕግስት ላይ በመትከላቸው ነው፡፡ዓለም በደቡብ አፍሪካ በሚፈሰው የጥቁርና ነጭ ሰዎች ደም መፍሰስ ሲዳላና ሲተርት ማንዴላ ጥቁርና ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን አንድ ላይ በማሰባሰብ፤በእርቀሰላም ጠበል በማጥመቅ አንድነታቸውን መሰረቱላቸው፡፡ ሠላም ብለው ሁሉንም ለሠላም አሰለፉ፡፡ጥላቻን ከስሩ ነቅለው ጣሉና አስጣሉ::
መለስ ከዕድል ጋር ቀጠሮ ነበረው፡፡በማንዴላ ጫማ ውስጥ ሆኖ የእግራቸውን ፈለግ በመከተል ታሪክ ሰርቶ ታሪከኛም ሊሆን ይችል ነበር፡፡ጠንካራና አንድ ግንባር የፈጠሩ ኢትዮጵያንን ማጠናከርና ዕውነት የነበረውን መልሶ ማረጋገጥና የፈረሰውን መገንባት በቻለ ነበር፡፡በብሔር ተራርቀው እንዲተያዩ ያደረጋቸውን መልሶ ለማገኛኘትና ለማዋሃድ ድልድዩን የመስራት አቅም ነበረው፡፡እሱ ግን የዜጎችን መለያየትና በጎሪጥ መተያየታቸውን መረጠ፡፡ይህ ተጋጊጦና ቀለም ተቀባብቶ የተሰራው መንገድ ደግሞ ለሕብረት ሳይሆን በተለያየ እርባና ቢስ ጎዳና የሚያስኬድ ሆነ፡፡ የሚገነባው ድልድይ ሁሉ ድጥ የሞላበት፤ ግድቡም ገደብ የመኮገተው ሆነና ለውጪ ሰዎች የሃገርን መሬት ቆራርሶ መቸርቸርን አስከተለ፡፡ይህም በልማት ስም በቅንጥብጣቢ ሳንቲሞች አሳልፎ የተሰጠና የጠፋ ጠፍ መሬት ሆነ፡፡ መለስ ከዕድል ጋር ኢትዮጵያን በአንድነት ለመገንባት የነበረውን ቀጠሮ አመለጠው፡፡
መለስ ከዕድል ጋር ቀጠሮውን ቢያከብር ኖሮ ምሳሌ ሊሆን የሚገባ መሪ ብቻ ሳይሆን፤በሥራውም ሆነ በውጤቱ ሊጠቀስም ይችል ነበር፡፡ለቁጣ ፈጣን በሰሩ ለነበሩትም ቀና ስሜት ያልነበረው ነበር፡፡ በ2008 ብርቱካን ሚዴቅሳን ሲያስር፤‹‹ብርቱካንን ለመፍታት አንዳችም መግባባት የለም ጨርሶ አራት ነጥብ፡፡ ያለቀ የደቀቀ የሞተ ጉዳይ ነው፡፡›› ብርቱካን አንዳችም ስህተት አልፈጸመችም ነበር፡፡በዓለም አቀፍ እውቅናን ያላቸው ጋዜጠኞች ሰርክ ዓለምና እስክንድር በወህኒ ቤት ለተወለደው ከጊዜው በፊት ለመጣው ልጃቸው የማቆያ መሳርያ ተጠቃሚነትን መከልከል፤ለሰብአዊነት እንደሌለው ጭፍን አመለካከት በገሃድ ያሳያል፡፡ ለአሜሪካን ዲፕሎማቶች ‹‹ ተቃዋሚውን ወገን ባለ በሌለ ሃይላችን እንደቁሳቸዋለን›› በማለት ገደብ የለሽ ፉከራውን ሲያሰማ ዋጋ ቢስነቱን አሳወቀ፡፡ከአካኪ ዘራፍ ይቅር ማለትን በስልጣን ላይ በነበረበት ማሳየቱ የበለጠ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ይልቅስ ቂም በቀልን መረጠ፡፡ መለስ የማንዴላን ፈለግ በመከተል፤ ከተቀቃዋሚዎች ጋር በመስራት ጠላቶቸሁን ወዳጅ አድርጎ ሊያሰልፍ በቻለ ነበር፡፡ በዚህም ዕድል ሊፈጥርለት ከሚችለው ቀጠሮ ጋር ተለያየ!
በቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመን፤ በደህነነት፤በግል የኤኮኖሚ ግንባታ፤ በዋስትናም ጭምር የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍ ለማድረግ በሚያስችል ዕድል ላይ መለስ ቀጠሮ ነበረው፡፡መለስ‹‹በኤኮኖሚ ዕድገትና በዴሞክራሲ በታሪክም በቲዎሪም ቀጥታ ግንኙነት የለም››ብሎ ያምን ነበር፡፡ ሕዘቡ መሰረታዊ መብቱን እየተገፈፈ፤ ወደ ግጭት እየተመራ፤ግጭትንና ጦርነትን እንዲያስብ እየሆነ እንዴት ተደርጎ ነው ዘላቂነት ያለውን እድገት የሚያመጣው፡፡ የሰበአዊነት መሰረቱ ክብሩ ነው፡፡ሆድን መሙላት ላይ ብቻ ያተኮረ ግን አይደለም፡፡እርግጥ የተራበ ሰው ቁጡና ግልፍተኛ ነው፡፡የዚያ የተራበ ሰው ዓላማ ግን ፍርፋሪ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የሕሊና ነጻነትና ክብሩንም ማግኘት ነው፡፡
የድሆች ድሀ፤እና የቱጃሮች ቱጃር ከምንም በላይ ከምግብም አስቀድመው ክብራቸውን ይናፍቃሉ፡፡ከእሩብ ምእተ ዓመት በፊት በሃገሪቱ የተከሰተውን ርሃብ በተመለከተ ዘገባ ላመቅረብ በቦታው የተገኘው የምእራቡ ዓለም ጋዜጠኛ እንደዚያ በመሰለ ረሃብና ችጋር ውስጥ ያለው ሕዝብ ለዕደላ ቢሰለፍም ክብሩንና ኩራቱን እንደተላበሰ ነበር እንጂ እንደርሃቡ አስከፊነት በመንሰፍሰፍና በመሽቀዳደም ለዕርዳተው ሲታገሉ አልታዩም፡፡ጋዜጠኛውን ያስገረመው በዚያን ወቅት አንዱ በሌላው ዜጋ ላይ ለሆዱ ሲል አንዱ ሌላውን በመግፋትና በመሽቀዳደም ማየት ባለመቻሉና ይልቅስ በመተሳሰብና በመከባበር አንዱ ሌላውን እያከበረ ማየቱ ነበር፡፡ክብር ደግሞ በተለያየ ገጹ ይገለጻል፡፡የመናገር ነጻነት፤የማሰብ፤በየሃይማኖት የእምነት፤የመሰባሰብ፤ለጉዳቱ አቤት የሚልበት፤ከማንኛውም በበለጠ ደግሞ አንድን መንግሥት ከመፍራት መላቀቅ፡፡ መለስ ግን ሰው በዳቦ ብቻ ይኖራል ብሎ ያምን ነበር፡፡በብቸኝነትም በግምብና በሞርታር አምኖ ኖረ፡፡በዚህም ያን የተስፋና የዕድል ቀጠሮውን ሳተ፡፡
መለስ ይቅር ባይና ታጋሽ አልነበረም፡፡አልፎ አልፎ ለምህረት ፈቃደኝነቱን እንደአስፋጊነት ሲጠቀምበት እንጂ ለይቅር ለእግዜር በሩን ከፍቶት አያውቅም፡፡ የሰጠውንም ምህረት ቢሆን እንደ መልሶ ማጥቂያ ጎራዴ ማርኳችሁ ባላቸው አናት ነላይ በማውለብለብ ነበር፡፡ዘወትርም እንደማራቸው ሁሉ መልሶ ደስ ባለውና ስሜቱ ባነሳሳው ወቅት ወደ ወጡበት ማጎርያ ሊከታቸው እንደሚችል ያሳስብና ይፎክር የነበረ ነው፡፡ከመወያየት ይልቅ ግጭትን፤ከማስማማት ይልቅ የራሱን ፍቃድ በመጫን ያምን ነበር፡፡የምንግዜም ፍላጎቱ በማሸነፍ ላይ ስለነበር ጨዋታው ሁሉ በዜሮ ግጥሚያ ይከተት ነበር፡፡ መለስ ከዕድል ጋር የነበረውን ቀጠሮ አጣው፡፡
መለስ ጨርሶ የሰራውን ስህተት የማያምን ተፈጥሮ ነበረው፡፡ስህተትን በማመንና ከስህተትም መማር እንደሚቻል ተገንዝቦት አያውቅም፡፡በሰራውም ስህተት ይቅርታ በመጠየቅ ስህተቱን በማረም ማስተካከል መቻሉንም ይጠላዋል፡፡በ2005 ዓ/ም ሕይወታቸው ያለፈውን 200 ሰላማዊና መብታቸውን ጠያቂ ዜጎች ሕልፈትና በጥይት ናዳ የቆሰሉት 800 የሚደርሱ ወገኖችን ሁኔታ በተመለከተ ሲጠየቅ የሰጠው አሳዛኝ መልስ‹‹ በመሞታቸው አዝናለሁ ነገር ግን እንዚህ እኮ ሰላማዊ ሰልፈኞች አልነበሩም ሰላማዊ የሆኑ ሰልፈኛች እኮ እጃቸው ቦንብ አይወረውርም፡፡›› ለዚህም መለስ ራሱ ካዋቀርው አጣሪ ኮሚቴ የተሰጠው የምርመራ ውጤት እነዚህ ሰላማዊ ሰልፈኞች አንዳችም የጦር መሳርያ ያልያዙ፤ ባዶ እጃቸውን መብታቸውን ለማስከበር የወጡ ናቸው›› የሚል ነበር፡፡መለስ ሁኔታውነ በተመለከተ ለማስረዳትም ሆነ ሟቾቹን በተመለከተም ለቤተሰቦቻቸው የይቅርታ ስሜት እንኳን አላሳየም፡፡በዚህም የተነሳ ነው እኔ ከወንበር ላይ ያለ መምህርነት ወደ እማይሰለችና የማያቋርጥ የሰብአዊ መበት ተሟጋችነት የተለወጥኩት፡፡
መለስ ዘወትር ልክ ነኝ ብሎ ያስባል ባለሟሎቹንም ያሳምናል፡፡ከስህተቱና ከግድፈቱ መማር እንደሚችል ጨርሶ ተገልጦለት አያውቅም፡፡መለስ አንድ ጊዜ አውቆም ይሁን ድንገት አዳልጦት፤ስህተቱን ያመነበት ወቅት ነበር፡፡አንድ ጋዜጠኛ ስለውጪ ጉዞው የተከሰተውን ተቃውሞ በተመለከተ ሲመልስ፤‹‹በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስህተት ፈጽመን ይሆናል፡፡ አዝናለሁ፡፡ ምናልባትም ሰበቡ በሃገር ውስጥ ስለምናደርገው እንቅስቃሴ በአግባቡ ስላልገለጥንላቸውና ከማስረዳት ጉድለት የመጣ ነው::›› እዚህም ላይ ከዕድል አጋጣሚ ጋር የነበረውን ቀጥሮ ሳተ፡፡
መለስ የሕግን የበላይነት ቢያከብር ኖሮ የወጣለት መሪ ለመሆን ይችል ነበር፡፡ ደጋግሞ ‹ሕገመንግሥታችን›› እያለ ስለሕግ የበላይነት ቢወተውትም አንድም ቀን ግን ሕገመንግሥቱን አክብሮ ለሕግም የበላይነት እራሱን አስገዝቶ አያውቅም፡፡ስለ ሰብአዊ መብት ጥሰት በዓለም አቀፍ ሕብረተሰቡ እንደወቀሰ፤እራሱ ያወጣውን የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት መንግስት የሰብአዊ መበት ዘገባና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የመለስን መንግሥት ሕጸጽ ነቅሰው በማውጣት ለእርማት ጥሪ ቢያሰሙም የመለስን ጆሮ ማግኘት ግን አልተቻለም፡፡በዚህና በተመሳሳይ ሰበቦች መለስ ከጊዜ አጋጣሚ ዕድል ጋር የነበረውን ቀጠሮ አፋለሰ፡፡
መለስ የተግባር ሰው ነበር፡፡ ተግባርን ግን ከራዕይ ጋር አጋጨው፡፡ስለ ‹‹ኢትዮጵያ እድገት›› ይሰብካል ‹‹አንዳንድ ሰዎች ‹‹ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ልዕልናዋ›› ሊመልሳት ይፈልጋል ይላሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች የራሱንም አገልጋዮችና አምላኪዎች ጨምሮ ከሃገሪቱ ጋር ያለውን ትስስር ጨርሶ ማወቅ አልቻሉም፡፡በ2007 የሚሌኒየም አከባበር ላይ ‹‹በዚህ በአዲሱ ሚሌኒየም ንጋት ላይ ሃገራችን በዓለም ካሉ ድሃ ሀገሮች ግንባር ቀደምዋ ናት›› ብሎ ነበር፡፡በዚያው ወቅት ሲናገር ከሌላ 1000 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያዊያን 4ኛውን ሚሌኒየም ለማክበር ሲሰባሰቡ ሶስተኛው ሚሌኒየም ለኢትዮጵያ በኢትዮጵያ የጨለማው ወቅት መጨረሻ መጀመርያ ነው ይላሉ ነበር ያለው፡፡የሚያሳዝነው ግን ከሱ በፊት የነበሩት በርካታዎች እንደመለስ ሁሉ ብለው ነበር ግን ሲሳካ አልታየም እንጂ፡፡ በበርሊን ከሸፈባቸው፡፡በሮምም ከአንድ ምእተ ዓመት ተኩል በፊት ሳይሆን ቀረ፡፡ በተሪፖሊና በባግዳድም እንዲሁ፡፡ መንገድ ቢሰሩም፤ግንባታ ቢካሂዱም፤ ግድብ ቢገድቡም፤ ጦር ሰብቀው ጦርነት ቢያካሂዱም ሁሉም ተጠራርገው ወደ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ነው የወደቁት፡፡
ከመጻኢ ዕድል ጋር የኛ ቀጠሮ
እኛ የአሁኑ ዘመን ነዋሪዎች ከመጻኢ ዕድላችን ጋር አዲስ ቀጠሮ አለን፡፡ ቀጠሯችንን ከማክበራችን አስቀድሞ ግና፤መለስ ካተረፈልን ደጋግ ችሮታዎች ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተን መስማማት ኖርብናል፡፡ እውነቱም መለስ የደረጋቸው ተግባራት ሁሉ ብቻውን የፈጸማቸው አለመሆናቸውን ማመን አለብ፡፡ በመለስን ስህተቶች ስህተት ከማለታችን በፊት የራሳችንን ስህተቶችና ድክመቶች ተቀብለን ማመን ይገባናል፡፡ የመለስን ስህተቶች በመኮነን ብቻ የትም አንደርስም፡፡ ያን ማድረግ የሚያመጣው ተመልሶ ወደጠሉት መግባትን ብቻ ነው፡፡ ባለፈው ስህተት ስናመነዥክ የወደፊቱን ሂደታችንን መቃብሩ ውስጥ ሆኖ መለስ እንዲቀይስልን የምንመኝ ነው የሚያደርገን፡፡ ላለፉት 21 ዓመታት የታዩትን ድክመቶች በመንቀስ እያጠራን ወደፊት መሄድን፤ ቁስላችንን ማጥገግ፤ ከፍርሃታችን መላቀቅን፤ቅራኔዎችን ማስታረቅን መማር የግድ ነው፡፡ ታሪክ እያነሱ ጥላቻን ማጫር ዋጋ የለውም፡፡ ፍቅርን ለማነጽ መጣር አለብን፡፡ከየአንዳንዳችን ለእየአንዳንዳችን ፍቅርንና መተሳሰብን መሰጣጣት መማር ይገባናል፡፡አሁን እንግዲህ መለስ የለምና፤ ሁላችንም የማነዴላን ጫማ ተጫምተን፤ አቅማችንን አሰባስበንና አጠናክረን ኢትዮጵያችንን በጠነከረ መሰረት ላይ የሕግ የበላይነትን ለመገንባት መቆም አለብን፡፡ ያለፈ ጥላቻን ማንቆሩ ዋጋ ቢስ ነው፡፡ አሁን ያለውና የሚቀርብልን ጥያቄ ግልጽ ነው፡፡እኛም ከመጻኢ ዕድላችን ጋር ያለንን ቀጠሮ እናፋልሰው ይሆን?
በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ ‹‹ ከፈላጭ ቆራጭ ስርአት ወደ ዴሞክራሲ  የማይቀረው ሽግግር›› በሚል መነሻ ስጽፍ ነበር፡፡በዚህም ሽግግር ወቅት ሊደረግ ስለሚችለው ሂደት አማራጮችም ጠቃቅሻለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ  የአንድ ሰው የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭ ዲክታተሪያዊ አገዛዝ አክትሟል፡፡ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር ፍጻሜ ለማድረስ፤ለመጻኢ ዕድላችንም ቀጠሮውን ለማክበር ብሔራዊ የሰላምና የመግባባት ድርድር መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ለመጀመር ቅድሚያ ሚሰጠው ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፍታትና፤ፕያንንም አሳሪና ተብታቢ የሆነውን ‹‹የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ›› የተባለውን ደግሞ በማየት ቦታውን ማስለቀቅ ግንባር ቀደም ተግባር ሊሆን አማራጭ የለውም፡፡
ወደ መልካም  አስተዳደርና  ዴሞክራሲ ጎዳና
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመለስን ጠንካራና ደካሞ ጎኖች በማንሳት አስተያየቴን ሰጥቻለሁ፡፡ በግሌ ከመለስ ጋር አንዳችም ችግር የለኝም፡፡ተገናኝተን ተዋውቀንም አናውቅም፡፡የሱን ፖለቲካ፤ ሂደት፤ ንግግሮቹን፤ ግን ተከታትያለሁም አጥንቻለሁ፡፡ የኔ ትኩረት ሰበአዊ መብትን ያስቀደመ በመሆኑ በማንኛውም ነገር ከሱ ጋር አለመስማማትን ስመርጥም በቅድሚያ የሰብአዊ መብትን የማክበር ግዴታ መወጣት እንዳለበት ስላመንኩ ነው፡፡ የኔ አንዲት ሰበቤ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት መከበር ነው፡፡ በ2005 በተካሄደው ምርጫ ማግስት  በንጹሃን ዜጎች ላይ መብታቸውን ለማስከበር  ባዶ እጃቸውን ሕገ መንግሥቱን አክብረው በወጡት ላይ በተከሰተው ጭፍጨፋ ሳቢያ ነው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ላይ ትኩረት አድርጌ መንቀሳቀስ የጀመርኩት፡፡ እኔ ቆራጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ:: ይህም ወንጀል ነው የሚባል ከሆነ እኔም ወንጀለኛ ለመሆን በኩራተ ዝግጁ ነኝ፡፡
መለስ ከመጻኢ ዕድል ጋር እንደጀግና ኖሮ እንደ ጀግና ለማለፍና ሃገሪቱን በመላ መቀበሪያው ለማድረግ ቀጠሮ ነበረው ብዬ አምናለሁ፡፡ የታላላቅ ስራዎቹ ታሪኩና ልእልና በእብነ በረድ ላይ ሳይሆን በሃገሩ ሰዎች በሴቱም በወንዱ ልብ ውስጥ ሊቀረጽለት ይችል ነበር፡፡ እኔ ግን እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች የመለስን ልእልና የማስበው በ2005 ዓ/ም ከተፈጠመው ጭፍጨፋ ጋር በማያያዝ፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን የፖለቲካ እስረኞች የሚታጎሩበትን ወህኒ ቤት፤ የፖለቲካ መገልገያ የሆኑትን ችሎቶች፤እና የሕግ የበላይነት የተደፈረበትን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡
መለስ በ2007 ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተስፋውንና ሊያደርግ የሚፈቅደውን ግን ጨርሶ ያልተሞከረውንና እንዲሁ በቃለ ምልልስ ብቻ ተሰምቶ የተቋጨውን ሃሳቡን ሰምቼ ነበር፡፡ በዚያ አባባሉ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከመከራና ከፍትሕ እጦት ከዴሞክራሲ አፈና፤ ተጠያቂነትን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የተስፋ ብልጭታ እንዳለው ተናግሮ ነበር፡፡ ያ ግን ነበር ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ አንዱም አልተሳካም፡፡ተስፋዬ ነው ብሎ ያነሳቸው ነጥቦች በተግባር ቢተረጎሙ ኖሮ ታላቅ እድገት እናይበት፤ ነጻነት የምናይበት የምንመሰክርበት ራዕይ ነበር፡፡ያ መለስ ያለው የወደፊት ተስፋ አሁን ነው፡፡የሱን ሳይቋጭ የቀረውን ራዕዩን መተግበር ያለብን አሁን ነው፡፡መልካም አስተዳደርንና ዴሞክራሲን በተግባር ማሳየት የሱን ያልተቋጨ ተስፋ ከግብ ማድረስ ነው፡፡ ይህን የመለስን ችሮታ ተተኪ ባለስልጣኖቹ በግልጽ አምነውና ገሃድ አውጥተው የመለስን የአመራር ብቃት የማሳያ መዘክር ሊያደርጉት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ፈጣን ለውጥ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ላይ ተመስርቶ አሁን መጀመር ያለበት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በነጻ በመልቀቅና ያንን አሳሪ ሆነውን የሽብርተኝነት አዋጅ በሕግ የበላይነት ላይ በማስተሳሰር ሊሰራ የሚችል እንጂ የቂም መወጫነቱንና የዝም ማሰኛነት ባህሪውን በመለወጥ ማስተካከልን ተግባራቸው ሊያደርጉት ይገባል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያዊያን ዓመት መለወጫ ዳር ላይ በመሆናችን በአዲሱ ዓመት ፈጣን ለውጥን በመልካም አስተዳርና በዴሞክራሲ እውነታ ሂደታችንን እንደ አዲስ መጀመር ይኖርብናል፡፡
ሁለቱን አሰርት ዓመታት የመለስን አገዛዝና የግዛት ዘመኑን ለማክበር ትንሽ በኑሮውም በሕልፈቱም ጀግና የሆነው ሰው ለማለት ብችል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ወንዱ ም ሴቱም ትልቁም ትንሹም፤እንባቸውን እንደጅረት እያፈሰሱ፤በፈቃደኝነት፤ አንዳችም እዝና ድጎማ ሳይደረግበት፤ የቀበሌ አዋጅ ሳይታከልበት፤ አልቃሽ ሳይቀጠርና ለደረት መምታት አንድ ዋጋ ለእንባ ብቻ ሌላ ዋጋ ሳይተመንለት፤ አልቅሱ ተብሎ ሳይለፈፍበት ሕዝቡ በራሱ ፈቃደኝነት ቢያነባለትና መንገዱ ሁሉ እንባ መራጫ ቢሆን ምን ያህል ደስ ባለኝ ነበር፡፡ያ እንዳይሆን ግን ሞቱንና ቀብሩን የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ አሁንም በሕይወቱ በነበረ ጊዜ አበጀህ ሲሉትና ሲገፋፉት የነበሩት አሁን ደግሞ ለራሳቸው ጥቅም ማስጠበቂያ አደረጉት፡፡ለመለስ እንደ አንድ አክራሪ ሂስ አቅራቢው ልከፍለው የምችለው ከበሬታ ያን ‹‹ፈጣን ለውጥና መሻሻል በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ግንባታ”  በኢትዮጵያ ሲካሄድ ሳይ ብቻ ነው፡፡
ለአንድ ጋዜጠኛ መለስ በአንድ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያዊያን እኔን ዲክታተር ነው የሚሉ ከሆነ ሌሊቱን በሙል እንቅልፍ ሳልተኛ አድራለሁ ግን እርግጠኛ ነኝ ይህን አይሉም›› ብሎ ነበር፤ የሚገርመው ግን፤መለስ ለመጨረሻ ጊዜ ከአንድ ቆራጥ ወጣት ጋዜጠኛ አንደበት የሰማው ቃል ይህንን የተጠራጠረበትንና ሊሸሽገው የሞከረውን እውነታ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ያንን አልጠበቅሁምም አላሰብኩም ነበር፡፡ግን ሆነ፡፡በጊዳዩ አልቆጭም፤ሆኖም ግን በጊዜው መጨረሻ ላይ መሆኑና ማረጋገጫውን ማሰማቱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ::››
ሌሎች ሰዎች መለስን ባለ ራዕይ፤መሪ ታሪክ የማይዘነጋው አፍሪካዊ መሪ፤›› በማለት የሕይወት ታሪኩን አጀግነውና አሰማምረው ይጻፉለት፡፡ እኔ ግን  ሼክስፒር: ከጁሊየስ ቄሳር ጽሁፍ ቃላት ተውሼ በዚያ እሰናበተዋለሁ፡፡
ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የራሳቸው መጨረሻ እድል ባለቤቶች ናቸው
ውድ መለስ የኛ ህልውና በከዋክብቶቻችን ላይ አይደለም
በራሳችን እንጂ፤ እኛ ታዛዦች ነን::
ስለዚህ:
ወዳጆች፤ኢትዮያዊን፤የሃገሬ ወንዶችና ሴቶች ጆሯችሁን አውሱኝ
አሁን ወቅቱ መለስን መቅበሪያ እንጂ ማመስገኛው አይደለም
ሰዎች የሰሯቸው እኩይ ተግባራት ከኋላቸው ይቀራሉ
መልካሞቹ ግን ከአጥንቶቻቸው ጋር መቃብር ይወርዳል
ለመለስም እንዲሁ ይሁን::

No comments:

Post a Comment