ከአራት ወራትና ሞቶ ከተቀበረ ከአንድ ሳምንት በኋላ ዛሬም የወያኔ አገዛዝ መሪ መርጦ አገሪቱን ማረጋጋት ተስኖት አገራችን ኢትዮጵያ በባህላችን መሠረት “እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ” የሚል የአገር መሪ ሳይኖራት አዲሱን አመት ለመቀበል በዝግጀት ላይ መሆኗ ህዝብን እያናገረ መሆኑ ተሰማ። አገርን ሲመራም ሆነ ሲዘርፍ ምንም ነገር በግልጽ መስራት የማይሆንለት የወያኔ አገዛዝ ለምን እስከዛሬ ድረስ መለስ ዜናዊን ተክቶ የተፈጠረዉን የአመራር ክፍተት መድፈን እንዳቃተዉ ከራሱ አንደበት የተሰማ ምንም ነገር ባይኖርም ጉዳዩ በወያኔ ባለስልጣኖችና በኢህአዴግ ፓርቲዎች መካከል በመካሄድ ላይ ያለዉ የስልጣን ሽኩቻ መሆኑን ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
በወያኔ መሪዎችና በኢህዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል በመካሄድ ላይ ያለዉ የስልጣን ሽኩቻ ከጠረቤዛ ዙሪያ ዉይይት አልፎ መለስ ዜናዊን የመተካቱ ሂደት በሀይል ከተፈጸመ ኢትየጵያ ዛሬም ከዘመነ መሳፍንት አገዛዝ አለመላቀቋን ያሳያል ሲሉ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ተናገሩ። ባለሙያዉ ንግግራቸዉን በመቀጠል ላለፉት ሃያ አመታት ፌዴራሊዝም ተገንብቶ የአገራችን የስልጣን ሽግግር ችግር አልባት አግኝቷል ሲባል የነበረዉ ነገር ሁሉ ተረት መሆኑን ባለፉት ሦስት ወራት ለማየት ችለናል ብለዋል።
አያሌ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ችግሮች ተብትበዉ የያዟት ኢትዮጵያ ያለመሪ ለረጀም ግዜ መቆየት ቀርቶ መሪ እያላትም አቅጣጫዋን የሳተች አገር ነበረች ያሉን አኚሁ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ያለ መሪ አንኳን አገርን የመሰለ ትልቅ ነገር አንድ ቤተሰብም ወደፈለገዉ ቦታ መድረስ እንደማይችል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ ዘረኝነት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኑሮ ዉድነት ህዝብን ባስጨነቀበት በአሁኑ ወቅት እነዚህን ችግሮች በተመለከተ አመራር ይሰጣል ተብሎ የሚታመንበት መሪ አለመኖር ጭንቀቱን እንደሚያባብሰዉና አገሪቱን ትልቅ ቀዉስ ዉስጥ እንደሚከትታት በዙዎች በመናገር ላይ ናቸዉ። በተለይ የኢትዮጵያ ህዝብ የመጪዉን ብሩህ ዘመን መምጣት በተስፋ በሚጠባበቅበት በአዲስ አመት ዋዜማ 99.6 በመቶ የህዝብ ድምጽ አገኘሁ የሚለዉ የወያኔ አገዛዝ በጭቅጭቅና በስልጣን ሽኩቻ አዲሱን አመት ማክበሩ አገዛዙና ህዝቡ የተለያዪ መሆናቸዉን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ነዉ ተብሏል።
No comments:
Post a Comment