Translate

Tuesday, January 29, 2013

እግርኳሳችን የራሷን ሙሴ ትፈልጋለች


እግርኳሳችን የራሷን ሙሴ ትፈልጋለች

game
ስሜት ጎርፍ ነው፤ ያውም ደራሽ ጎርፍ፤ ብሄራዊ ቡድናችንን ስንደግፍም ሆነ ስናወድስ እንዲሁም ስንወቅስ በዚሁ ደራሽ ጎርፍ መወሰዳችን ይታያል። ይሄ ችግር ግን እንደ ሃገርም ችግራችን እየሆነ የመጣ ነገር ነው በስሜት መደገፍ በስሜት መቃወም፤ ዛሬ ያወደሱትን ነገ መርግም ሁሉንም ነገር በዘላቂ ጥቅም፤ በዘላቂ ስራ እና በዕውቀት መመዘን እያቃተን ነው። ከዚያም ዐልፎ ስሜታችን ጫፍ ላይ በሚደርስበት ጊዜ ሰከን ብሎ የሚያስብ ሰው ሲያጋጥመን እንደጭራቅ እንመለከተዋለን። ከእኛ በሓሳብ የተለየ አስተያየት የሰጠ እንደሆነማ በቃ ቤተክርስቲያን ውስጥ የገባ ውሻ እናደርገዋለን።…
የሰሞኑ የብሄራዊ ቡድናችን ውጤትም የዚህ ጎርፍ ሰለባዎች መሆናችን አንዱ ማሳያ ነው። መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አዲስ አበባ ከቤኒን ብሄራዊ ቡድን ጋር ሲጫወት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የአሰላለፍ ስህተት ሰርቶአል መሃል ላይ ምንም ፈጣሪ /creative/ ተጫዋች አልነበረውም በሚል ከውጤቱ በኋላ ህዝቡም ጋዜጠኞችም ሲያወግዙት ከረሙ። ልብ አድርጉ እዚህ ጋር ሁሉም የሚያወራው በስሜት የዕለቱን ጨዋታ በተመለከተ የነበረውን ችግር እንጂ በዕውቀት የሃገራችን እግርኳስ ችግር ምንድን ነው? ብሎ ስለዘለቄታው የሚያወራ እና የሚያስብ የለም። ፌደሬሽኑም ቢሆን ህልውናውን ከጊዜያዊ ውጤት ጋር አጣብቆ የተቀመጠ ስለሆነ ዘለቄታዊ ስራ ሲሰራ አይታይም እናም አቶ ሰውነት ያቺን የተችት ፍላጻ እንደምንም ሽል ብለው አሳለፏት ። …
ቀጥሎም ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሱዳንን አሸንፈን ለአፍሪካ ዋንጫ አላፊ መሆናችንን አረጋገጥን፤ ስሜት አሁንም እንደደራሽ ጎርፍ አጥለቀለቀን ህዝቡ ”ሳላዲን ጥቁር ሰው” ተባለ። ሲሰደብ የነበረው ሰውነት በየኤፍኤም ራዲዮው ጋሼ ጋሼ መባል ተጀመረ። አንዳንዶቹም ኢትዮጵያዊው ሞሪኖ ይሉት ጀመር። አሁንም እዚህ ጋር ረጋ ብሎ በዕውቀት ይሄ ውጤት ጊዜያዊ ነው፤ ዘለቄታዊ ውጤት የምንፈልግ ከሆነ ሰከን ብለን የእግርኳሱን ችግር እንመልከት በስሜት አንነዳ የሚል ሰው ሲገኝ እንደከሃዲ ሃገሩን እንደማይወድ ተቆጥሮ መወገዝ ጀመረ በስሜት! አቶ ሰውነትም ይህቺን ስለሚያውቅ በሴካፋ ውድድር መሳተፋችን አስፈላጊ አይደለም ብሎ ራሳችንን ከሴካፋ ውድድር እንድናገልል አደረገ። ለምን? ምክኒያቱም ስሜታዊ መሆናአችንን ስለሚያውቅ በሴካፋ ላይ የሚመጣው ውጤት የእርሱን ከብሄራዊ ቡድን ጋር ቆይታ ስለምትወስን ቁማሩን መቆመር አልፈለገም። አዎ ስራዎች በዕቅድ እና በዕውቀት ሳይሆን በስሜት በሚሰሩበት ሃገር ለምን ሪስክ ይወስዳል? …
የዛምቢያውን ጨዋታ አቻ ስንወጣማ ሁሉም ራሱን በስሜት አበደ፤ በደራሹ ውሃ እየተገፋ የሃገር ፍቅር ስሜት በሚል ሽፋን ተጫዋቾቹ ወኔ አላቸው ጀግና ናቸው ማለት ተጀመረ። በዚህ ወቅት እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ረጋ ብለው በስሜት ሳይነዱ እግርኳስ ጥበብ እንጂ ወኔ አይደለም ብለው ለመናገር ድፍረት የአገኙት እንደ Genene Mekuria Libro ያሉት ሰዎች፤ ግን ማን ያዳምጣል? ሁሉም በስሜት ባሉን እየተንሳፈፈ ነው ከጋዜጠኛ እስከ ፌደሬሽኑ ድረስ፤ እንደማይደርስ የለም ዐርብ ዕለት የቡርኪናፋሶ ውጤት የስሜት ባሉኑን ክፉኛ አስተንፍሶት ከነበርንበት ከፍታ በድንገት ከመሬት ወርደን ዝርግፍ አልን ፤ አሁን ደግሞ አሰልጣኙን ማውገዝ ተጀመረ በሳምንት ውስጥ ስናወድሰው የነበረውን ሰውዬ ወደተለመደው በስሜት ማውገዝ ተጀመረ ያሳዝናል ። …
በሃገር ፍቅር ስሜት ቢሆን በቁርጠኝነት ቢሆን ኖሮ የአፍሪካ ዋንጫን አይደለም የዓለም ዋንጫንም ቢሆን ከእኛ ልጆች የሚነጥቅ ሃገር አይኖርም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ለተጫዋቾቹ ያለኝ ክብር በጣም ከፍተኛ ነው የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል የቆጠቡትም አንዳች ነገር አልነበረም እናም ክብር ይገባቸዋል። መጪው ውጤት ምንም ቢሆን ቢያልፉም ባያልፉም ለእነሱ ያለኝ ክብር አይቀንስም … አሁንም ቢሆን ግን ከጊዜያዊ ውጤት ባሻገር ነገሮችን በዕውቀት የሚመለከት ጋዜጠኛ፤ በዕውቀት የሚሰራ ፌዴሬሽን እና ጊዜያዊ ውጤት ተመልክቶ ሳይሆን ዘላቂ ስራዎች እየተመለከተ የሚደግፍ ተመልካች ያስፈልገናል። እግርኳስ የስሜት ስፖርት መሆኑ ሳይረሳ ስሜቱም በሜዳ ላይ እንጂ ከሜዳ ጀርባ የሚሰራው ነገር በሙሉ በዕውቀት እና በጥበብ የሚሰራ መሆኑም ሳይዘነጋ …
አዎ እግርኳሳችን የእራሷን ሙሴ ትፈልጋለች!

No comments:

Post a Comment