Translate

Thursday, January 24, 2013

ተከደነ ብቃት በዓለም አደባባይ ሲውል


“Eine große Überraschung”  EuroSprt

“አንድ አዲስ ያልተጠበቀ ብርቅዬ ነገር”

ከዛሬ የከሰዓት በኋላ ኢሮ ስፖርት ትንተና የተወሰደ
ከሥርጉተ ሥላሴ 22.01.2013
መቼም ፍቅር ከነተፈጥሮው የሚገኝበት ሚስጢር ከእናትና ከማልያ ላይ ብቻ ነው። የማልያ ፍቅር ተጫዋቹን ብቻ ሳይሆን ታዳሚውንም በሙሉ ፈቃደኝነት የሚሰደምም  … ዕጹብSouth Africa Ethiopian fans ድንቅ ጥበብ ነው። የበቃ!
እግር ኳስ የዓለምን ህዝብ በፍቅር ክንፍ የሚያደርግ ጨዋታ ነው። ሌላው ቀርቶ የእግር ኳስ ህግጋትን በሚመለከትም ከዳኞች ባላነሰ ታደሚዊቹ በቂ ዕውቀት እንዳላቸው እገምታለሁ። ስለምን? በእግር ኳስ ጨዋታ ታዳሚው በባለቤትነት ስሜት መንፈሱንና አካሉን በፈቃዱ ለድንቡልቡሏ ውብ ተዋናይ በውዴታ ስለገበረ፤ ሰለለገሰ በቀላሉ ሜዳ ላይ ባለው ትዕይንት ብቻ መማር ስለሚቻል።
የተቀባው እግር ኳስ ዕልፍ አዕላፋትን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍቅር ብቻ ቤተኛ
በሚያደርገው  ስጦታው በሙያው የሰለጠኑ፤ በጸጋው የተካኑ የብርቅና ድንቅ ሰዎችም ማፍሪያ ተቋም ነው። እግር ኳስ በሰው ኃይል አሰላለፍና አደረጃጃትም ሆነ አመራር ከዓለም- ዓቀፍ ጀምሮ እስከታች ድረስ በተዋረድ ሰፊ ሰራተኞችን ያሰማረ የሥራ መስክ ነው።
እግር ኳስ በኢኮኖሚ አቅሙ ሆነ በዓለምዓቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ተጽዕኖ በማሰደር እረገድም አንቱ የተባለ ነው። ዘረኝነትን በመዋጋት እረገድም ግንባር ቀደም ሲሆን፤ በማህበራዊ ህይወትም ቢሆን ወሳኝ ድርሻ ያለው ዘርፍ ነው። እግር ኳስ የአንድ ሀገርን የባህል ደረጃ ከፍ ከሚያድርጉት ወሳኝ ክስተቶች አንዱ ሲሆን፤ አብሶ አዲሱን ትውልድ በፍቅር በመገንባት በኩልም የእራሱ መጠነ ሰፊ አስተዋፆ አለው።
በሌላ በኩል በህጉ አፈጻጸም አካሄድ በኩልም የእኔ የሚለው የችሎት አደባባይ ያለው ሲሆን አብሶ ሜዳ ላይ በትወና፤ በፊሽካ፤ በቢጫና በቀይ ካርድ ቅጣት፤  በነፃና በማዕዘን ምት ተንቆጥቁጦ በራሷ ጊዜ ድንቡልቡሏ መረብ ላይ ስተሞሽር ልብን በሐሤት የሚያስጨፍር፤ ፍጹም የሆነ ፍሰኃን የሚቸር ውበት ያለው የህበረት መንበር ነው።
ከሁሉ በላይ አስልጣኞች ከሜዳ ውጪ ሆነው ልጆቻቸው የሚያድረጉትን እንቅስቃሴ በመከታተል ጎል ሲጋባ፤ ሆነ ምቱን ሲስቱ፤ እንዲሁም ሲቀጡ፤ ሜዳ ላይ ተቀናቃኛቸው በሚፈጥረው ግፊያ ሲወድቁም ሆነ ሲነሱ፤  የሚያሳዩት ልዩ እንቅስቃሴ ሌላኛው የደስታ ማሳ ነው – ለእኔ። አብሶ ሲሸነፉ ጋዜጠኞች ሲያፋጥጧቸው የሚያቀርቧቸው ሰበቦች ልዩ ድራማ ነው – አሁንም ለእኔ፤ በለስ ቀንቷቸው ካሸነፉ ደግሞ ተዘጋጅተን ገባን፤ አሸነፍ በማለት በሙሉ ልብ ሲናገሩ ማዬት ውበቱ ጥንድ ነው። ቡድኖቻቸው ያሸነፉላቸው አሰልጣኞች አንዳንዶቹ ትንሽ ጣሪያ ጣሪያ ሲሰኛቸው ማዬቱ ደግሞ በራሱ ሌላው የህይወት ት/ቤት ነው። እኔ ያለበትን ማዕከላዊ እንብርት ያሳያል። ትችቱ፤ ድጋፉ ሲደማመር ደግሞ ውበቱን ያነጥረዋል።
ከእግር ኳስ ጨዋታው ጋር እጅግ በርካታ ጉዳዮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይታደማሉ … ፤ ወጌሻዎች ሲራወጡ፤ የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ለመቸር ሲጣደፉ፤ አራጋቢዎች ገራና ቀኝ ሲከንፉ፤ የመሃል ዳኛው ሜዳው አልበቃ ብሏቸው ሲባትሉ፤ የጸጥታ አስከባሪዎች አካባቢውን በቅኝት ሲያፋጥጡት፤ እራሷ ድንቡልቡሏ – ስትደለቅ – ስትረገጥ በጥፊ ስትናጥ፤ ሜዲያ ደረቱን ገልብጦ እንካችሁ እንደ አሻችሁ ጨፍሩብኝ ብሎ ሲያውጅ፤ ሆቴሎች ተሰናድተው ሲቀበሉና ሲሸኙ፤ ማለያዎች ከሙሸሮች ጋር ሲፍነሸነሹ፤ ሰንደቆች ከፍ ብለው አንገታቸውን ቀና አድርገው ሲወርቡ፤ ድምጽ ማጉሊያዎች ከባትሪ ጋር ተጋብተው በድምጽ ሲፈርሹ፤ ሰዓት ተሎ ተሎ እያለ አቅልን ሲዘቀዝቅ … ለባለ ድሉ እኔ አለሁ ሲል  ዋንጫው … ሳተናው ጋዜጠኛ ሁለገብ ተግባሩን ለመከወን ትጥቁን አሟልቶ ሲገሰግስ ሁሉም በዬፊናቸው ዬዬራሳቸውን መክሊት ይዘው ጨዋታውን በሁሉሙ መስክ ያስጌጡታል።
ከዚህም ሌላ በአፍሪካ ሆነ በዓለም የዋንጫ ውድድር ጨዋታውን ተከትሎ የሚፈጠሩ የዝምድና ግንኙነቶች እስከ ጋብቻ ድረስ የሚያደርሱ፤ ህይወትን መስመር ሊያስዙ የሚችሉ ገጠመኞች ሁሉ የእግር ኳስ አልማዛዊ ማህደሮቹ ናቸው። ከሁሉ በላይ እግር ኳስ ብሄራዊ ስሜትን የማነሳሳት አቅሙ የላቀና የመጠቀ ነው- እንዲያውም አንጡራ ሃብቱ ነው ማለት ይቻላል። ሰንደቅዓላማ ልደትህ መቼ ነው? ተብሎ ቢጠዬቅ በአህጉራዊና  በዓለምዓቀፋዊ  የእግር ኳስ ጨዋታ ብሎ እንደሚመልስ እርግጠኛ ነኝ። እግር ኳስ ይጠራል – ማንነትን፤ …. እግር ኳስ ያናገራል ውስጥን፤ እግር ኳስ ያስተሳስራል ህብረትን፤ … እግር ኳስ ልቡ – የሰላምና የፍቅር ማማ ሲሆን ጠንካራ ክንዱ ደግሞ ሐሤትን ማፍለቅ ነው። …
እኛም በ2013 እ.አ.አ በ2005 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ለአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ታዳሚ ለመሆን በቃን። እግዚአብሄር ይመስገን። ይህ ዕድል በብዙ መልኩ ሲመነዘርና ሲዘረዘር የድንቁ ባላወለታ፤ የተከበሩት የፓን አፍሪካኒስቱ ዬይድነቃቸው  ህልምና ስኬት ነው። የኪንግ ማርቲን  ህልም በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዕውን እንደ ሆነው ሁሉ የተከበሩ ዕንቁችን ዬይድነቃቸው ህልም ደግሞ በዕንቡጦቻችን ይኸው ዕውነት ሆነ ዛሬ።
በሌላ በኩል ዕድሉ ቁልፍ ነውና ይኸው ሰፊ በር ቧ ብሎ ተከፈተ። ትናትም ዛሬ ኢሮ ስፖርት ስለ ይድነቃቸው ፍሬዎች እጅግ አበረታች ትንተናዎችን እዬተሰጠ ነው። መጀመሪያ ላይ ኢሮ ስፖርት እርግጠኛ አልነበረም።  በቅድመ ዝግጅት ትንተናዎች ላይ በጥቅሉ ከ30 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ዕድሉ እንደተገኘ ሲዘግብ ሰነባበት። ስለምን? ብዙም የይድነቃቸውን ልጆች መሰረት ስላላጠና መሰለኝ። ትናንትና እና ዛሬ ግን እጅግ ምርጥ በሆኑ ቃላት ብሄራዊ ቡድናችነን እያሽሞነሞነው ይገኛል። „ፈጽሞ ዕውቅና ያልነበረው፤  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግልና የህብረት ጨዋታ ውብ የሆነ፤ ሳንጠብቅው በመንፈሳችን ላይ ተጽእኖ የፈጠረ ብቁ  አዝናኝ ጨዋታ ነው፤ ያልተጠበቅ ትልቅ ልዩ ብርቅና ድንቅ ነገር፤ የተመልካችን አትኩረትን በእጅጉ የሳበ፤“  ሲለው … በሌላ በኩልም የተቀናቃኙን  የዛንብያን ቡድን በሚመለከትም „የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛንብያን ተስፋ አሳጣ፤ የዋንጫ ባለቤት የነበረው ዛንቢያ ያልጠበቀው ሽንፈትና ሰቀቀን ገጠመው። ዛንብያ ውጤቱ እንደጠበቀው ሳይሆን ቀረ“ በማለት አጣጥሎ ዘገበው።  ኢሮ ኒውስ ብሄራዊ ቡድናችን አግኝቶት የነበረው  የፔናሊቲው ምት አለመሳካቱን አልደነቀውም። እቁብም አልሰጠውም ። ጨርሶም ሲያነሳው አልሰማሁም። ለኢሮ ኒውስ ልብና ቀልብ የሳበው እኩል ለእኩል መውጣቱንና፤ የጨዋታ ብልጫ ሆነ ጥበብም ከብሄራዊ ቡድናችን ያዬ መሆኑን ነው ዘጋቢው በደስታ የሚገልጸው …
ብዙ ዕድል ስል ከላይ ያነሳሁት ነጥብ ነበር … ኢሮ ስፖርት አሁንም ቅድምም የይድነቃቸውን ልጆች እያመጣ ሲሳዬን በውስጣችን ያለችውን እናት ሀገራችን ኢትዮጵያን ሲያነሳሳ ደስ ይላል። ሌላም ስንት እጮኛ ተሰልፎ ይሆን ለቀንበጦቻችን? አንድ ሰው ብዙ ነው- ለእኔ።  (ማለት እራሱ ግለሰቡ፤ ቤተሰቦቹ፤ ደጋፊዎቹ፤ ሁሉ ሲደማማሩ የትዬሌሌ ነው። የቁጥር ተማሪ እባካችሁን ሁኑ።)
… አጋጣሚው እረድቶ ለውጪ ሀገር ክለቦች የመጫወት ዕድል ከኖረ ብዙ ነገር ይታፈስበታል። ለአዲስ ልምድና ተመክሮ መንገድ ይኖራል፤ ተጫወቾች ዕውቀታቸውን የማሻሻል ሆነ የመማር አጋጣሚ ይኖራቸዋል፤ የአኗኗር ደረጃ ከፍ ማለትን ያመጣል፤ የፕሮሚ ሰውነትንም ያስገኛል፤ ዬፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ማዕረግንም ያክላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አጋጣሚዎቹ ስለሚያግዙ ተደማጭነትም ማግኘት ያስችላል። በተጨማሪም  …. የሌላ ሀገር የእግር ኳስ አፍቃሪ አዲስ ደጋፊ ማፈራትን ሁሉ ያካትታል … የሶሊዳሪቲ ማዕደኝነትም እንደ ማለት። ድንበር አልባ ፍቅርና  የጸሎት ጥበቃም … ያስገኛል … ጠንክሩና እፈሱ ውዶቻችን ….
አዎን 21ኛው ምዕተ ዓመት የእግር ኳስ ጨዋታ ዕድገቱ እንደ ዘመኑ ነው። በዚህ ዘመን በሁሉም ዘርፍ ታዳሚ መሆን መቻል ለነገ ሟተት ነው። አይቦሪ በ2006 ጀርመን ላይ፤ በ2010 ደቡብ አፍሪካ ላይ የዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አፍቃሪ ማህበረሰብ ፋቦሪቲ -ቀዳሚ ተዋዳጅነትን ያተረፈ ነበረ – በዝሆኑ ድርጎባ አማካኝነት። ያው እንደምታውቁት አፍሪካዊው ድርጎባ በዝሆን ቅጥል ስም በዓለም ከሚታወቁት አምስት ኮከብ ተጫዎቾች አንዱ ነው። ከነሜሲ፤ ከነክርስቲያን ሮናልዶ ወዘተ …  ይህ ዕድል በቀጥታም በተዘዋዋሪም ብቃቱን በማጎልመሱ አዎንታዊ ትርፍ ለአይቮሪ አስገኝቶለታል። የሚዲያ አትኩሮትንም ከሌሎች ሀገር ብሄራዊ ተጫዎች ለእሱ ጫን ያለ ነው። የ2012 በአውሮፓ ሊግ የዋንጫ ጨዋታም እኩል ያደረገውን ጎል ያስገባም፤ የፔናሊቲውን የመጨረሻ ወሳኝ ጎል ያሰቆጠረ ድርጎባ ነበር። በመሆኑም ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግሊዙ ቻልሲ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቃ። ምን ለማለት ነው ነገ ተስፋው የፋፋ ነው … ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ እድገትና ዕውቅና – ግኝት የዘንድሮው ልዩ ናሙና ነው። በማስተዋል ሁነን ሁለገቡን ራዕይ እንዳስሰው …
ይገርማችኋል  ለእኔ አሸንፈዋል ዕንቡጦቻችን። የ30 ዓመት የታመቀ ህልም ፈተዋል። ትናንትና የፔናሊቲው ዕድል ሳይሳካ ሲቀር ምንም አልመሰለኝም። በፍጹም። ዋናው ፍሬ ነገር ታላቁ በር ተከፍቶ፤ ትብትቡ ተፈታቶ ከዚህ ደረጃ መድረሳቸው ነው። ነገ ሌላ አዲስ ብሩኽ  ቀን ነውና።
የብሄራዊ ቡዳናችን ሶስት አባላት ከሲዊዲን ራዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩትና ገረመኝ። ከእኛ እነሱ ይበልጣሉ። እነሱ ለኮፒ ራይት፤ ለልዩ ቅብ ሴሪሞኒ አይደለም የተሰናዱት። ለታላቁ ሚስጢር ለኢትዮጵያዊነት ብቻ  እንጂ። በማስተዋል የመለሷቸው ነጥቦች ሁሉ ጎሉን ማን አስገባ?! ሳይሆን የወል ዓላማቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ቀድመው የተመደቡላትና በውጤትም የሚመደቡላትን ተቀናቃኞቿን በመርታት  ለድል መብቃት ስለመሆኑ አስተማሩን። … ድንቅ ናቸው አይደል? መርቁልኝ። እርግጥ በጥያቄው እኔ ያልተመቸኝ አንድ ጥያቄ ነበር። „ስንት ጎል አስቆጥራለሁ ብለህ ታስባለህ?“ ይህን ጥያቄ አንድም ቀን በሌላ ጋዜጠኛ ሲጠዬቅ ሰምቼው ስላማለውቅ ምን ይመልስ ይሆን ብዬ ሳስብ መረቅ የሆነ መልስ ተሰጠበት። እኔ በእነሱ ኮራሁባቸው። በተረፈ ጎል ሁሉ ነገር ለተሟላላት ብሄራዊ ቡድን እንኳን ከነፃነት ጀምሮ ማለቴ ነው …
-        የአዬር ባህሪ፤
-        የተጨዋቾች ትንፋሽ ጤናማነት፤ የሥነ ልቦና ሰላማዊነት፤
-        የደጋፊዎች ብርታትና ጥንካሬ፤
-        የዕለቱ ዳኛ የአመራር ብቃት፤
-        የቀናት፤ የሰዓቱ ምቹነት … ዕድላማነት …
-       የተቀናቃኝ ጎል በቀኝ በኩል መገኘት፤
-       ከዚህ ሌላ ተቀናቃኝ መንፈሱ ሳይሰባሰብ የአጥቂውን ጉልበት ሳይመጥን  ቀድሞ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ማጥቃት መሰንዘር ወይንም መቅደም የመቻል ብቃት፤ ወይንም …
-       ባለቀ ሰዓት ተቀናቃኝ ደከም ብሎ ዛል ወይንም ሲጠነዝል ጥቃት የመሰንዘር ጥበብና ስልት …
-       ወይንም ተቀናቃኙ ቀድሞ በማስገባቱ ዘና ማለት ሲጀምር … ጎል ከመረብ ጋር የመገናኘት ዕድሉ ስምረት ያገኛል። የተዘራ ሁሉ እንደማይበቅል ሁሉ የተለጋ ሁሉ ወይንም ወደ ጎል የተቃጣ ሁሉ ግብ ሊሆን አይችልም። ብቻ ከላይ የጠቃቀስኳቸው እና ሌሎቹም ታክለው ጎል ጎል ጎል …  ይሆናሉ። ያስጨፍራሉ ያስደልቃሉ። ያሳብዳሉም።
ነገር ግን አንድ ተጫዋች እኔ በዚህ ጨዋታ በግሌ ይህን ያህል ጎል አስቆጥራለሁ ብሎ መገመትም ሆነ ማስላትም ግን ፈጽሞ የሚቻል አይመስለኝም። ጎል የህብረት ጥረት እንጂ የአንድ ሰው ውጤት አይደለም። አንድ ተጫዋች የማስገባት ዕድሉ እያለው ግን ለጎሏ ቅርበት ወይንም ለግብ ለተመቼው ተጫዋች ኳሷን ይልካታል። ከዛ በስልትና በጥበብ ቅብብል ኳስ ለመረብ ትዳራለች። ለዚህ የጀርመኑን ብሄራዊ ተጫዋች፤ በአሁኑ ወቅት የሪያሉ ክለብ ተጫዋች የሆነውን ኡዚልን ማናሳት በቂ ይመስለኛል። በ2010 ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ዓለምዓቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ የባዬሩ ክለብ ተጫዋች ሙለር የእግር ኳስ ንጉስ ተብሎ የተሸለመው ሆነ የተወደሰው …  ኡዚልና ባስቲ ባመቻቸሉት ፍትፍት ነበር። በምድር ላይ ኢጎይዝምን ካለይግባኝ የገደለ የሰለጠነ የሙያ መስክ ቢኖር እግር ኳስ ነውና። … በማናቸውም የትግል ሕይወት ውስጥ ከዚህ መጠራቅቅ የወጣ ህዝብ ሆነ ፓርቲ  ነፃነቱን ይጎናጻፋል።
ሌላው አብክሬ ላስገነዝብ የምፈልገው እግር ኳስ በጣም ከስሜት ጋር የተጋባ ነው። ከሥነ ልቦናዊ ሁነቶች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። በፍጹም ሁኔታ ከመንፈስ ጋር የተዋህደ ነው። ማሸነፍ የሚኖረው በራስ የመተማመን መንፈስ ሲጎለብት ነው። ይህ ለተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን ታዳሚዎችንም ይጨምራል። በሙሉ ኃይልና በአንድነት ብሄራዊ ቡድናችነን ልናበረታታ፤ ልናደንቅ፤ ልንደግፍ ይገባል። ምንም ዓይነት ክፈተት ሳይኖር በአኃቲ ልቦናና በቅንነት አዘውትረን ልናስባቸው ይገባል። እባካችሁን!?
ወገኖቼ እግር ኳስ 13ኛው ፕላኔት ነው። በ13ኛው ፕላኔት ደግሞ ታዳሚዎች በፍቅር፤ በመተባበር፤ በመረዳዳት፤ በመተሳሰብና በቅንነት በኪናዊ ህብረት የሰለጠነ ተግባር መፈጸም አለብን። ባለው የኤሌትሮኒክስ የግንኙነት መስመር ሁሉ ድሌ! ድሌ! ማለት አለብን። እስኪ ትንሽ ንጹህ አዬር እንተንፍስ … ወያኔ ከፈጠረው፤ ካመጣው ትርምስ ወጣ ብለን በያለንበት ለዚህች ለተወሰነ ቀን ተ ጫዎቾቻችን መንፈሳቸው፤ ሃሳባቸው፤ ስሜታቸው ሳይከፋፈል እስከ ቻሉት ድረስ እንዲገፉ እንደግፋቸው አደራ!
ከዚህ ሌላ መብለጥ ወተታችን ይሁን። መቅደም ማር ወላላችን ይሁን። ተጫዎቾቻችን ሲፊ ደጋፊ አላቸው። እሱን ሁሉ ሃብት ማደረግ የመቻልን ሥነ -ጥበብ እንካንበት። … ተሽለን እንገኝ። ሁሉ አለን። ሁሉንም መሆን እንችላለን። ምን ሲገደን?! በደማችን ውስጥ ያለው ብሄራዊ ስሜት ቀልቡን ባይሆን በብሄራዊ ቡድኑ ላይ እስኪ ትንሽ አረፍ እንዲል እንርዳው።
አራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
ድል ከክብር ጋር ለብሄራዊ ቡድናችን!
ዕልፍነታችን በድጋፍ እናንቆጥቁጠው!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

No comments:

Post a Comment