Translate

Monday, January 7, 2013

የጎልጉል ቅምሻ


የጎልጉል ቅምሻ

(ከዚህም ከዚያም)
gun wedding


ጋብቻ በጠብመንጃ
ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የ“ጠብመንጃ ጋብቻ” አሁን በከፍተኛ ቁጥር ቀጥሎ እንዳለ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ በላስቬጋስ የሚካሄደው ይኸው የጋብቻ ሥነስርዓት በቅርቡ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤት በተተከፈተ ተኩስ ህጻናት ከሞቱ በኋላ ይቋረጣል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ከተለያየ የዓለማችን ክፍል በመምጣት 500ዶላር አካባቢ በሚከፈልበትና በጠብመንጃ ሱቅ ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ሥነስርዓት ሙሽሮች የተለያዩ ጠብመንጃዎች፣ ዑዚ መትረየስ፣ ኤኬ47፣ ወዘተ (ታንክ ሲቀር) የጦር መሣሪያዎችን በመያዝ ቃለመሃላቸውን ከፈጸሙ በኋላ ለእነርሱ ብቻ በተዘጋጀ ቦታ ላይ የዒላማ ተኩስ በማድረግ ጋብቻቸውን በተኩስ ያደምቁታል፡፡
ወ/ሮ የመከላከያ ሚ/ር
ከተመሠረተ ጀምሮ ከወንዶች በስተቀር እንስት ሚኒስትር ያላየው የአሜሪካው የመከላከያ ሚ/ር (ፔንታጎን) ምናልባት የመጀመሪያዋን ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሊያገኝ ይችላል፡፡
ቀድሞ በመ/ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩትና ከአስራአምስት ወራት በፊት ከልጆቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እፈልጋለሁ በማለት ሥራቸውን የለቀቁት ሚሼል ፍሎርኒይ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሊሾሟቸው ይችላሉ ከተባሉት ምክትል ሚ/ሩ አሽተን ካርተርና ሪፓብሊካኑ ሴናተር ቸክ ሔግል በቀዳሚነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ጊዜ በሐዋይ የባሕር ግዛት ሽርሽር ላይ ሲሆኑ በዚህ ሳምንት ተመራጩን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ስድስት ተኩሳ አንድ ሳተች
በአሜሪካ የጆርጂያ ጠቅላይ ግዛት ነዋሪ በሆነችው ግለሰብ ቤት በመግባት ለመዝረፍ የሞከረው ሌላ እንዳሰበው አላጋጠመውም፡፡ ከሁለት መንትያ ልጆቿ ጋር የነበረችው እናት በሯ ሲንኳኳ እንደተለመደው ከበር በር እየዞሩ ዕቃ ከሚያሻሽጡ አንዱ መስሏት ሳትከፍት ትቀራለች፡፡  
ሁኔታው ግን እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ ዘራፊ ቤቷ መምጣቱን ስትገነዘብ በቶሎ ልጆቿን ይዛ ከጣራ ሥር በሚገኘው ትንሽ ክፍል (አቲክ) ውስጥ ትደበቃለች፡፡ ግን ባዶ እጇን አልነበረችም፤ ሽጉጥዋን ጥይት አጉርሳለች፡፡ ዘራፊው ክፍሉን ሁሉ በርብሮ እርሷና ልጆችዋ ወዳሉበት ሲደርስ፤- ተጠንቀቅ፣ አነጣጥር፣ ተኩስ!! ስድስቱን ጥይት ለቀቀችበት፤ አምስቱ ዒላማውን ሲመታ አንዱ ብቻ ሳተው፡፡ ፊቱን ይዞ እያለቀሰ እንደምንም አምልጦ ደሙን እያዘራ ወደመኪናው ቢገባም ብዙም ርቆ ለመሄድ አልቻለም፡፡ መንገድ ስቶ ከዛፍ ጋር ተላትሞ እዚያው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎታል፡፡ ቤት ያልነበረው አባወራ “ባለቤቴ ጀግና ነች፤ ራስዋንና ልጆችዋን በመከላከል አንድ የመሣሪያ ባለቤት ማድረግ የሚገባውን አድርጋለች” በማለት አወድሷታል፡፡
ዝነኛው ብስክሌተኛው ሊናዘዝ ነው
ባለፈው ጥቅምት ወር ሰባት ጊዜ ያሸነፈውን የፈረንሳይ ዙር ማዕረግ የተገፈፈው የዓለማችን ዝነኛ ብስክሌተኛ የነበረው አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ በይፋ ኃይልና አበረታች ዕጽ መውሰዱን በማመን ይቅርታ ሊጠይቅይችላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
በተደጋጋሚ የተነሳበትን የአበረታች ዕጽ ጉዳይ ሲክድ የነበረው አርምስትሮንግ ባለፈው ጥቅምት በእርሱ ላይ የወጣው ዘገባ “የስፖርቱ ዓለም ከተለመደው ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የተወሳሰበ፣ እጅግ ዘመናዊና በባለሙያ የተጠና እንዲሁም የተሳካ የዕጽ ፕሮግራም” ማካሄዱን መስክሮበታል፡፡ ከብስክሌት ውድድር ዕድሜልኩን የተወገደው አርምስትሮንግ ጥፋቱን በይፋ በመናዘዝ ቅጣቱን ለማቅለልና ለወደፊት በሌሎች ስፖርቶች ለመወዳደር ማሰቡን ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡
ባዶ ተስፋ
ከጥቂት ወራት በፊት ሳንዲ የተባለችው ዓውሎነፋስ የቀላቀለችው ዝናብ የአሜሪካንን በርካታ ምስራቃዊ ጠቅላይ ግዛቶችን ባጥለቀለችና ንብረቶችን ባወደመች ጊዜ የጉዳቱን ተጠቂዎች ፕሬዚዳንት ኦባማ ሲጎበኙ ዶና ቫንዛንትን ሲያጽናኑ የተቀረጸው በዓለም ዙሪያ የሚዲያ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡
የአነስተኛ ንግድ ባለቤት የሆኑት ዶና በወቅቱ ከኦባማ ለእርሳቸውና ለሌሎች የጉዳቱ ተጠቂዎች መልሰው እንዲቋቋሙ ከመንግሥት ፈጣን ርዳታ እንደሚደረግላቸው ተስፋ የተሰጣቸውም ቢሆንም በቅርቡ ባደረጉት ቃለምልልስ እርሳቸውና ሌሎች ተጠቂዎች አንዳችም ምላሽ ከፕሬዚዳንቱ እንዳላገኙ፤ ተስፋው ባዶ እንደሆ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ሌላም ሰሞኑን “የመከላከያ ሠራዊቱን ስለሚደግፉ ምስጋናችን እንገልጽልዎታለን” የሚል ፈጽሞ ግለሰቧ ያልጠየቁት ዓይነት ደብዳቤ ከኦባማ እንደደረሳቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የሳምንቱ ምርጥ ፎቶ
ምስሉን ያገኘነው ከፌስቡክ ነው፡፡ የ“ጀግናው” ሞት ያስቆጨው በሃዘኑ እስከዚህ ደርሷል፡፡ በገና በዓል ሥጋ ባንበላም፤ “የገና በዓል አይሞትም” ብለን ሥጋ ቤት ባንከፍትም፤ ሥጋ በፎቶና በቲቪ እያየን በዓሉን በቁጭት ብናሳልፈውስ?
ዘገባውን ለማጠናቀር በየጽሁፉ ከጠቀስናቸው ምንጮች በተጨማሪ ሌሎችንም የሚዲያ ውጤቶች መጠቀማችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከዜናዎቹ ማነስ አኳያ በየጸሁፉ ለመግለጽ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment