Translate

Wednesday, January 23, 2013

በጥምቀት በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲሸጡ የነበሩ ሰዎች ታሰሩ


ኢሳት ዜና:-ብዙውን ጊዜ በጥምቀት በዓል ጊዜ የሚጠቀሰውንና ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5 ላይ ያሰፈረውን ፦“አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጥምቀት” የሚል  የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተፃፈበት ቆብ  የጥምቀት ዕለት ለሰንበት ት/ቤታቸው ገቢ ማስገኛነት በመሸጥ ላይ የነበሩ ወጣቶች በፖሊስ ታፍሰው ታሰሩ።

እንደ ደጀ ሰላም ዘገባ፤ ጥር 11/2005 ዓ.ም ታቦተ ሕጉን ተከትለው በሞቀና በደመቀ ሃይማኖታዊ መንፈስ በማክበር ላይ እያሉ በፖሊስ የታሠሩት ስድስት ወጣቶች ሲሆኑ ፤ጥቅሱ የተጻፈበትን ቆብ ይሸጡ የነበሩት  ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ገቢ ለማስገኘት  እንደሆነ ተገልጿል።
 ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር  በአንድ ወቅት ወጣቶችን ሰብስበው ስለሀይማኖቶች ባደረጉት ገለፃ ፦ ተመሳሳይ ጥቅስ የተፃፈበትን ቲሸርት የለበሱ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን ፦<<አንዲት ሀይማኖት የሚሉ አክራሪዎች>>በማለት እንደዘለፏቸው ይታወሳል።

 አንድ ኣማኝ ለሚያምንበት ነገር ምክንያቶቹን እንደሚያቀርብ ሁሉ ክርስቲያኖችም ስለ እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱሳቸው የተፃፈውን ጠቅሰው ለራሳቸው ትምህርትና ጥቅም ማዋላቸው እንዴት ከ አክራሪነት ጋር እንደተያያዘ ግልጽ አይደለም ያሉት የሀይሞኖቱ አባቶች፤ “አክራሪነት ማለት የራሱን እምነት በሌሎች ላይ በሀይልና በተጽዕኖ ለመጫን መሞከር ነው።መንግስት እያደረገ ያለው ግን የራሳችሁን እምነት አትከተሉ ይመስላል።ሰዎቹ የቀራቸው ነገር ጥቅሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሰረዝ አለበት የሚል አዋጅ ማውጣት ብቻ ነው>>ብለዋል።
 ያለ በቂ ዕውቀት የሃይማኖት አክራሪነትን እዋጋለኹ  ብሎ የተነሳው መንግስት ‘አንዲት ሃይማኖት…አንዲት ጥምቀት’ የምትለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ለራሳቸው መማሪያ የሚያውሉትን ክርስቲያኖችን በሙሉ በማሳደድ ላይ ይገኛል ብሏል-ደጀ ሰላም።
 የመጽሐፍ ቅዱስን ኃይለ- ቃል እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት የሆነውን ቃለ እግዚአብሔርን መናገር፣ ማስተማርም ሆነ በጽሑፍ መያዝ ፤ሌሎች እምነቶችን እንደመዋጋት ተደርጎ እንደሚቆጠር በመናገር በፖሊሶቹ አማካይነት ጥብቅ ማዋከብና እንግልት የሚፈጽመው መንግሥት እነዚህን ስድስት ልጆች ያሰረውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን በወቅቱ በቦታው የነበሩ እማኞች ተናግረዋል።
 ድረ-ገጹ አክሎም ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩ ቀደምት መንግሥታት ሁሉ በባሰና በከፋ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ ረዥም እጁን አስገብቶ የሚያምሰው  ይህ መንግስት ፣  በቅርቡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት ላይ ሳይቀር ባለ ሥልጣኖቹን በመላክ የሲኖዶሱ ተሰብሳቢ ለመሆን በመሞከር ላይ ይገኛልም ብሏል።
 መንግሥት በአገሪቱ ቀደምት እምነቶች ላይ ያለውን አቋም ለካድሬዎቹ በተከታታይ ሥልጠና በመስጠት የሚያስጠናበት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
 ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድረስ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በሌሎች ኃላፊዎች ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና እስልምና ላይ ያነጣጠረ እንደሆነም ደጀ-ሰላም አስፍሯል።
 መንግሥት በነባር አገራዊ ቤተ እምነቶች ላይ እያስፋፋ የመጣው ጣልቃ ገብነት ድንበሩን አልፎ የእስልምና መሪዎችን በማሰር እና  የቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶስ በመዘወር መገለጡ ይታወቃል ብሏልም።
 መንግሥት ለባለሥልጣኖቹ የሚሰጠውን ሥልጠና ለማወቅ ለሚፈልጉ  ሁሉ ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ ሙሉ ዶኩመንቱን ለማቅረብ እንደሚሞክር ድረ-ገጹ ገልጿል።

No comments:

Post a Comment