Translate

Monday, January 14, 2013

ሰፈር ያሸበረ ዶሮ በፍርድ ቤት ሞት ተወሰነበት



Image-በአዲስ አበባ ከጽዮን ሆቴል ጀርባ በሚገኘው መደዴ ሰፈር ውስጥ ነዋሪውን   ያመሰ ዶሮ፤ በፍርድ ቤት ሞት ተፈረደበት።
ሸገር ራዲዮ ዶሮውን << አሸባሪ>> ብሎታል።
በጽዮን ሆቴል ጀርባ በሚገኘው መደዴ ሰፈር ወጪ ወራጁን፣አላፊ አግዳሚውን እየደበደበ ያስቸገረ ጉልበተኛ አለ የሚል ጥቆማ በደረሳቸው መሰረት ወደ ስፍራው ማቅናቸውን ነው የሸገር ጋዜጠኞች የሚናገሩት። ይህን ጉልበተኛ የደፈረችውም፤ ሰናይት የምትባል የሰፈሩ ሴት ብቻ መሆኗን የአካባቢው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ሰናይት ደፈረችው የተባለውም፤ ያሰደረሰባትን ከፍተኛ ደብድባ ተከትሎ መብቷን ለማስከበር ለፖሊስ ክስ መስርታበት በፍርድ ቤት ስላስፈረደችበት ነው።
እንደዘገባው ከሆነ ከሰፈሩ ነዋሪዎች በተጨማሪ ቆራሌ የሚሉ አነስተኛ ነጋዴዎችን የኔ ብጤዎች በተደጋጋሚ በጉልበተኛው ዶሮ ከፍ ያለ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል።

የ አካባቢው ድመቶችና ውሾች ሳይቀሩ በጉልበተኛው ዶሮ የሚደርስባቸውን ንክሻና ጥቃት አሜን ብለው ከተቀበሉም ሰንብተዋል።
ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱት የሸገር ዘጋቢዎች በቦታው ሲደርሱ በነሱም ላይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ሁኔታውን በርቀት መከታተልን እንደመረጡ ተናግረዋል።
እግሮቹ ወፋፍራምና ዓይኖቹ ድፍርስ የሆኑት ይህ ጉልበተኛ፤ ከድብድብ ብዛት ግንባሩ እና ጀርባው ላይ መቁሰሉን የጠቀሱት ዘጋቢዎቹ፤ ካሉበት ስፍራ ሆነው ሰዎች በርቀት ሲያሷያቸው- እሱም  ከጉራንጉር ውስጥ ሆኖ እንዳያቸው ጠቁመዋል።
በነሱም ጥቃት እንዳይፈጽምባቸው  ዶሮውን በ አንድ ዓይናቸው የጎሪጥ እየተከታተሉ  በሰሩት ቃለ ምልልስ፤በርካታ የአካባባው ወላጆችና ወጣቶች ሳይቀሩ በዚህ ጉልበተኛ ዶሮ መነከሳቸውን በምሬት ለጋዜጠኞቹ ተናግረዋል።
ከሰፈሩ ሰው አልፎ መንገደኞችን፤ቆራሌዎችንና የኔብጤዎችን ድንገት  ዘልሎ ትከሻቸው ላይ ድረስ እየወጣ በተደጋጋሚ ከፍ ያለ ጥቃት እንደፈጸመባቸው የተናገሩት አንዲት እናት፤ በዚህም ሳቢያ የኔብጤዎች ወደ መንደሩ መምጣታቸውን ጨርሶ እንዳቆሙ ገልጸዋል፡፡
ቃለ-ምልልስ የተደረገለት የመንደሩ ኮስታራና ጎረምሳ ወጣት በበኩሉ፦<<  …በጣም ሀርደኛ ነው፤ እኔ ራሴ እፈራዋለሁ። ፈጽሞ አይመቸኝም>> ሲል በምሬት መልክ ተናግሯል።
የመደዴ ሰፈሩ ዶሮ “ኩኩሉ ሲል ደስ ይላል፤ በጧት ይቀሰቅሰናል ተብሎ ለሰዓት ነጋሪነት እንዲሰነብት ቢደረግም ሳይታሰብ የ የአውሬነት ባህሪይ ማምጣቱ ያስገረማቸው የሰፈሩ ነዋሪዎች፤ <<ምን ታሪክ ነው?>> ሲሉ አግራሞታቸውን ገልጸዋል።
በዶሮው ከፍተኛ ጥቃት ከደረሰባቸው በርካታ ሰዎች መካከል፤ ሴት ሰናይት የተባለች የአካባቢው ነዋሪ አንዷ ነች።
ሁሉም  የደረሰባቸውን ጥቃት አሜን ብለው በቁጭትና በዝምታ ሲመለከቱት፤ሰናይት ግን <፣መብቴ በጉልበተኛ ሲገሰስ በዝምታ አላይም>> በማለት ፍርድ ቤት ገትራዋለች።
ሰናይት   ጥጋበኛው ዶሮ ላደረሰባት የሀይል ጥቃት በወረዳ 10 ፖሊስ ጣቢያ  ክስ እንደመሰረተችበትና ጉዳዩ እስከ ፍርድ ቤት እንደደረሰ የገለጹት የሰፈሩ ነዋሪዎች፤ ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ከተመለከተ በሁዋላ፦<<የገና በዓልን እንዳያልፍ>> በማለት የሞት ፍርድ ቢወስንበትም፤ የዶሮው ባለቤት ውሳኔውን ተግባራዊ ሳታደርግ ገናን እንዳሳለፈችው ተናግረዋል።
<< በፍርድ ቤት የተወሰነበት ውሳኔ ለምን ተግባራዊ አልሆነም?>> ተብለው የተጠየቁት የዶሮው ባለቤት፤ ስለ ዶሮው  እድሜና ሁኔታ ካብራሩ በሁዋላ፦<< ውሳኔውን ለመጪው ጥምቀት ተግባራዊ አደርጋለሁ፤ለጥምቀት ይታረዳል>> ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
የመንደሩ ትልቋ እማማ በበኩላቸው ለጋዜጠኞቹ ቡድን፦<<በጉዳዩ ዙሪያ ትናንት ተሰባስበን  ውይይት አድርገንበታል።  በአስቸኳይ እረዱ ብለን ተናግረናል። ወስነናል።  የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መጽናቱ የማይቀር ነገር ነው>>ብለዋል።

No comments:

Post a Comment