Translate

Monday, January 7, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ


ከእሁድ እስከ እሁድ

(ከእሁድ እስከ እሁድ)
isayas


ኢሳያስ “ተላላኪ” ሲሉ ህወሃትን ዘለፉ
በፈረንጅ የዘመን አቆጣጠር አዲስ ዓመት የተቀበለችውን ኤርትራን የሚመሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰሞኑን ባገራቸው ቴሌቪዥን በትግርኛና በአረብኛ ተሳድበዋል። የአዲስ አበባው መንግስት የሚሉትን ህወሃት፣ “ተላላኪ” ሲሉ ዘልፈውታል። ስርዓቱ በአሜሪካ ጠንካራ እንክብካቤ እድሜውን ቢያራዝምም ተቃውሞ የሚመሰረተው ውስጥ ባለው ሁኔታ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኢሳያስ፣ “የራሱን ጥቅም ብቻ በሚያስቀድመውና አገሪቱን በሚያስተዳድረው ጠባብ ቡድን፣ እንዲሁም በተቀጥላነት በሚያገለግላቸው የውጪ ሃይሎች…” አማካይነት ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ተናግረዋል።

ጠ/ሚ ቢቀያየር ትርጉም እንደሌለው ያመለከቱት ኢሳያስ፣ በሃይል የተያዘባቸው መሬት እስካልተለቀቀ ድረስ እንደማይደራደሩ አስታውቀዋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ  ላስተላለፉት የእንደራደር ጥያቄ “የጉዳዩን ምንጭ እናውቀዋለን” ካሉ በኋላ በእንዲህ ዓይነቱ ቲአትር ውስጥ ኤርትራ እንደማትገባ አስታውቀዋል። አሜሪካንና ምዕራባዊያን  አገራቸው እያስመዘገበች ያለውን ለማዳከም እየተንቀሳቀሱ መሆኑንንም አመልክተዋል። (ዜናው ከቪኦኤና ከተለያዩ ገጾች የተውጣጣ ትርጉም ነው።)
ድምጻችን ይሰማ አንድ ዓመቱን አከበረ
ድምጻችን ይሰማ በሚል እንቅስቃሴ የጀመሩት የእስልምና ተከታዮች አንድ ዓመት ሞላቸው። ይህንኑ አስመልክቶ ባለፈው አርብ ካካሄዱት የጸሎት ስርዓት በኋላ 365 ቁጥር በማሳየት ንቅናቄያቸውን የጀመሩበትን አንድ ዓመት አክብረዋል። የድምጻችን ይሰማ ጥያቄም እየሰፋ መሄዱ ታውቋል።
(ፎቶ: ከፌስቡክ)
በተለያዩ ድረገጾችና የዜና ማሰራጫዎች ይፋ የሆኑ በምስል የተደገፉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ንቅናቄው እየሰፋ ነው። የሰው ህይወትም እየበላ ይገኛል። መንግስት ጥያቄውን “ከሽብር ጋር ይያያዛል” በሚል እስርና ሃይል ቢጠቀምም ጊዜ ከመፍጀት ውጪ አለማትረፉን የሚገልጹ ወገኖች “ጉዳዩ ፈር እንዳይለቅና አሳዛኝ ውጤት እንዳይመዘገብበት ፍርሃቻ አለን” እያሉ ነው። ጉዳዩ ወደ አሳሳቢ ደረጃ ሊያመራ እንደሚችል የውጪ ሚዲያዎችም እየዘገቡ ነው።
ቀይ መስቀል ቤት የፈረሰባቸውን እንዳይረዱ ተከለከሉ
ቀይ መስቀል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤት የፈረሰባቸውን ወገኖች እንዳይረዳ መከልከሉን ቪኦኤ ዘግቧል። ከአዲስ አበባ የቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጸሃፊ አስተባብለዋል። ቪኦኤ የሰብአዊ መብት ጉባኤ ዳይሬክተርን አቶ እንዳልካቸው ሞላን ጠቅሶና በቃል አሰምቶ እንደዘገበው ቀይ መስቀልን ጨምሮ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ተፈናቃይ ወገኖቻቸውን እንዳይረዱ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። በተለይ የቀይ መስቀል ኦፊሰሮች ጉዳዩን ለሰመጉ በቃል አሳውቀዋል ብለዋል። ተፈናቃዮቹ ህጻናት ይዘው በላስቲክ ቤት፣ በድንኳን፣ ሜዳ ላይ ፈሰዋል። እነዚህን መርዳት የርዳታ ድርጅቶች ቀዳሚ ኣለማ ነው በማለት ተናግረዋል።
የቀይ መስቀል ጸሃፊ አቶ ኤልያስ አያና በበኩላቸው “ርዳታ እንዳናደርግ ማንም አልከለከለንም” ካሉ በኋላ ችግሩ ተረጂዎቹ ከሚኖሩበት ቀበሌ በትክክል ተጎጂ ስለመሆናቸውና፣ የሚያስፈልጋቸውን ርዳታ በመዘርዘር ከቀበሌያቸውና ህጋዊ ከሆነ ተቋም ደብዳቤ አለማቅረባቸው መሆኑን ያወሳሉ። አፈናቃዩ ቀበሌ፣ ቤት አፍራሹ ቀበሌ፣ ፖሊስና አመራሩ ሁሉም ኢህአዴግ ናቸው። ሰዎቹ ህጻናትን ይዘው ሜዳ ላይ ፈሰው ምን ደብዳቤ ያስፈልጋል? ሁሉም ሰው የሚያቀርበው መከራከሪያ ነው፡፡
የሻሸመኔዋ ነብሰ በላ ታዳጊ ብትገደልስ?”
በሻሸመኔ አስገራሚ የተባለ ዜና ተሰምቷል። አንድ ያስራ አምስት ታዳጊ ለአንድ ወር ተኩል ተቀጥራ በምትሰራበት ቤት ውስጥ አባት ሲቀር ሙሉ ቤተሰብ ህይወት ባሰቃቂ ሁኔታ አጥፍታለች። በፖሊስ ፕሮግራም የቀረበችው ታዳጊ ፍርድ ቤት ውስጥ “… ፈቃድ ከለከለችኝ፣ መታችኝ። ሁሉም ስራ ሲሄዱ ኩሽና ሄጄ መጥረቢያ አመጣሁና ልጆቹን በየተራ…” በማለት አይኗን እያጉረጠረጠች  ስትናገር ታይታለች።
የሶስት ዓመትና ሰባት ዓመት ህጻናትን ገድላ ከደበቀች በኋላ እናት ከስራ ስትመለስ ተመሳሳይ ርምጃ ወስዳ የተሰወረችው ታዳጊ ሞባይል፣ ሃምሳ ብርና ሽቶ ወስዳም ነበር። ፖሊስ አፈላልጎ የያዛት ወንጀለኛ መገደል አለባት የሚል ተቃውሞ ቢቀርብም፣ እድሜዋንና ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ወንጀሉን ሳትክድ በማመኗ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንደተፈረደባት ይፋ ተደርጓል። እባካችሁ ወላጆች የጊዜያዊ ጸብ መጨረሻ አይታወቅምና ከሰራተኞቻችሁ ጋር የሚኖራችሁን ግንኙነት በጥንቃቄ አድርጉት የጎልጉል መልክት ነው።
ከሆድ ጥያቄ ወደ ብሄር ግጭት ያደገው ጸብ
(ፎቶ: ሪፖርተር)
በአራት ኪሎ ተነሳ የተባለውና ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ያረገበው ብጥብጥ መነሻው የብሄረሰብን ስም የሚያጎድፍ ጽሁፍ በግቢው ውስጥ በመገኘቱ ሳቢያ ነው። በዚሁ የተነሳ ጎራ ለይተው ከተቧቀሱት መካከል 74 ከኦሮሞ፣ 21 ከአማራ፣ 10 ከትግሬ፣ ከደቡብ 8 በድምሩ 113 የሚሆኑ ተማሪዎች መታሰራቸውን ገዳ ዶት ኮም ዘግቧል። ድረ ገጹ በጃንዋሪ 5 20013 “የተማሪዎች አመጽ እንደቀጠለ ነው” በማለት እንዳስታወቀው፣ ሰባት ክፉኛ የተጎዱ ሲሆን ገመቹ የሚባል ተማሪ ህይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው ብሏል።
የእሁድ ሪፖርተር በበኩሉ የታሰሩ ተማሪዎችን ቁጥር ባይገልጽም ቀደም ብሎ ገዳ ዶት ኮም ከዘገበው ጋር የሚመሳሰል ዜና አስነብቧል። ሁለት ተማሪዎች የቀዶ ጥገና እርዳታ እንደተደረገላቸው የገለጸው ሪፖርተር ጉዳቱ የደረሰው ተማሪዎቹ ቡድን ለይተው በዱላና በድንጋይ በመከሳከሳቸው ነው። በፖሊስ ጣልቃ ገብነት የበረደው ጸብ የዩኒቨርስቲዎችን ረብሻ አንድ ደረጃ ያሳደገው ነው የሚል አስተያየት እየተሰጠው ነው።  ከደረሱን አስተያየቶች መካከል “የዩኒቨርስቲዎቻችን ጥያቄ ከቂንጬ፣ ሩዝ፣ ዳቦና ሾርባ ከፍ በማለት ወደ ብሄር ግጭት ከፍ አለ” የሚለው ይገኛል።
ስብሃት ለኦርቶዶክስ “ሰጋሁ” ይላሉ
በቀናት ልዩነት ኢሳት አጋልጧቸዋል
አቶ ስብሃት ነጋ ሰሞኑን ለሰንደቅ ሳምንታዊ ጋዜጣ የሰጡት ቃለ ምልልስ አነጋጋሪ ሆኗል። አስተያየት እንዲሰጡ ከተጠየቁባቸው ጉዳዮች መካከል ስለ እምነት ጣልቃ ገብነት ተጠይቀው ከዚህ የሚከተለውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ባሉ በቀናት ልዩነት ውስጥ ኢሳት አቶ ስብሃት በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በትግርኛ መመሪያ ሲሰጡ እንደነበር ድምጻቸውን በማሳማት አጋልጧቸዋል። እንዲህ ነበር ያሉት፡-
“…የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም እንኳ የመንግስት ጥገኛ ሆኖ በመቆየቱ እጅግ ቢጎዳም በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የነበረው ሚና መተኪያ የለውም። ከመንግስት ይለይ፣ ከፖለቲካ ነፃ ይውጣ ቢባልም አሁንም ከፖለቲካ መድረክነቱ ሊወጣ አልቻለም። የእምነቱ አመራርም ቢሆን የአማኙን መንፈሳዊ ህይወት ሊያረካ አልቻለም። ከዚህ አልፎም አሁን ባለው ሁኔታ ሳይረባበሽ እንደማይቀር ነው የሚገመተው። ለሁለት ተከፋፍለዋል። ይህን መሰል አደጋ ቤተክርስቲያኒቱ አጋጥሞት አያውቅም። ቤተክርስቲያኒቱ ለሁለት የከፈለው ውጭ ያለው ፓትሪያርክ የሚያራምዱት እንቅስቃሴ መሆኑ በስፋት ይታመናል። ይህ አልበቃ ብሎ የአሜሪካው ሲኖዶስ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደግፍ ይወራል። አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስም የቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ቆርቁሮት ተነስቶ ይህን ድርጊት አላወገዘም። የእስልምና አክራሪነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ደጋፊ ከሆነም መንግስት እርምጃ መውሰድ ነበረበት። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትኩረት ካልሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርዓቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቧል…”
አነጋጋሪው አዋጅ ጸደቀ
በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የተዘጋጀ አዋጅ ጸደቀ። አዋጁ አገራችን በዓለም ገበያ ውስጥ የምታደርገውን የንግድ የኢንቨስትመንትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿን የበለጠ የተሳኩ እንዲሆኑ እንቅፋቶችን በመቀነስና በማስወገድ፥ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ድርሻ አለው የሚል ማብራሪያ ቀርቦበታል።
በምክር ቤቱ ውስጥ ብቸኛው የመድረክ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ አዋጁ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሰፊ ውይይት ያልተካሄደበትና ማካተት ያለበትን ነጥቦች በሚገባ ያላሟላ እንደሆነ በመጠቆም ነቅፈውታል። አዋጁ መንግስት አፈናን ለማስፋፋትና አሸባሪን ለመርዳት በሚል ክስ ለመመስረትና ንብረት ለመውረስ ያለውን ዝግጅት የሚያሳይ እንደሆነ አስተያየት ተሰጥቶበታል። አዋጁ ኢህአዴግ ነኝ የሚሉትን የግል ተወዳዳሪ ጨምሮ በሙሉ ድምጽ ሲጸድቅ የተቃወሙት አቶ ግርማ ብቻ ናቸው። አዋጁ በጥድፊያ መጽደቁ አነጋጋሪ ከመሆኑም በላይ ስጋትም ፈጥሯል። (ዘገባው የፋና ብሮድካስቲንግ ነው።)
ሃያ አመት በእስር ያሳለፉት ኮሎኔል ደበላ አረፉ
ሃያ ዓመታትን በወህኒ ቤት ያሳለፉት ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ አርፈዋል። ወለጋ ጊምቢ በ1933 ዓ ም የተወለዱት ደበላ ዲንሳ ሰባት ልጆችና፣ ዘጠኝ የልጅ ልጆች አይተዋል። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ደበላ ዲንሳ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ የአብዮትና ዘመቻ አስተባባሪ ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት ቀይ ሽብር እንዲቆም የጠየቁ ስለመሆናቸው በቅርብ የሚያውቋቸው በህይወት እያሉ መስክረውላቸዋል።
በፖሊስ መኮንንነት የተለያዩ ሃላፊነት የነበራቸውና ከደርግ ጋር ወደ ስልጣን የመጡት ደበላ ጃንሆይ ስልጣን እንዲለቁ ሲጠየቁ ቤተመንግስት ተገኝተው ደብዳቤ አንብበዋል። መዝናናት እንደሚወዱ፣ ቀልደኛ እንደሆኑና ንግግራቸው ለዛ እንዳለው በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ  በልብ ህመም 73 ዓመት ኖረው ያለፉት ታህሳስ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ነው። (ምንጭ፡ ቋጠሮ)


No comments:

Post a Comment