Translate

Tuesday, January 8, 2013

መገደብ የማይችል ሕዝባዊ እምቢተኛነት በኢትዮጵያ


ዳኛቸው ቢያድግልኝ
Tigray People Front, TPLFትግራይ ተገንጣይ ቡድን እንደ መንግስት የመቆም አቅሙ ከእለት ወደ እለት እየተፍረከረከ መሄድም መዳህም አቅቶት ሲንገታገት እያየነው ነው። እንደ ፓርቲ ተሰነጣጥቆአል፣ እንደ መንግስት አርጅቶአል፣ እንደተገንጣይ ቡድንም ክህደቱን የትግራይ ሕዝብ አውቆበታል። የገንጣዩ ቡድን መሪዎችም አንዳንዶቹ ሞት ቀንሶአቸዋል፣ አንዳንዶቹ ጃጅተዋል፣ ጥቂቶቹም ታማሚ ሲሆኑ  ሌሎቹም ንቃት መለስ አድርጎአቸዋል። በአሮጌ ጨርቅ እንደተቋጠረ የበሶ ዱቄታቸው በየአቅጣጫው የሚያፈተልኩባቸው ጎጠኛ ሰራሽ ፓርቲዎቻቸውም አስተማማኝ አሽከር እንደማይሆኑ እያሳዩ ነው። ኦህዴድ ቀልዳችሁን አቁሙ ብሎ በድፍረት ሽቅብ ማየት ጀምሮአል። የበረከት ሰዎችም አማራነትን ለኛ ተውልን እያሉት ነው። እናም አደጋው ከምንጊዜውም የከፋ ይመስላል። ትግራይ በቀል ‘አረና ትግራይ’ በትግራይ ተገንጣዮች እየተደበደበ ነው። ዱላው እመንደሩ ድረስ ስለዘለቀ ክፋቱ ገፍቶ መጥቶአል።

ወይዘሮ አዜብ በመለስ ራዕይ ሊሸብቡት ባሌ ከመሰዋቱ በፊት የአምስት አመት ስትራቴጂ ለትግራይ እየሰራ ነበር የሚል ላሞኛችሁ አይነት ንግግር ለትግራይ ሕዝብ አሰምተዋል። መለስ የዋሸውን ያህል አሁን  የለም ብለው በስሙ ሁሉም ይዋሻሉ። መለስ ብቻውን የሚነድፈው የአምስት አመት ስትራቴጂ ሊኖር አይችልም። ካለ ደግሞ ጭፍን፣ ራሱን ብቻ አዋቂ የሚያደርግ በሌሎች ላይ እምነት ያልነበረው ብቸኛ ሰው ነበር ብለው መመስከራቸው ነው። ይህ አባባላቸው እንዲያውም ጥላቻን የሚያስፋፋና ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይበልጥ ይህንን ስርዓት እንዲታገለው ማበረታቻ ነው ያደረጉት። እሳቸው በተናገሩ መጠን የበለጠ ወያኔን ራቁቱን ያቆሙታል። ምክንያቱም በትግራይ ሕዝብ ስም የሚዘረፈው የሀገር ሀብት የአቶ መለስና ቤተሰባቸው እንዲሁም ጥቂት አጋሮቻቸው እንጂ የትግራይ ሕዝብ ሀብት ሆኖ አያውቅም። የሕዝብ ሀብት ከራሱ ከሕዝቡ ተደብቆ የሚከማች አይደለምና። ለዚሀም ነው አረና ትግራይና ሌሎች ተቃዋሚዎች በራሳቸው መንደር የጥቃት ሰለባ የሆኑት። ቢሮአቸው በቡልዶዘር እየፈረሰ አባላቶቻቸው እየታሰሩ ያሉትና በትግራይም ነጻነት ያለመኖሩን ያረጋግጣል። ይህ ማለት ለዘመናት የታፈነውና የተቀጠቀጠው ትግራይም የነርሱ ዋሻ ሊሆን እንደማይችል ነው። ስለዚህ መሰረታችን ነው በሚሉት ትግራይ ውስጥም ሕዝባዊ አመጽ ይነሳል። የፈለገውን አይነት ትጥቅና ስንቅ ትግራይን አስገንጥሎ ሀገር አያደርጋትም። እናም በትግራይ ተገንጣይ ቡድን የማይገደብ ሕዝባዊ አመጽ በግዱ ይነሳል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ያሰሙን ዜና እጅግ የሚያስደስት ነው። ሀገራቸው የነርሱ ናትና ለነገው ቤታቸው ዛሬን የቤት ሥራቸውን መስራት አለባቸው። በመሆኑም ሀገር አቀፍ የሆነ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የሚካተት ታጋይ ድርጅት መፍጠር መቻላቸውን ሲያበስሩ መስማት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው። አዎን ኢትዮጵያቸውን ዛሬ ካልታደጉ ነገ ሀገር አይኖራቸውም ወይም የሀብታም ጎጠኞች አገልጋይ ይሆናሉ ሰግደው እስከተገዙ ድረስ። ስለዚህ በተለያዩ ክፋላተሀገራት እንደመበተናቸው መጠን ግብታዊ ሳይሆን ሚዛናዊ፣ ስሜታዊ ብቻም ሳይሆን እውቀትና ብልህነትም የታከለበት ትግላቸውን ተጠናክረው ይቀጥሉበታል ብለን እናምናለን። የወያኔን የጎጥ ጸብ አጫሪነት ተሻግረው ኢትዮጵያን ለማዳን ይህ አይነቱ የወጣቶች ሀገራዊ መነሳሳት መገደብ የማይችል የሕዝባዊ አመጽ ምልክት ነውና አሸናፊነቱን መጠራጠር ከቶውን አይቻልም።
የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ሲያቀርቡ የነበረው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ያልቻለው ያለው መንግስት ለዚህ የተዘጋጀ ባለመሆኑና ያገኘው ሕዝባዊ ስብስብ ውስጥ የሀይማኖት ጓዳ ድረስ ዘልቆ አፈና ማኪያሄድ በመሆኑ ነው። ጥያቄያቸው አንድ ደረጃ ወደላይ አድጎ ማስተዳደር ያልቻለ መንግስት ይወገድ ወደሚለው ሀገራዊ መፈክር ማደጉም የሚያመለክተው የትግራይ ተገንጣይ ቡድን ካፍንጫው ራቅ አድርጎ ማሰብ ባለመቻሉ የራሱን መቃብር በጥፍሩ ቆፍሮ የጨረሰ መሆኑን ነው። በወሎ የተደረገው ጭፍጭፋና ድብደባ፣ በአርሲ የተደረገው፣ በሐረር እየሆነ ያለው በሁሉም ሰው አይን ውስጥ ገብቶአልና ቁጣው ወደ ሕዝባዊ አመጽ ይቀየራል! ይህ አያጠራጥርም። ፌዴራል ፖሊሶች የጎጠኞች መሳርያ የመሆናቸውን ያህል አንድ ክፉ ቀን እንደ ደቡቡ አፍሪካ ነጭ ለባሾች ጎማ ባንገታቸው እያጠለቁ የሚያቃጥሉዋቸው ሰዎች እንዲነሱባቸው ማድረግ ይመጣልና ከወዲሁ ሊያስቡበት ይገባል። የቅንጅትን መሪዎችን በማሰር ትግሉን እንዳጨናገፉ ሁሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን መሪዎች በማሰር ስኬትን አገኛለሁ ማለት የሞኝ መንገድ መሆኑ እየተመሰከረ ነው።  ማወቅ የሚያስፈልገው ነገር ይህ ሁሉ በደል የበዛበት ሕዝብ ያለው ኃይል ታላቅ መሆኑንና ይህ ሕዝባዊ አመጽ ተጠናክሮ ሊቀጥልና አሳሪዎችን ታሳሪ ሊያደርግ የሚችል አቅም ላይ መድረሱን ነው። ይህንን ነው መገደብ የማይቻል ሕዝባዊ እምቢተኛነት ማለት የሚቻለው።
የክርስትና በተለይም የኦርቶዶክሱ ቤተክርስትያን የጎጠኞች ሰለባ ሆኖ በዚህም በዚያም ጥቃት ሲፈጸምበት መኖሩ ይታወቃል። አሁን ባለቀ ሰዓት እንኳን አስታራቂዎች ላይ የደረሰው በደልና ግፍ የሚያመለክተው ነገር ቢኖር ቤተክርስትያኑ በትግራይ ተገንጣይ ማፊያዎች እንደታገተ ነው። ስለዚህ ሕዝበ ክርስትያኑ ያለውን ሁኔታ በሚገባ ሊረዳው እንደሚችል ነው። ይልቁንም መረጃ በቀላሉ ወደ ሀገር ቤት እየገባ በመሆኑ ከማንም የተደበቀ አይደለምና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ለማዳከም፣ ለመበታተን ይልቁንም ሀገር አቀፍ ጉልበት እንዳላቸው በማመን ያንን ለማፍረስ የሚደረገው ክፋት እየተጋለጠ ነው። ከእስልምና ተከታዮች የበለጠ በቤተክህነቱ ላይ ዘረፋ በመኪያሄዱ ያንን ለማፈን የሚደረገው ርብርቦሽ እየተዳከመና ለመዕመናኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ይህም የግድ ሕዝባዊ አመጽ የሚያነሳሳ ነውና በየአቅጣጫው ቋጠሮ የሚፈታበት ቡድን ልብ ሊለው የቻለ አይመስልም። ቢልም የማቆም አንዳች ኃይል የለውም።
የወያኔ ሰራዊት እየተፈታ ነው። ሰራዊቱ እየካደ ጥሎ እየጠፋ ነው። ጠፍቶ ወዴት እንደሚሄድም ግልጽ ነው፣ በጣም ግልጽ ነው። ሕዝባዊ ኃይል መቀላቀል መጀመሩን ራሳቸው የጎጠኛው ጦር አዛዦች እየተናገሩ ነው። በሰራዊቱ መካከል ያለመግባባት መኖሩንም ግልጽ የሚያደርገው በቡሬ ግንባር የሆነው ነው። በተለያዩ አካባቢዎች እስረኞችን ማስፈታት፣ ፈንጂ መቅበርና የመሳሰሉት ሕዝባዊ ቁጣዎች የየቀን ዜና መሆን ጀምረዋል። ይህ በዚህ ከቀጠለ በሌሎችም ክፍላተ ሀገራት በቅርቡ የምንሰማው ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ሕዝባዊ እምቢተኛነት ሲቀጣጠል መያዣ መጨበጫ ያጥራል።
ከሰሞኑ ግንቦት ሰባት ሕዝባዊ ኃይል የሚል ድርጅት ራሱን ይፋ አድርጎአል። በሰራዊቱ ውስጥም በሚስጥር የተደራጀ ኃይል ስለመኖሩ ሰምተናል። ይህ የወያኔን ማፈኛ መንገድ እንደ አሮጌ መቋጠርያ በየቦታው የሚቀዳድደው ነውና ታላቅ ሕዝባዊ አመጽ መነሳቱ ያለ ጥርጥር እየታየ ነው። የአርበኞች ግንባር ብሎ ራሱን የሚጠራው ኃይልም እስረኞች ማስፈታትና በጎጠኞች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደቀጠለ ነው።
ይህንን ሕዝባዊ አመጽ ማገትና ማቆም የሚቻል ነገር አይሆንም። የሚከተለውን አደጋና እልቂት ለመቀነስ ግን አሁንም ጊዜ አለ። ይህንን ዘረኛነት፣ ጎጠኛነትና እብሪት አጥፍቶ ለሁሉም እኩል የሆነች ሀገር ለመመስረት ለብሄራዊ እርቅ መዘጋጀት ከብዙ ጥፋት ያቅባል። እብሪት ላይ የተመሰረተ በራስ መተማመን ግን አምባገነኖችን ይዞ እንደሚጠፋ ሰደድ እሳት ነው። በአንድ ጀንበር የሚጠፋም ስልጣን መሆኑን ከታሪክ ያለመማር የውድቀትመደምደሚያ ነው። መገደብ የማይችል ሕዝባዊ እምቢተኛነት በኢትዮጵያ እየተቀጣጠለ ነው።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ሕዝብዋን ይባርክ!!

No comments:

Post a Comment