Translate

Monday, January 14, 2013

ከእሁድ እስከ እሁድ


(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)

lalibelaየላሊበላ ቅርስ አደጋ ላይ ነው
ታሪካዊና የኢትዮጵያ የጥንት የስልጣኔ አሻራ ምስክር የሆኑት ውድ የላሊበላ ውቅር አቢያተክርስቲያናትና ቅርሶች በመፈራረስ  ላይ መሆናቸው በተደጋጋሚ መጠቀሱ ይታወቃል። መንግስትም በተደጋጋሚ ቅርሶቹን ለማደስ እንደሚሰራ ማስታወቁም አይዘነጋም። በሳምንቱ መጨረሻ በስፍራው የተገኙ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ስጋት አለን። ቅርሶቹ በመፈራረስ ላይ ናቸው” ሲሉ በመንግስት ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናትና ውድ ቅርሶች የመፍረስ አደጋ እንደከበባቸው ቢገለጽም ምላሽ አለማግኘቱ አነጋጋሪ ሆኗል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነና የመንግስት ቴሌቪዥን ይፋ እንዳደረገው ታሪካዊዎቹ የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫዎች የሚፈለጉት ለቱሪዝም ገቢ ብቻ ነው። በዓመት እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ ቱሪስቶች ይጎበኟቸዋል። ከመቶ ሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስገባሉ።  ይህ ገንዘብ ብቻ በያመቱ ለቅርሶቹ እድሳት ቢውል እንደዚህ ላለ ታሪክን ሊያሳጣ የሚያደርስ አሳሳቢ አደጋ ላይ አይደረስም ነበር። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።
ለብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የዲፕሎማሲ ስልጠና ተሰጠ   
ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቴክኒክ ስልጠና በተጨማሪ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስልጠና እንደተጠተው በሸራተን አዲስ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ተጠቁሟል። የመንግስት መገናኛዎች ተቀባብለው እንደዘገቡት የአባይ ግድብ የብሄራዊ ተሳትፎ አስተባባሪ በስልጠናው ላይ ተጨዋቾቹ ስለ አባይ ግድብ በማስተዋወቅና በመናገርየአገራቸው አምባሳደሮች እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን “ግንዛቤ አስጨብጠዋል”፡፡
ተጨዋቾቹ በሚያገኙት አጋጣሚ በአገራቸው እየተካሄደ ስላለው ልማትና ስለ አባይ ግድብ ለሌሎች በማስተዋወቅ ከመጫወት በተጨማሪ የህዝብ ግንኙነት ስራ እንዲሰሩ አደራ ተሰጥቷቸዋል። አንድ ቀልደኛ የጎልጉል ሰው ኢትዮጵያ ሁለት ለባዶ ስትመራ ቆይታ ሁለት ለሁለት ጨዋታው ተጠናቆ ጎሎቹን ያገባው ተጨዋች ጋዜጣዊ መግለጫ ስጥ ቢባል “በምሳሌ አስረዳለሁ። አንድ ሁለት መቶ ብር የነበረው ሰው አንድ መቶብር ለአባይ ግድብ፣ አንድ መቶ ብር ለአዲስ ራዕይ ግዢ ቢያውል ምን ይተርፈዋል? ምንም። ስለዚህ ውጤቱ እንዲሁ ይመስላል” በማለት ልማቱንና ውጤቱን በማያያዝ ሊመልስ እንደሚችል ተናግሯል። በነገራችን ላይ የተለያዩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 20 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የጉዞ ኢንሹራንስ ገዝተዋል።
በጣና ሃይቅ ግድያ የፈጸሙ ተያዙ
ፖሊስ ተራ ሌቦች ናቸው ብሏል
ባለፈው ሳምንት በመዝናናት ላይ ከነበሩ ቱሪስቶች መካከል አንዱን ተኩሰው ገድለዋል የተባሉት ሶስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታውቋል። ኮማንደር እርቅ ይሁን ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ወንጀሉን ፈጽመዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች የተያዙት በ48 ሰዓታት ውስጥ ነው። ለጊዜው ያመለጡት ሁለት ተፈላጊዎች ህዝብና የጸጥታ ሃይሉ በረሃ ገብተው እያሰሱዋቸው ስለሆነ በርግጠኛነት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ኮማንደሩ ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር በበኩላቸው ድርጊቱን ለጊዜያዊ ጥቅም የተፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል። የክልሉን ገጽታ እንደማያበላሽ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የተቀሩትን ባስቸኳይ በቁጥጥር ስር በማዋል አስፈላጊው የህግ ውሳኔ ተሰጥቶበት ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን አስታውቀዋል። ተጠርጣሪዎቹ ሲያዙ በጃቸው ላይ 5,700 የኢትዮጵያ ብር፣ 150 ዩሮና ፓስፖርትና ተይዞባቸዋል።
አበበ ገላው ማለት “እኛ ነን
አበበ ገላውና ሲሳይ አጌና
በጋዜጠኛ አበበ ገላውን ለመግደል በዝግጅት ላይ የነበሩ ቅጥረኞች የተሰጣቸውን የቤት ስራ ሳያከናውኑ እንደተደረሰባቸው መገለጹን ተከትሎ ጉዳዩ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ሰንብቷል። ኢሳት በሰበር ዜና በአሜሪካ ሀገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆ የሚኖረውና የህወሃት ሰላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚታመን በስም ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ይኽው ግለሰብ ጋዜጠኛ አበበን ለመግደል ሶስት የወንጀሉ ተባባሪ የሚሆኑ ግለሰቦችን መመልመሉ ተደርሶበታል። የግድያውን ሴራ የFBI መሪማሪዎች ደርሰውበት እንዳከሸፉት የተነገረለት ይህ ከፍተኛ የወንጀል ድራማ በአገርቤትና በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን አስቆጥቷል።
ጋዜጠኛ አበበ ገላውን በመደገፍና በማበረታታት በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በርካታ ጽሁፎች የተበተኑ ሲሆን “አበበ ማለት እኛ ነን” የሚል ይገኝበታል። የግድያ ሙከራውን በማውገዝ ሞረሽ የሚባለው የአማራ ተቆርቋሪ ነኝ የሚለው ማህበር  ድርጊቱ “በአማራ ነገድ ላይ ያነጣጠረ ነው” በማለት ያወጣውን መግለጫ አበበ እንዳልወደደው አስታውቋል። አበበ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ወደ አንድ ብሔር የመጠጋጋት ጉዳይ አጀንዳው እንዳልሆነ በይፋ የገለጸበት ጽሁፍ በተለያዩ ድረገጾች ተላልፏል። FBI ደርሶበት አከሸፈው ስለተባለው የግድያ ሙከራ ከህወሃትም ሆነ፣ ህወሃት ከሚመራው ኢህአዴግ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ከጅቡቲና ከጎዴ ቅድሚያ ለማን
በሶማሌ ክልል የጎዴ ከተማ የመብራት አገልግሎት የምታገኘው ከጄኔሬተር መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አስታውቀዋል። ከንቲባው እንዳሉት በከተማዋ ያለው የኤሌትሪክ ችግር እንዲቀረፍ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች እየጠየቁ ነው። ስለከተማዋ ልማት በኢቲቪ የዜና እወጃ ላይ ቀርበው የተናገሩት ከንቲባው የመስመር ዝርጋታው በቅርቡ ጎዴ ይደርሳል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል መሸጥ መጀመሯ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በክልሉ በተከሰተ ረሃብ ከብቶቻቸው የሞቱባቸው፣ ግመሎቻቸውን ያጡና በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱት አርብቶአደር የጎዴ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲችሉ በተደረገው ጥረት የኮብል ድንጋይ ማዘጋጀት ጀምረዋል። በኮብል ድንጋይ የሚሰራ መንገድ በመስራት ገቢያቸውን አሳድገዋል። ይህ ጅምር ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባው አስታውቀዋል።
ዓለም ባንክ ቴሌን ዳር ዳር እያለው ነው!
የዓለም ባንክ ባለፈው ዓርብ ይፋ ባደረገው ጥናት የቴሌኮም ዘርፉ ለከፍተኛ ሙስና አደጋ የተጋለጠ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ በተለይ በግዥና በአቅርቦት ሒደቶች የሚታዩት ክፍተቶች ለሙስና አደጋ በመጋለጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል ተብሏል፡፡
መንግሥት ከባንኩ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የባንኩ አጥኚ ቡድን የአገሪቱን የሙስና መጠን ለስድስት ወራት ያህል ሲያጠና ቆይቷል፡፡ ጥናቱ የተካሄደባቸው ስምንት ዋና ዋና ዘርፎች ሲሆኑ፣ በአብዛኞቹ ዘርፎች ላይ የሙስና መንሰራፋት ያን ያህል አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ አይደለም ብሏል፡፡ ሆኖም ጥናቱ “አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች” ብሎ በመደባቸው ንዑሳን ክፍሎች ውስጥ የተካተቱት ቴሌኮም፣ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና ሕክምና እንዲሁም የመድኃኒት ዘርፉ በሙስና ቀለበት ውስጥ የወደቁ መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
ጥናቱ በአጠቃላይ የአገሪቱን ስምንት ዋና ዋና ዘርፎች በሦስት ክፍሎች መድቧቸዋል፡፡ “የመሠረታዊ አገልግሎት ሰጭ ዘርፎች”፣ “አሮጌዎቹ ዘርፎች”፣ እንዲሁም “አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች” በማለት የመደባቸው ሲሆን፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ የተካተቱት፣ ከፍተኛ ፈንድ የሚጎርፍላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ከሌሎቹ ዘርፎች አኳያ በአገሪቱ ያላቸው ተሞክሮ አነስተኛ ሆኖ የሚገኙ ናቸው፡፡
በመሠረታዊ የአገልግሎት ሰጭ ዘርፍ ውስጥ የተካተቱት እንደጤና፣ ትምህርት፣ ፍትሕና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በአሮጌው ዘርፍ ውስጥ ደግሞ እንደ ማዕድን፣ ኮንስትራክሽን፣ መሬትና ሌሎችም ተደልድለዋል፡፡
የባንኩ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት፣ በመሠረታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማቱም ሆነ በአሮጌዎቹ ዘንድ የሚታየው የሙስና ደረጃ ያን ያህል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ በዘርፎቹ የሚታየው የሙስና መጠን እያደገ ቢመጣም፣ ህልውናቸውን እንደማይፈታተነው ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በተለይ የመሠረታዊ አገልግሎት ዘርፉ ከሌሎቹ አኳያ ለሙስና ያለው ተጋላጭነት አነስተኛ ሆኖ ይታያል፡፡
ከዚህ ይልቅ አሮጌዎቹ ዘርፎች ለሙስና ያላቸው አስተዋጽኦ ከአዳዲሶቹ ቀጥሎ ያስቀምጣቸዋል፡፡ በተለይ የቴሌኮም ዘርፉን በመከተል መሬትና ኮንስትራክሽን በሙስና አደጋ ውስጥ ቢገኙም፣ የትኞቹም የቴሌኮም ዘርፉን ያህል ግን አይደሉም፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት “ቴሌን ደህና ሰንብት?” በሚል ርዕስ ባወጣነው ዜና ላይ ቴሌ የአውሮጳውያንን ኩባንያዎች ማግለሉና በሙስና የተዘፈቀ ድርጅት መሆኑ ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ (ከላይ የተጠናቀረውን ዜና በቀጥታ የወሰድነው ከሪፖርተር ነው)

No comments:

Post a Comment