Translate

Saturday, January 26, 2013

ብስጭት በጨዋታ “…ቡርኪናፋሶ አበዛብኝ ለቅሶ!”


ብስጭት በጨዋታ “…ቡርኪናፋሶ አበዛብኝ ለቅሶ!”

ABE TOKCHAW
እንደምን አደራችሁ ብስጭት እናስነብባለን በመጀመሪያም አርዕስተ ብስጭት።
በትላንትናው ዕለት ብሄራዊ ቡድናችን ላይ በደረሰበት መጠነ ሰፊ ጥቃት በርካቶች መበሳጨታቸው ተሰማ።
በቅድሚያ፤
ብሄራዊ ቡድናችን፤ በደቡብ አፍሪካ ያለ ኮከብ በሚያበራው የኢትዮጵያ ባንዲራ፤ በባለ አንበሳው ሞአንበሳ ባንዲራ በባለኮከቡ የፌደራሉ ባንዲራ እንዲሁም በባለ ዋርካው የኦነግ ባንዲራ ምን እርሱ ብቻ በባለ ቀንበጡ የኤርትራ ባንዲራ ሁሉ ሲደገፍ ተመልክተን እማማ ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች እንዳሏት አየን ደስም አለን!

የብስጭቱ ዝርዝር ቀጥሎ ይቀርባል፤
ጨዋታው እንደተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ ማራኪ ጨዋታዎችን አድርጎ የነበረው ብሄራዊ ቡድናችን በሽመልስ አማካይነት የተሞከረችው የጎል አጋጣሚ ለጥቂት በጣም ለጥቂት በግቡ ቋሚ አማካይነት መከነች። እንዴት ነው ነገሩ የግቡ ቋሚ የቡርኪናፋሶ ረዳት በረኛ ነው እንዴ ብለን በጣም ተበሳጨን! እርርር..ም አልን።
እያለ እያለ አንድ ጎል ገባብን አንድ የቡርኪናፋሶ ተጫዋች ኦፍሳይት ክልል ውስጥ ነበር። ምናልባት እርሱ አዘናግቷቸው ይሆን…? ብለን አሁንም ተበሳጨን። ትንሽ ቆይቶ አሉን ከምንላቸው ተጨዋቾች ውስጥ አዳነ ግርማ ከአንዱ የቡርኪናፋሶ ተጫዋች ጋር ተጋጭቶ ሲወድቅ አየነው። ሲገጭ ያየነው እግሩ አካባቢ ነው። አዳነ ግን የያዘው ብሽሽቱን ነበር። እንዴት ነው ነገሩ ሰዎቹ እግር ገጭተው ብሽሽት የሚያሳምሙት…? የአዴ ስልት ነው… ወይስ ህመም በእግር “ሜሴጅ” ያደርጋሉ። ብለን እየተጨነቅን ሳለ አዴ ህመሙ በረታበትና ከሜዳ ወጣ። ኤርሚ  እንደዘገበልን፤ አዳነ የታመመው እግሩን ከተገቢው በላይ ከፍ በማድረጉ አማካይነት የሚመጣ የጡንቻ መሳሳብ ነው። ይህ ህመም ለሚቀጥሉት አስር ቀናት ከሜዳ ያርቃል። ተበሳጨን አይገልፀውም፤ “ኦ…. ብስጭት ሆይ እንዲህ ደጋግመሽ የምትጎበኝን አንቺ የቤተሰባችን አባል ነሽን!?” አልን።
ከዛ በኋላማ አዳነ አለቀሰ ተመልካቹ አለቀሰ ጎሉም አልቀነሰ። እየወሰዱ ብቻ ጎል…! አረ የከልካይ ያለ። አረ የተከላካይ ያለ! ያ “አጭበርባሪ” በረኛቸው በቀይ ሲወጣ “ችርስ” ብለን እጃችንን አጋጭተን የነበርን ሁላ ዝም ብሎ ብቻ ጎል ሲቆጠርብን፤ መቁጠሩ ደከመንና “የወጣው በረኛ የእኛ ነው እንዴ!” ብለን አሁንም ተበሳጨን ተበሳጨን ተበሳጨን።
እንሆ ብዙ ተስፋ ያደረግነው ጨዋታ አራት ለምንም በሆነ በጣም የሚያበሳጭ ውጤት ተደመደመ። ያለቀሰ ሰውም በረከተ። የግጥም አዚምም ይህንን አስባለን
“ያሳለፍኩት ጊዜ
መጣ ተመልሶ
ጋሸ ቡርኪናፋሶ
አበዛብኝ ለቅሶ”
በመጨረሻም ተስፋ
ማክሰኞ ለጥር ማሪያም ዕለት 2005 በሚደርገው ጨዋታ ቡርኪናፋሶ ነፍሴ ዛምቢያን ቢያሸንፍልን እና እኛ ደግሞ ናይጄሪያን ብናሸንፍ ወርቅ አድርገን እናልፋለን። ዛምቢያ እና ቡርኪናፋሶ አቻ ቢወጡ እና አሁንም እኛ ናይጄሪያን ብናሸንፍ አሁንም ተንደላቀን እናልፋለን። ስለዚህ ድል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለቡርኪናፋሶ ብሄራዊ ቡድን ማለት አለብን ማለት ነው።
ብስጭታችን በዚህ ያብቃ!

No comments:

Post a Comment