Translate

Tuesday, December 4, 2012

እውን ይህ አገር የማነው ?? የሁላችንም ጥያቄ መሆን አለበት !


  • ጉራማይሌዎቹ የመንግስት ሎሌዎች
    እድሜያቸው ጠና ያለ ነው፡፡ አብዛኛውን እድሜያቸውን ክፍል ያሳለፉት ቀላል በማይባል የህይወት ውጣ ውረድ ነው፡፡ የያዙት ዲን(ሀይማኖት) ጠንክሮ መስራት ከኢባዳዎቹ መካከል አንዱ እንደሆነ አስተምሯቸዋልና ሁሌም ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ይተጉ ነበር፡፡ አንድ ቀንም የተሻለ የሚባል ኑሮ እንደሚኖራቸው ያምኑ ነበርና ወጣትነታቸውን አምርረው በስራ አሳለፉት፡፡ አናም እኚህ አባት አልተሳሳቱም ነበር፡፡ አሁን አላህን እያመሰገኑ መልካም የሚባለ ኑሮ ይኖራሉ፡፡ እናም እኚህ አባት ቤተሰብ መስርተው ሲኖሩ ሲኖሩ ሲኖሩ (ተረት አስመሰልኩት አይደል ምን ላድርግ ማሳጠሬ እኮ ነው) ህዳር 21\2005 ደረሰ፡፡ አርብ ህዳር 21 የማይቀር ቀጠሮ ነበረባቸው፡፡ በልደታ ፍርድ ቤት መገኘት ነበረባቸው፡፡ እናም ሁሌም እንደሚያደርጉት ነጭ የኢስላም ኮፍያቸውን ራሳቸው ላይ ደፍተው በጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተከሰቱ፡፡ አንባቢዎቼ እዚህ ጋር ላስቁማችሁ፡፡ እኚህ አባታችን በእለተ አርብ ህዳር 21\2005 ልደታ ፍርድ ቤት የግድ መገኘት ነበረባቸው ስላችሁ ቀኑ ኮሚቴዎቻችን ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ስለሆነ የነሱን የፍርድ ሂደት ለመከታተል የተገኙ መስሏችሁ እንዳትሳሳቱ፡፡ እሳቸው በግል ጉዳያቸው በገጠማቸው እክል ነው ፍርድ ቤት የመጡት፡፡ ኧረ እንዲያውም ኮሚቴዎቻችን ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ቀን መሆኑንም የሚያውቁም አይመስለኝ፡፡ ብቻ አሁን እሱን እንተወውና ወደገደለው እንግባ(ወደገደለው ማለቴ የኛ የወጣቶቹ ዘመነኛ ቋንቋ ነች ሌላ እንዳይመስልህ lol) ፡፡ እናም እኚህ አባታችን የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው እንዳይረፍድባቸው በመስጋት ከመኖሪያ ቤታቸው እንደምንም ተወርውረው ልደታ ፍርድ ቤት ደረሱ፡፡ ቶሎ ቶሎ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ጨራርሰው ጁሙዐ መስገድ አለባቸው፡፡ አሁን ደረሱ፡፡ አልሃምዱሊላህ፡፡ልደታ ፍርድ ቤት እንደደረሱ ባይናቸው በብረቱ አረጋግጠዋል፡፡ ግን የተሳሳቱ መሰላቸው፡፡ ለበርካታ ግዜ የተመላለሱበት ፍርድ ቤት ጠፋቸው ይሆን? ኖ ልክ ናቸው፡፡ ልደታ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ግን ደግሞ የተሳሳቱ መሰላቸው፡፡ ፍርድ ቤት እሄዳለሁ ብለው የሆነ ጦር ካምፕ ውስጥ ይሆን የመጡት ? አባታችን ተምታታባቸው፡፡ አሁን ትንሽ ተረጋግተዋል፡፡ ልክ ናቸው ልደታ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ዛሬ ፍርድ ቤቱን ይጎበኛሉ ማለት ነው፡፡ ወይ ከሚዲያ መራቅ! ETV መክፈት ስላቆምኩ ነው እንጂ ብከፍት ኖሮ ነገ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ልደታ ፍርድ ቤትን ስለሚጎበኙ ሁላችሁም ሰጥ ለጥ ብላችሁ እንድታሳልፏቸው የሚል ዜና ያዳምጡ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ETV አልከፈቱም ነበር፡፡ለዚህ ነው ዛሬ ልደታ ፍርድ ቤትና አካባቢዋ የጦር ካምፕ የመሰሉት፡፡ አባታችን ይህን እያሰቡ ወደ ፍርድ ቤቱ ሲጠጉ በዛው ልክ ወደሳቸውም አቅጣጫ መሳሪያ የታጠቁ ሰው መሳይ ነገሮች እየተጠጓቸው ነው፡፡ ነገሩ ምን እንደሆነ እንኳ ለመረዳት ግዜ አላገኙም፡፡ አንዱ ፌዴራል መጥቶ ገፈተራቸው፡፡ እንዴ ግራ ተጋቡ፡፡ የገፈተራቸው ሰው ክንዳቸውን ጠፍንጎ ለሌላኛው አቀበላቸው፡፡ አባት ግራ ተጋቡ፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልደታ ፍርድ ቤትን ለመጎብኘት እንዳልመጡ ተረድተዋል፡፡ ተሳስተዋል ማለት ነው፡፡ እኔ ሳልሰማ ሃገራችን ኢትዮፕያ በጠላት ጦር ተወራለች ማለት ብለው አሰቡ፡፡ እንዴ መንግስትስ ይሄን አልሰማም ? እንዴት የጠላት ጦር ድንበር ተሻግሮ መጥቶ መሃል አዲስ አበባ ልደታ ፍርድ ቤት እስኪደርስ ዝም ተባለ ? አባት ምኑም ሊገባቸው አልቻለም፡፡ እሳቸው ጠላት በመሰሏቸው ታቂዎች እየተገፈተሩ መኪና ላይ ሲጫኑ በወገናቸው ለዚያውም ግብር እየከፈሉ ደሞወዝ በሚከፍሏቸው ፌዴራል ፖሊሶች መሆኑን እንዴት ይመኑ ?ግን አባት ማመን አልቀረላቸውም፡፡ አንዱ የፌዴራል ፖሊስ አባል “ጫነው ”ብሎ ሲያዝ ሰሙት፡፡ አሁን አመኑ፡፡ በአማርኛ ነው ሰውየው የተናገረው፡፡ ለዛውም እሳቸውን የሚያህል ትልቅ ሰው “አንተ” ብሎ ነው የዘረጠጣቸው፡፡ አሁን አባት ወደማንነታቸው ተመለሱ፡፡ ድንገትም ቱግ አሉ፡፡ ምን እየተደረገ እንደሆነ እንዲያስረዳቸው አንዱን ፌዴራል ፖሊስ አባል በቁጣም ጭምር ጠየቁት፡፡ ግን ምንም ዋጋ አልነበረውም፡፡ የጦሩ አዛዝ “ጫነው” ብቻ ብሎ አዘዘው እንጂ አናግራቸው አላለውምና መልስ የለም፡፡ ይህ በሆነ በ5 ደቂቃ ውስጥ የተጫኑበት መኪና ጉዞ ጀምሮ ነበር፡፡ አባት ሃገር አልባነት ተሰማቸው፡፡ ምንም ነገር ሳያውቁትና ሳይነገራቸው ወታደራዊ ጥቃት ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በሃገራቸው ሀገር እንደሌላቸው ከመንገድ ላይ ታፍሰው ወደማያውቁበት ቦታ እየተወሰዱ ነው፡፡ በጃቸው የያዙትን የፍርድ ቤት ዶክመንቶቻቸውን አጥብቀው እንደያዙ አካባቢያቸውን ቃኘት አደረጉ፡፡ መኪናው ላይ ከሳቸው በተጨማሪ ወደ 5 ሌሎች ወጣቶች አብረዋቸው አሉ፡፡ ጉድ ነው እስካሁን ይሄን ልብ አላሉም ማለት ነው፡፡ መኪናው ላይ እነሱን የሚጠብቁ 2 የአዲስ አበባ ፖሊስ አብረዋቸው አሉ፡፡ አሁን አባት ነገሩ ይበልጥ ግልፅ ሆነላቸወ፡፡ የኮሚቴዎቻችንን የፍርድ ሂደት ለመከታተል የሚመጡ ሰዎች እየታፈሱ እንደሆነ ተረዱ፡፡ እሳቸውም ምንም እንኳ ወደ ፍርድ ቤቱ የመጡት ለግላቸው ጉዳይ ቢሆንም የሙስሊም ኮፊያ በማድረጋቸው ብቻ እንደታፈኑ ተረዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አባት ፖሊስ ጣቢያ እስኪደርሱ አጠገባቸው ላሉት ፖሊሶች የሚችሉትን ያህል ልክ ልካቸውን እየነገሩዋቸው ነው ጣቢያው የደረሱት፡፡ ፖሊሶቹ ግን እኛ ምን እናድርግ አይነት አስተያየት ከመስጠት ዉጪ ትንፍሽም አላሉ፡፡ አሁን አባት ፖሊስ ጣቢያው ደርሰው እየወረዱ ነው፡፡ እሳቸው እስኪረጋጉ ወደ ሌላ ጀግና እናታችን ልውሰድህ ፡፡ የአባታችንን ከፖሊስ ጣቢያ እስከ ፍርድ ቤት የሰሩትን ገድል እቀጥልልሃለው፡፡
    ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ አንድ ስድና ጋጠ ወጥ ፖሊስ ተይዘው ወደመጡት ሙስሊሞች ላይ ያልተገባ ቃል እየተናገረ ነው፡፡ ሰውየው እንዲሁ ሲታይ ለሆዱ ያደረ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ እዛው ውስጥ የሚያውቁት ሰዎች እንደሚናገሩት ይህ ፖሊስ እድገት ለማግኘት ብሎ የራሱን የስራ ባልደረቦች ጭምር እየሰለለ ለደህንነቶች ወሬ እንደሚያቀብል አንዱ ፖሊስ ሹክ ብሏቸዋል፡፡ ይህን ፅሁፍ የምታነቡ ሁሉ ፖሊሱ ላይ ይህን ስፅፍ ፖሊስ ስለሆነ እና ወገኖቼን ስላሰረብኝ ተበሳጭቼ እንዳይመስላችሁ፡፡ በአላህ ስም እምላለሁ ይህን ነገር ያጋለጠው ከራሱ የስራ ባለደረቦቹ መካከል ላዱ ታሳሪ ሹክ ያለውን ነው፡፡ ከልክ በላይ ሙስሊሞችን ሲያበሻቅጥ ሙስሊሞቹም ተናደው ሌላ ግርግር እዛው ሲፈጠር ነው ሌላኛው ባለደረባው ቀስ ብሎ ለአንዱ ታሳሪ ሙስሊም ሹክ ያለው፡፡ “እናንተ ተረጋጉ እሱ እድገት ለማግኘት ሲልና ለመወደድ ነው እንዲህ እንዲህ የሚያደርገው፣ እንኳን ለናንተ ለኛም አይመች” በማለት ሹክ ያለው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ ማስረጃ ላይ ቆሜ ነው የምነግርህ፡፡ በስራው ታታሪ ሆኖ ወገንን ከማገልገል ይልቅ አቃጣሪ ሆኖ መኖርን መርጧል ማለት ነው፡፡ ይብላኝ ለልጆቹ (ካለው ማለቴ ነው) ሁሌም የአቃጣሪ ልጆች እየተባሉ ይኖራሉ፡፡ ለነገሩ እሱ ምን ያድርግ፡፡ ከስራ ይልቅ የሚያቃጥሩለትን የሚሾመው መንግስታችን ነው ከሰውየው በበለጠ ተጠያቂው፡፡ እሱ ደልቶት ስልጣኑን ለማደላደል ትንንሽ ሆዳሞችን ከታች ለህዝቡ ቤዛ ያደርጋል፡፡ ወደ ጉዳዬ ስገባ የዚህ መጥፎ ሰው ንግግር ያልጣማት ይህች እናት ዝም ማለት አልቻለችምና ነገረችው፡፡ “እኛ አንተ እንደምትለው ሽብር ለመፍጠር አደይደለም የመጣነው፣ የጀግኖቹ ኮሚቴዎቻችንን የፍርድ ሂደት ለመከታተል ነው” በማለት፡፡ አላሁ አክበር ብለሻል አላት፡፡ በደንብ አድርጋ አላሁ አክበርን ደጋገመችለት አጠገቡ፡፡ አበደ ነቀለ፡፡ አሁንም አላሁ አክበርን አባረችው፡፡ሌላኛዋን ወጣት ደግሞ ባጋጣሚ ሲጠራት ወይ ልብ አላለችውም ወይ አልሰማችውም ነበርና መልስ ስላልሰጠችው በጥፊ አላት፡፡ ሁሉም ደነገጠ፡፡ ለካ ፈሪ ነው፡፡ ፈሪነቱን አረጋገጠች፡፡ ሲታይ ወንድ ይመስላል እንጂ ከልቡ ፈሪ ነው፡፡ ሴት ልጅ ላይ እጁን የሚያነሳ ለናቱ ክብር የሌለው የመጨረኛ ወራዳ እንጂ ሌለ ምን መሆን ይችላል? ከታሳሪዎቹ መሃል የሆኑትና እድሜያቸው ወደ 55 የሚጠጉት እናት ደግሞ በዚህ ሰው ብግን ብለዋል፡፡ እኚህ ጀግና እናት ይህ ሰው ቦቅቧቃ እንደሆነ ተረድተዋል፡፡ እጁ ላይ ነፍጥ ስለያዘ እንጂ ብቻውን ቢሆን ያችን ልጅ ጫፏን እንደማይነካት ተረድተው ነበር፡፡ ልጅቷን በጥፊ ሲመታት ሌሎች ፖሊሶችን ጨምፖ ታሳሪዎቹ ቢደነግጡም ይህች ጀግና እናት ግን ደስ ነው ያላቸው፡፡ ለዲኒየል ኢስላም አይደለም በጥፊ መመታት ሞትስ ቢመጣ! ሰውየው እራሱን አዋረደ እንጂ ልጅቷስ ክብሯም አይነካ፡፡ የዚህን ፈሪነት የተገነዘቡት እናት ይህ ሰው እሳቸውንም ይሁን ሌላውን ታሳሪ ጥያቄ ሲጠይቅ ትክክለኛ ምላሽ ነበር የሚሰጡት፡፡ ለዛውም ኮራ ጀነን ብለው፡፡ ምላሻቸው ደግሞ እውነት በመሆኑ የትኛውም ፖሊስ ሊያስቆማቸው አልቻለም፡፡ ፍርድ ቤት መገኘት ወንጀሉ ምን እንደሆነ እንዲያስረዷቸው ለፖሊሶቹ ጠየቁ እናት፡፡ማንም ፖሊስ ግን ቀና ብሎ መልስ አልሰጠም፡፡ ጋጠወጡ ፖሊስ “አንቺ ምን አግብቶሽ መጣሽ” አላት፡፡ የመረጥኳቸው ኮሚቴዎቼ ናቸው፡፡እንደልጆቼ ነው የማያቸው” መለሱለት እናት ኮራ ብለው፡፡በመጨረሻማ ይህ ጋጠወጥ ፖሊስ የህፃን ጨዋታ አመጣ፡፡ አንድ መጥፎ ቃል ማንኛውም ሙስሊም ታሳሪ ላይ ሲወረውር መልስ የሚሰጡት እኝህ እናት ነበሩ የሁሉ ጠበቃ፡፡ በመጨረሻ ይህ ፈሪ ፖሊስ “እኔ አንችን አላናገርኩም፡፡ ከአሁን በኋላ በቃ አታናግሪኝ” ብሏት እርፍ አለላችሁ፡፡ ህፃንነቴ ትዝ አለኝ፡፡ ህፃን ሆነን እቃቃ ስንጫወት ጫወታው ለኔ የሚመች ካልሆነ በቃ አታናግረኝ ካንተ ጋር አልጫወትም ብላችሁ ያላችሁት ትዝ አላላችሁም ? ለማንኛውም እቃቃ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ፡፡ አሁን ወደሌሎቹ ልመለስ፡፡ የቅድሙ አባትና ሌሎች ወጣቶች ደግሞ በግቢው ላሉት ፖሊሶች ሁሉ በጥሩ መደማመጥ ስሜት መንግስት በሃይማኖታችን ላይ ጣልቃ እንዴት እንደገባ፣ ስለ አወሊያ፣ ስለ መጅሊስ ወዘተ እያስረዱ ነበር፡፡ ያ ጋጠወጥ ፖሊስና ጥቂት ሴት ፖሊሶች ሲቀሩ ነገሩን አምነውበት ተማምነው እነሱ ታዘው እንጂ አስበውበት የሚያደርጉት አንዳች ነር እንደሌለ ተናገሩ፡፡ ወይ ጉድ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ አሉ፡፡ ያላመኑበትን ነገር ታዳ ምን አሰራቸው፡፡ አንዱ ፖሊስማ አስቂኝ ነገር ነው የተናገረው “ እኛ ጥያቄያችሁና እየሄዳችሁበት ያለው ነገር ትክክልና ህጋዊ ነው፡፡ ግን እኛን ስራ አበዛችሁብን ፡፡ የናንተ ኮሚቴዎች ፍርድ ቤት በመጡ ቁጥር እኛ ጫና ይበዛብናል፡፡ ለምሳሌ እዚህ አድረን ረፍት መውጣት ነበረብን፡፡ ግን እድሜ ለናንተ እዚሁ ዋልን፡፡ ማታ ደግሞ ተመልሰን ገቢዎች ነን፣ ታዳ ለኛስ ለምን አታዝኑልንም ?” ሲል ተነጫነጨ፡፡ ኧረ ጎበዝ እንዴት አይነት ነገር ነው የሚያወሩት ?ሄደው መንግስት ላይ ይጩሁ እንጂ እኛ ምን አደረግናቸው ጃል፡፡ የህግ አካላት ሆነው ስለህግና መብትም እናስረዳቸው እንዴ ? ፍርድ ቤት መገኘት መቼ ነው ደግሞ ወንጀል የሆነው ? ፖሊሶቻችን ኧረ አንብቡ! ማንበብ እውቀት ይጨምራል፡፡ በዚህ መሃል ሁላ ያ ጋጠ ወጥ ፖሊስ አሁንም አለ፡፡ እሱ ሲናገር እኚያ እናት ልኩን ይነግሩታል፡፡ አይናቸው እያየ መቼስ ሴት በጥፊ ሲማታ አይተውታልና ፈሪነቱን አልተጠራጠሩም፡፡ አሁንም አፉ አላረፈም፡፡ “መንግስት ጣልቃ አልገባባችሁም ደሞ ይሄም ሃይማኖት ሆኖ ” ሲል ለመንግስት ከማቃጠር የዘለለ ፍላጎቱን ይፋ አደረገው፡፡ አሁን እሱም ሌሎቹም ፖሊሶች ደነገጡ፡፡ ለካንስ እንዲህ የሚያክለፈልፈው ለኢስላም ያደረበት ጥላቻም ጭምር ነው፡፡ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ የግሉን አጀንዳ እየሰነቀረ ነው፡፡ ለካንስ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ተመስገን ደሳለኝ በአንድ ወቅት በፍትህ ጋዜ ላይ “እውነት ይህች አገር የማናት?” ሲል የፃፈው ወዶ አልነበረም፡፡ ይህ አፄው አይነት ስርአት ናፋቂ የሆነ ተራ አቃጣሪ ፖሊስ አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በመርሳት ይህን ካንሰር አስተሳሰቡን የማይረባ አንጎሉ ውስጥ ደንቅሯት ኖሯል፡፡ እንደነዚህ አይነት ዜጎች እያሉ መች ሃገር ታድጋለች፡፡ እንደራሳቸው ተራና የወረደ ሃሳብ ይዘው ሃገሪቷን ወደኋላ ይጎትታሉ፡፡ ለዘመናት ይህች ሃገር ወደ ኋላ የተንፏቀቀችው በንደነዚህ አይነቶቹ ሃሳብ አራማጆች እየተመራች በመሆኑ እንደሆነ ዛሬም አይማሩም ፡፡ የሚገርመው ይህ አላማቸው አንዲትም ኢንች እርቀት አያስኬዳቸውም፡፡ ይህ ፖሊስ “መንግስት ጣልቃ አልገባባችሁም ደሞ ይሄም ሃይማኖት ሆኖ ” ሲል ፖሊሶቹም፣ ሙስሊሞቹም ደነገጡ ብዬህ አልነበረም ? አዎ ተደናገጡ፡፡ ሌሎቹ ንቀውት በተዉት አይነት ሲሜት ሲዋጡ እኚህ እናት ግን ነገሩት “ለዛውም እስከ ጭንቅላቱ ነዋ! “ አሉት ፡፡ተናግሮ ሊያናግር ነው፡፡ ዘሎ ሀይማኖት የተሳደበው የሱንም ሃይማኖት(ካለው ነው እንግዲህ) እንዲሰደብና ሌሎችም በጉዳዩ እንዲገቡ ነበር፡፡ ግን አኒያ አባትና ሌሎች አረጋጉ፡፡ ተዉት ይለፍልፍ በማለት፡፡ እኒያ እናት ግን ”አንተ ሃይማኖትህ ሲነካ ፈርተህ ዝምታን መርጠህ ይሆናል ፣ወይም ሃይማኖት የለህም፡፡ እኛ ግን ዲናችንን ማንም እንዲነካው አንፈቅድም ” በማለት ተገቢውን ምላሽ ሰጡት፡፡ አሁን ነገሩ አስፈራ፡፡ ይህች እናት ምንም አልበገር ስላለችው ነው መሰል“ እነዚህንስ ማሰር ሳይሆን በጥይት ነበር” ሲል የመጨረሻ ፍላጎቱን አፍረጠረጠው፡፡ “ሞክሩና!” የጀግናዋ እናት ምላሽ ነበር፡፡ ነገሩ እየመረረ ሲሄድ ሌሎች ፖሊሶች ሰውየውን ዘወር እንዲል አደረጉት፡፡ ታሳሪዎቹንም አረጋጉ፡፡ ግን ግን የሚመራን መንግስት ተሿሚዎች ምን አይነቶች እንደሆኑ አየን አይደል ? ለሃገር ሰላም በማያስቡ ደንታ ቢሶችና ሃይማኖት የለሾች ነው መዋቅሩ የተተበተበው፡፡ለየትኛውም እምነት የማይበጁ ፣ሆዳቸውን ከማሯሯጥ ውጭ ሌላ ምንም በማይታያቸው ግለሰቦች ነው ሃገሪቱ እየታመሰች ያለችው፡፡ ሀገሪቱን አንዴ በዘር ሌላ ግዜ ደግሞ በእምነት እየመረጡ ህዝብ የሚጨቁኑት፡፡ ግን ከምንም በላይ ተጎጂዎቹ እነሱ አይደሉም ፡፡ ሃገሪቱ ነች፡፡ ወደማትወጣው ገደል እየሰደዷት ነው፡፡ ለማንኛውም ወጌን ልቀጥልልህ፡፡ ያን ቀን በዛች ፖሊስ ጣቢያ ብዙ ጉድ ቢወራም እየመረጥኩ ነው የማወራህ፡፡ ፖሊሶቹ ሌላም ነገር ግልፅ አድርግዋል፡፡ ሙስሊሙ ለመንግስት ከባድ ፈተና እየሆነ እንደመጣ በሙስሊሙ ጉዳይ እላይ ድረስ ጭቅጭቅ እንደሆነ በማስሰጠንቀቅም ጭምር ለፈፈ አንዱ አለቃ መሳይ ፖሊስ፡፡ እኛ መች ጠፍቶን ይሄ፡፡ ለዲናችን እስከ ህይወት መስዋእትነት ማለት አይገባቸውም? ለዛውም እዛ የሚያደርስ ምንም ነገር የለውም፡፡ በዲናችን ጣልቃ አትግቡ ማለት ወንጀል ነው ? መሪዎቻችንን ራሳችን እንምረጥ ማለት ወንጀል ነው ?ግራ የገባቸው ፖሊሶቻችን እኛንም ግራ አጋቡንኮ! ለማንኛውም እስረኞቹና ፖሊሶቹ በዚህ አይነት ሲነታረኩ ውለው መሸ፡፡ ካሁን አሁን ትለቀቃላችሁ እየተባሉ ጊዜው ነጎደ፡፡ ማንነቱን የማያውቁት አካል ከበላይ እየደወለ ፖሊሶቹን እንዳይለቋቸው ስላስጠነቀቀ በእስር ቤቱ ማደር ግድ ስለሆነባቸው ሴቶቹም ወንዶችም በመኪና እየተጫኑ ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ፡፡ መኝታቸውንም በዛው አደረጉ፡፡ እኒያ አንደበተ ርቱኡ አዛውንትም ያን እለት ለታሰሩት በጠቅላላም አንድ ነገር ሲያበሽሩ ነበር፡፡ “አብሽሩ ፍርድ ቤት ብንቀርብና የገንዘብ ዋስትና ብንጠየቅ ማናችሁም እንዳትጨነቁ፣ማንንም እንዳታስቸግሩ ሁሉንም እኔው አስፈታለሁ” ሲሉ አበሽረው ነበር፡፡ አቦ አላህ ያበሽራቸው ሲነጋ አስገራሚውን የአቃቤ ህግ ክስንና የዳኛውን ውሳኔ እነግርሃለው፡፡ እስኪነጋ አንድ የተረሳ አጋጣሚ ላጫውትህ፡፡
    እንደገና ወደኋላ አርብ ከጠዋቱ 4 ሰዐት ተኩል አካባቢ
    አሁን ኮሚቴዎቹ ከልደታ ፍርድ ቤት ለባቡር ስራ በሚል በተቆፈረውና ዝግ በሆነው በር በኩል እየወጡ ናቸው፡፡ ሰዉን አባረው እንኳ ያልጠረቁት በርካታ ፌዴራሎች አሁንም ኮሚቴዎቻችንን ከጫነው መኪና ጋር በእግራቸው እየሮጡ ነው፡፡ ከልደታ ፍርድ ቤት ቁልቁል ወደሳር ቤት በሚያስወጣው መንገድ ላይ፡፡ የተወሰኑ እህቶችና አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ ከፍርድ ቤቱ አካባቢ በመባረራቸው ወደሳር ቤት ወደሚወስደው ቁልቁለቱ ላይ እይሄዱ ነው ወደቤታቸው፡፡ ኮሚቴዎቹን ባለማየታቸው አዝነዋል፡፡ እናም ተስፋ ቆርጠው ወደቤታቸው እየሄዱ ነው፡፡ በዚህ መሃል ድንገት ሁካታና ወከባ ከጀርባቸው ተሰማቸው፡፡ አንድ ሙሉ ለሙ የተሸፈነ መኪና ከኋለውና ከፊቱ ፌዴራለ ፖሊስ አጅቦት ወደነሱ እየቀረበ ነው፡፡ ኮሚቴዎቹን የጫነው መኪና እንደሆነ አውቀዋል፡፡ ደስ አላቸው፡፡ በሁለቱም አስፋልት ከግራና ቀኝ በእግር በሶምሶማ መኪናዎቹን እየተከተሉ የሚሮጡ ፌዴራል ፖሊሶችም እየቀረቧቸው ነው፡፡ እኒህ ጥቂት ወንድሞችና እህቶች በሩጫ ስለሚመጡት ፌዴራል ፖሊሶች ግድም አልሰጣቸው፡፡ ቆመው ጠበቋቸው፡፡ ኮሚቴዎቻችንንም በስር በኩል በተሰራው አየር ማስገቢያ እጃቸውን እያውለበለቡ ነበር፡፡ ኮሚቴዎቹ ይህን ያደረጉት ሰው አይተው ሳይሆን የተጫኑበት መኪና ሙሉ ለሙሉ ሽፍን በመሆኑ ምንም አይታያቸውም፡፡ ግና በርግጠኝነት ህዝቡ እነሱን ብሎ እንደሚመጣ ስለሚያውቁ በግምት ነበር እጃቸውን የሚያውለበልቡት፡፡ እናም እነዚህ ጥቂት ወንድሞችና እህቶች ይህን እድል አገኙ፡፡ ወዲያው ግን በፌዴራሎች መከበባቸውን አዩ፡፡ ወንዶቹንና ሴቶቹን ከያዙት ፌራሎች መሃል ግን የሆነ ነገር ተነገረ፡፡ ፌዴራሉ በተናገረው ነገር ሁሉም ደንግጧል፡፡ አንዱ ፌዴራል ቀስ ብሎ “ባክህ ቀስ አድርገህ ልቀቃቸው” አለው፡፡ ይህም ፌዴራል “ቆይ አይዛችሁ አስመልጣችኋለዉ ተረጋጉ የሰራችሁት ወንጀል የለም ብሎ ማስመለጫ ቦታ አይኑ ሲቀላውጥ የእድል ነገር ሆነና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሌሎች ፌዴራል ፖሊሶችና የአዲስ አበባ ፖሊሶች በሚኪና ደርስው ጫኑዋቸው፡፡ እነዚህ ሙስሊሞች የገረማቸው መጫናቸው አይደለም፡፡ ቢጫኑም ቢያንስ የኮሚቴዎቻችንን እጆች በማየታቸውም አልቆጫቸውም፡፡ የገረማቸው ግን ከ 2ቱ የፌዴራል ፖሊስ አባላት “አስመልጣቸው” የምትለዋ ቃል ነች፡፡ እጅግ ጥቂት ቢሆኑም የመንግስት ህገ ወጥነት የማይዋጥላቸው ም ወታደሮች ከውስጣቸውም እንዳለ አመላካች ነው፡፡
    እንደምን አደራችሁ አሁን እለተ ቅዳሜ ህዳር 22\2005 ከጠዋቱ 4:20 ይላል፡፡ ቦታው ሜክሶኮ ዋቢሸበሌ ሆቴለ ፊት ለፊት ከሚገኘው ፍርድ ቤት፡፡ ተከሳሾች 8 ሴቶችና 32 ወንዶች(ከነዚህ ውስጥ 7ቱ ወንዶች አቃቤ ህግ በልዩ ክስ ነው የከሰሳቸው፡፡ የተያዙት ግን ልደታ ፍርድ ቤት ለምን መጣችሁ ተብለው ነው፡፡) ዳኛው አቃቤ ህጉን ጠየቁ ”ክሳቸው ምንድነው? “ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ከመሞከራቸውም በላይ ኮሚቴዎቹ ከፍርድ ቤት ሲወጡ የኮሚቴዎቹን መኪና በግድ ለማስቆም ሞክረዋል”፡፡ ዳኛው የደነገጡ መሰሉ፡፡ ይህን ከባድ ክስ ወደተከሰሱት ተከሳሾች ዞረው ተመለከቷቸው፡፡ ከ8ቱ ሴቶች አንዷ እናት ናቸው፡፡ሌሎቹ ደግሞ እድሜያቸው ከ17 አይዘልም፡፡ ከወንዶቹ መሃል ደግሞ አንድ የ14 አመት ታዳጊ ና ሌላ አንድ አዛውንት ይገኙባቸዋል፡፡ ዳኛው ያቃቤ ህጉ ልቅ ውሸት ባይዋጠላቸውም ዳኛ ናቸውና ተከሳሾቹን አስተያየት ጠየቁ፡፡ አሁን አዛውንቱ ተናገሩ “ክቡር ፍርድ ቤት እውነት ለመናገር እኔ ኮሚቴዎቹን እንደ ልጆቼ እወዳቸዋለሁ፣አከብራቸዋለሁ፣የታሰሩትም ፍትሃዊ የሃይማኖት ጥያቄ ስላነሱ ነው፡፡ እኔ እነዚህን ጀግኖች ፍርድ ቤት ተገኝቼ ፍርዱን መከታተል ብችል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግኔ እኔ ባጋጣሚ ፍርድ ቤት የመጣሁት ለራሴ የግል ጉዳይ ነው፡፡ ከፍርድ ቤት አፍሰውኝ የኮሚቴዎቹን መኪና ለማስቆም ሞከረ ሲሉ አያፍርም እንዴ ለመሆኑ ክቡር ፍርድ ቤት ለመሆኑ ይህች ሃገር የኛ የሙስሊሞቹ ም አይደለችም እንዴ ? አሁን እነኚህ ህፃናት ናቸው (ወደ 14 አመቱ ታዳጊና ወደሴቶቹ እያመለከቱ) መንግስትትን በሃይል የሚገለብጡና መኪና አስቁመው እስረኛ የሚያስመልጡ ?እኔ በመታሰሬ ምንም አልተሰማኝም፣ የተሰማኝ ሙስሊም በመሆናችን ብቻ ያለ ወነጀላችን መሰቃየታችን ነው ” ሲሉ እያለቀሱ ጭምር አስረዱ፡፡ ዳኛው ሌሎቹንም አናገሩ አንዱ ወጣት “እንኳን ተደራጅተን መኪና አስቁመን እስረኛ ለማስመለጥ አይደለም ስታሰርም ታሳሪዎቹን ያየኋቸው እዚህ እስር ቤት ነው፡፡ ካለዛሬም አይቻቸው አላውቅም ”አለ፡፡ ጀግናዋ እናትም “የመጣሁት ኮሚቴዎቼን ለማየት ነው መብቴ ነው ” ብለው እውነቷን ቁጭ አደረጉ፡፡ ዳኛውም ወደ አቃቤ ህጉ መለስ ብለው ማስረጃ ጠየቁት፡፡ ማስረጃ ለማሰባሰብ የ14 ቀን ቀጠሮ ጠየቀ፡፡ ወይ ሃገር፡፡ አሁን አቃቤ ህግ ተሆነና ተሞተ! በሱ ቤት በቃ ፕሮፌሽናል አቃቤ ህግ ነው፡፡ ዳኛው ግን አልሰሙትም በነፃ እንዲፈቱ ካልሆነ ግን ሰኞ ሲመጡ በነፃ ከዛው ከፍርድ ቤት እንደሚለቋቸው ነገሩትና ችሎቱን ዘጉት፡፡ ፡፡ይህን ይመስላለል እንግዲህ ወንጀል ባልሰሩ ሙስሊሞቸ ላይ በግፈኛው መንግስት ሲንገላቱ የነበረው፡፡ ለዛውም ህፃናት ፣አዛውንትና ሴቶችን፡፡ በዚህ ፅሁፍ ጉራማይሌ የመንግስት ሎሌዎችንም ታዝበናል፡፡ ጥቂቶቹ የመንግስት አካሄድ ባይዋጥላቸውም እንጀራችን ነው በሚል ፈሊጥ አሽከርነታቸውን ተቀብለዋል፡፡ ገሚሶቹ ፍጥጥ ብለው ከህዝብ ጋር ጀርባ ሆነው ከአምባገነኑ ጋር በመለጠፍ ለፍርፋሪ ይተጋሉ፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ህሊናቸውን ፈርተው በሚችሉት ለህሊናቸው ይሰራሉ፡፡ ኢንሻ አላህ አላህ እነዚህን በዳዮች በቅርቡ ከተበዳዮች በታች ሁነው ሲሸማቀቁ ያሳየን፡፡ ፍትህንም ያቅርብልን፡፡አሚን፡፡
    (እና እውን ይህ አገር የማነው ? የኔ ያንተ የእሱ የእሷ የተቃዋሚ የደጋፊ የኢህአዲግ የኦነግ የሙስሊሞች የክርስቲያኖች የአማኞች ሀይማኖት የሌላቸው በአጠቃላይ የሁላችንም ኢትዮጵያኖች አገር ነች እና ሁላችንም በ እኩል መኖር አለበን”) በቅንፍ ውስጥ ያለው የአንዋር ጅላል ንግግር ነው

No comments:

Post a Comment