Translate

Monday, December 10, 2012

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች ውዝግብ መሥሪያ ቤቱን እያመሰው ነው


ኢሳት ዜና:-ሰንደቅ በህዳር 25፣ 2005 ዓም እትሙ እንዳስነበበው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሚኒስትሩና በሚኒስትር ዴኤታው መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ተቀስቅሷል።

በሁለቱ ሚኒስትሮች የተፈጠረው አለመግባባት በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ላይ ግራ መጋባትን መፍጠሩን የጠቀሰው ሰንደቅ፣  ወደ 1 ሺህ 800 የሚጠጉ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችም ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን አልቻሉም ብሎአል።
የጸቡ ምክንያት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንትና ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዳውድ መሐመድ የሚኒስትር መስሪያቤቱ ሚኒስተር   መስሪያ ቤቱን ለብልሹ አሰራር አጋልጠውታል በማለት በግልፅ ነቀፌታ በማቅረባቸው ነው።
የሁለቱ ሚኒስትሮች አለመግባባት የተቋሙ የማኔጅመንት ሰራተኞች በተሳተፉበት በቅርቡ በተካሄደ ስብሰባ ለመፍታት ቢሞከርም በሚኒስትሮቹ መካከል በተፈጠረ እሰጥ አገባ ሰራተኛው ተደናግጦ እንደነበር ተገልጿል።

በቅርቡ ሚኒስትሩ አቶ አሚን ሚኒስትር ዲኤታውን አቶ ዳውድን ደብዳቤ በመፈረም ወጪ እንዳያደርጉ ትእዛዝ የሰጡ ሲሆን ይሄንን ተከትሎ አቶ ዳውድ የሚመሩት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የባህል ዘርፍ ከፍተኛ የስራ መበደል እየደረሰበት መሆኑን የመስሪያ ቤቱ ምንጮችን ምንጮች በመጥቀስ ጋዜጣው ዘግቧል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደምም በቀድሞ ሚኒስትር አምባሳደር መሐመድ ድሪር እና በቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ መሐመድ ጋአስ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ መቆየቱን ያስታወሰው ጋዜጣው፣ አቶ ዳውድ አሁን ስለተፈጠረው ችግር ለጋዜጣው ፤ “ትልቁ የሚያጣላን ነገር የአመራር ችግር ነው። ” በማለት ገልጸዋል።
“አንድ አመራር አንድ የሆነ ስትራቴጂክ ዕቀድ እና አስተሳሰብ ይዞ ካልተንቀሳቀሰ ለውጥ አያመጣም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሞታቸው በፊት አንድ ስልጠና ወስደን ነበር። ስልጠናው በልማት ሰራዊት ተቋሙን የመቀየር ዓላማ የሰነቀ ነበር። የለውጥ ሰራዊት እቅድ አውጥተን ብንቆይም እንዳለ የለውጡን እቅድ መፈፀም አልቻልንም። 11 ወራት አልፎታል። የሚያጣላን ነገር ለምን ሥራው ተፈፃሚ አይሆንም በሚል ነው።” በማለት የተናገሩት አቶ ዳውድ ፤ ሚኒስትሩ አቶ አሚን ስልጠና ላይ እያሉ እኔና ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ ሁሉንም ሰራተኞች አሳትፈን የተቋሙ ችግሮች ምንድን ናቸው ብለን አንድ በአንድ ለቅመን ካወጣን በኋላ ወደ እቅድ ብንቀይረውም፣   ችግሮቹ ነጥረው ወጥተው ውይይት እንዲካሄድባቸው ግን አልተፈለገም ብለዋል።
አንድ ችግር በግልፅ ካልወጣ ወደ እቅድ መግባት አይቻልም” የሚሉት አቶ ዳውድ ሰራተኛው የሚጋራቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉም ተናግረዋል።  ሰራተኛውን ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዴኤታዋ (ወ/ሮ ታደለች) በኔትወርክ በመያያዛቸው መካከለኛ ማኔጅመንቱ እንዲጠናከር አልፈለጉም ሲሉ ቅሬታቸውን የገለፁት አቶ ዳውድ፤ “ካለን ወደ አንድ ሺ ስምንት መቶ ሰራተኛ ውስጥ የተወሰነ ሃያ ወይ ሰላሳ ሰው ይዞ መሄድ ምን ያህል አግባብ ነው ለሀገርስ ይጠቅማል” ሲሉ ጥያቄ ማቅረባቸው ተዘግቧል።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ሚኒስትሩ አቶ አሚን እና ሌላኛዋ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች “የተወሰነ የራሳቸውን የጥቅም ኔትወርክ ይዘዋል” በማለት አጋልጠዋል። ወ/ሮ ታደለች የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን ማርኬቲንግ ክፍልና የሚኒስትሩ አማካሪ በመያዝ የማይሆኑ ሰዎችን በማሰባሰብ ለውጥ ማምጣትም አይችሉም በማለትም ነቅፈዋል።
ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትር ዴኤታዋ የሰበሰቡትን ኃይል “እናፍርሰው ብለን ተስማምተን ነበር”። ነገር ግን የሚኒስትሩ ቡድን የራሳቸው ጥቅም ስላላቸው ፈቃደኛ አልሆኑም። ዋናው የሚያጣላንም ጉዳይ የሰው ኃይል ምደባ የመሆኑም ሚስጢር ይሄው ነው። ጠንካራ ሰው እንዲመጣ አይፈለግም። በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ስር ያሉ የተቋማት ኃላፊዎች ማለትም ብሔራዊ ቴአትር፣ ቤተ መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት፣ የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ቅርስና የዱር እንስሳት ጥበቃ አሉ። እነዚህን ተቋማት የሚመሩት ጠንካራ ሰዎች አይደሉም በማለት ሚኒስትር ዴኢታው መስሪያ ቤቱን ገመና ገሀድ አውጥተዋል።
“በጨለማ ተደብቀው የመሾም ተግባር ነው ያለው። ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች አሉ። ተቋማቱን የሚመሩ ኃላፊዎች መሾም ያለባቸው በአቅምና ሕግ በሚጠይቀው መመዘኛ እና በሙያም በፖለቲካም ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው የሚሉት አቶ ዳውድ፣ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አሳታፊ ባልሆነ እቅድ ስራው ወደ ቀበሌ መውረድ አልቻለም ” ሲሉ ወቅሰዋል።
በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሰራር መኖሩን  ሚኒስትር ዴኤታው አጋልጠዋል።  ለምሳሌ ይላሉ ሚኒሰትር ዲኤታው  ”  ሚኒስትሩ 128 ሺህ ብር ከመስሪያ ቤቱ ሂሳብ ቋት ወጪ በማውጣት ለህክምና ተጠቅሟል።በመመሪያው መሰረት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ደኤታዎች ስንታመም መታከም ያለብን ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ነበር። ነገር ግን ከባህልና ቱሪዝም ፋይናንስ ወጪ በማድረግ በወ/ሮ ታደለች በተፈረመ ወጪ አላግባብ ታክመዋል” በማለት ገልጸዋል። ይህ ብልሹ አሰራር ማስረጃ ያለው በመሆኑ እንጂ ማስረጃ የሌላቸው በርካታ ብልሹ አሰራር በተቋሙ ውስጥ መኖሩንም ገልጸዋል።
በወ/ሮ ታደለች ስር የ35 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት መኖሩንም የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ይህ ፕሮጀክት እየተጓተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ” ከሁሉም እኔ የሚያስጠላኝ ለቋሚ ኮሚቴ የሚቀርበው ሪፖርት ውሸት ነው። ሲቪል ሰርቪስ የሚቀርበው ሪፖርት ውሸት ነው። እኛም ጋ ማኔጅመንት ስንገማገም የሚቀርበው ሪፖርት ውሸት ነው። እኔም ውሸት ሲሰለቸኝ ተውኳቸው”ሲሉ የገለጡት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ቀደም ሲል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሰው ተመድቦ ለአንድ ቀን በር ዘግተው ተገማግመው እንደነበር አስታውሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ችግሩን እንድንፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ ፍቱ መባሉን  ጠቅሰው፣  ”ሚኒስትሩና ወ/ሮ ታደለች አቅጣጫውን አልተቀበሉትም። ምክንያቱም ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ከሄዱ ተጠቃሚነትን ያጣሉ። በዚህም መሰረት የተሳሳተውን አቅጣጫ ማስቀጠል ነው የመረጡት” ብለዋል።
“ከእኛ በፊት የነበሩ ሚኒስትሮች ፎቅና ቤት ሲሰሩ በማየታቸው እነሱም መስራት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ይሄንን ለመፈፀም የተሳሳተ አቅጣጫ መከተል አለብህ ትክክለኛና ህዝባዊ አቅጣጫ ስትከተል ግን አታገኝም” በማለት በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ ሚኒሰትሮች የሚፈጽሙትን ሙስና አጋልጠዋል

No comments:

Post a Comment