Translate

Tuesday, December 18, 2012

መስፍን ኢንጂነሪንግ 30ሚሊዮን ዶላር አተርፋለሁ አለ


በአማራ አረም ለማስወገድ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ ተደረገ

mesfin industrial engineering


በኤፈርት ስር ከታቀፉት የህወሃት የንግድ ተቋሞች መካከል አንዱ የሆነው መስፍን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪያል በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር ለማትረፍ እንደሚሰራ አስታወቀ። ለሶስት ስኳር ፋብሪካዎች የአገዳ መቀቀያ ገንዳ (ቦይሊንግ ሃውስ) ለመስራት የሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ስምምነት አደረገ።
የአማራ ክልል በብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ድምቀት ላሳየው “ቁርጠኛነት” ተደነቀ፣ ጣና ሃይቅና አካባቢውን የወረረውን አደገኛ አረም ለማጥፋት የአንድ ለአምስት የጥርነፋ አደረጃጀት ማከናወኑ የአካባቢውን አርሶ አደሮች እንዳስደሰተ ተጠቆመ።
ኢቲቪ ትላንት ይፋ እንዳደረገው ከተቋቋመ አስራ ዘጠኝ ዓመት የሞላው መስፍን ኢንጂነሪንግ ከስኳር ፋብሪካዎቹ ጋር የገባውን ውል በአስራ አንድ ወራት ውስጥ ለማስረከብ ሃያ አምስት ቶን ብረት ከውጪ አስገብቷል። ስራውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ምክትል ስራ አስኪያጁ አቶ አማኑኤል ገብረኪዳን “መስፍን ኢንጂነሪንግ አገራዊና ግዙፍ ወደ ሆኑ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተዛውሯል” ብለዋል።
መስፍን ኢንጂነሪንግ ቀደም ሲል ሲሰራቸው የነበረውን ስራዎች ለአነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች በማስተላለፍ በከፍተኛ ፕሮጀክቶች ላይ በማተኮር እንደሚሰራ ያስታወቁት አቶ አማኑኤል፣ ድርጅታቸው አዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ በ35ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ከፍተኛና በአይነቱ ልዩ የሆነ ላቦራቶሪ (ካልቸር ሃውስ) በማስገንባት ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።አያይዘውም በቀጣይ ሁለት ዓመታት 30 ሚሊዮን ዶላር ለማትረፍ መታቀዱን ተናግረዋል።
የህወሃት ንግድ ተቋሞች ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመሸጋገር በወርቅ ማዕድን ፍለጋ፣ በአስመጪነትና በላኪነት፣ በባንክና በኢንቨስትመንት በከፍተኛ እመርታ ላይ እንደሚገኙ ወ/ሮ አዜብ መግለጻቸው አይዘነጋም። በቅርቡ ወ/ሮ አዜብ ይፋ ባደረጉት መረጃ መሰረት በቀጣዩ አምስት ዓመታት ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል እቅድ አቶ መለስ በነደፉት መሰረት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ታውቋል።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ሲዘግብ ወ/ሮ አዜብ የባለቤታቸውን የአቶ መለስን ማንነት በሚያጋልጥ መልኩ አስገራሚ መረጃዎችን ማውጣታቸውን ጠቅሶ ነበር። በወቅቱም “ኢትዮጵያ ህዳሴ ባለቤትና ባለራዕዩ መሪ” በመባል በራሱ በህወሓትና በመላው የኢህአዴግ ሰዎች “የሚመለኩት” አቶ መለስ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በጎሳና በቀበሌ ደረጃ ወርደው የሚያስቡ “የጎሰኛነት አባት” መሆናቸውን ባለቤታቸው አሳብቀዋል።
“በተዘዋዋሪ የህዝብ ንብረት ናቸው” ሲሉ የገለጿቸው የኤፈርት እህት ኩባንያዎች ለአስራ ሰባት ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ወ/ሮ አዜብ በወቅቱ ያመለከቱ ሲሆን መስፍን ኢንጂነሪንግ በሶስት፣ አልሜዳ ጨርቃጨርቅ በአምስት እጥፍ እንደሚያድግ፣ መሰቦ ሲሚንቶ የማስፋፊያ ስራውን በማጠናቀቁ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ማስታወቃቸውን ድረገጻችን ጨምሮ ዘግቦ ነበር።
ሰሞኑን ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከኤርትራ ጋር ለመደራደር መፈለጋቸውንና ካስፈለገም ለሰላም ሲሉ አስመራ እስከመሄድ እንደሚደርሱ በተደጋጋሚ መግለጻቸውን አቶ መለስ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ከወጠኑት ዓላማ ጋር የሚያያይዙት አስተያየት ሰጪዎች ዕቅዱ ተግባራዊ እየሆነ በሚሄድበት ወቅት ህወሃት ከኤርትራ ጋር ሰላም መፍጠሩ ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአናት ካለ የዘመናት ባላንጣ ጋር ስምምነት ሳይፈጽሙ ስለ ልማትና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ማውራትም ሆነ ማቀድ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን መጨመር እንደሆነ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ታላቁ መሶብ በባህርዳር
ወጉ እንዳይቀርባቸው የየፓርቲያቸውን የንግድ ተቋማት የመሠረቱት የህወሃት “አቻ” ድርጅቶች በቀጣይ ስለሚሰሩት ስራና አሁን ስለደረሱበት የአቅም ደረጃ ብዙም አለመሰማቱ በደጋፊዎቻቸውና በሚመሩት ክልል ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚታሙ ያስታወሰው የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ በአማራ ክልል በተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች “በፖለቲካ ታማኝነት” መመስገናቸውን አመልክቷል።
በሌላ ዜና ክልሉ በብሄር ብሄረሰቦች ጭፈራ ተይዞ በከረመበት በዚሁ ሰሞን የጣና ሃይቅንና አካባቢውን እያጠፋ ስላለው አረም የክልሉ የሚዲያ ሰዎች ያስተላለፉትን ዜና አስገራሚ ተብሏል። በጣና በለስና አካባቢው በከፍተኛ ፍጥነት የተራባውን አረም ለማጥፋት የአካባቢው አርሶ አደሮች አንድ ለአምስት በተሰኘ አደረጃጀት መጠርነፋቸው ሲነገራቸው የተሰማቸው ደስታ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ተዘግቧል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ይህንን አደገኛ አረም ለማጥፋት “ቁርጠኛነታቸውን ገልጸዋል” በሚል ከክልሉ የተሰራጨው ዜና እንዳመለከተው አርሶ አደሮቹ “አረሙን በማጥፋት የመለስን ራዕይ እናሳካለን” ማለታቸውን አድንቆ ይገልጻል። የአረሙን አደገኛነት የተረዳው የክልሉ መንግስት ሁለት ሚሊዮን ብር መመደቡንና ግብረሃይል ማቋቋሙን ያወሳው ዜና የከብቶቻቸውን መኖና እርሻቸውን፣ ብሎም የውሃ ውስጥ እንስሳትን የሚያጠፋውን ይህንን አረም እስከመጨረሻው ለማጥፋት በመደራጀታቸው የተደሰቱት አርሶ አደሮች አረሙን በማጥፋት ቁርጠኛነታቸውን ያድሳሉ ብሏል።

No comments:

Post a Comment