Translate

Friday, December 28, 2012

የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ እየተበረበረ ነው


ሰነዱን ምዕራባውያን፣ የስለላና የመብት ተቋማት ተርጉመውታል

insa ethiopia


አዲሱ ቴሌ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ/ኢንሳ” በሚል ርዕስ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ያዘጋጀው ጥናታዊ ሪፖርት የታላላቅ አገር የስለላ ተቋማት፣ ለጉዳዩ አግባብ ያላቸው መምሪያዎችና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ትኩረት መሳቡ ታወቀ። ሪፖርቱን አገራቱ በራሳቸው ቋንቋ በመተርጎም የህወሃት/ኢህአዴግን የስለላ መረብ ከተለያየ አቅጣጫ እየመረመሩት ነው።

የጎልጉል ምንጭ የሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እንዳስታወቁት አኢጋን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አዲሱ ቴሌን (ኢትዮ ቴሌኮምን) ከዋንኛው የስለላ መ/ቤት ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ወይም በእንግሊዝኛው (Information Network Security Agency (INSA) – ኢንሳ) ጋር በማጋባት ስለላው በምን ዓይነት መልኩ እንደሚካሄድ በማመልከት ይፋ ያደረገው ባለ 47 ገጽ ሰነድ የተጠቀሱትን ክፍሎች ቀልብ የሳበው ዘገባው በወጣ ማግስት ነበር።
ሪፖርቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሪፖርቱ ባለቤት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዘገባውን ወደ እንግሊዝኛ በመቀየር ሰነዱን የሚጠቀሙ አካሎች እውቅና እንዲሰጡት ተጠይቆ እንደነበር ያስታወሱት የመረጃው ምንጭ፣ አኢጋን ተከታታይ ሪፖርቶችን የማዘጋጀት እቅድ እንዳለውና መረጃው በዋናነት ለኢትዮጵያዊ ወገኖች እንዲደርስ ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ ለጊዜው የትርጉም ስራው ላይ ትኩረት እንደማያደርግ መግለጹን ተናግረዋል። ይሁንና አኢጋን ሪፖርቱን መጠቀም ለሚፈልጉና ተጨማሪ መረጃ ለሚፈልጉ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን በገለጸው መሰረት ሪፖርቱ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች ለመተርጎም በቅቷል።
ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እና ሌሎች የአውሮጳ መንግሥታ ሪፖርቱን ለራሳቸው ለመተርጎም ቅድሚያውን የያዙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ካላቸው አገሮች መካከል ዋና የሚባሉት አስቀድሞ ከሚያደርጉት ጥንቃቄ በበለጠ ከስላለው መረብ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቁ የማስጠንቀቂያ መመሪያ ከተላለፈላቸው ሰነባብቷል።
የደህንነቱን ስራ ከቴሌ ጋር በማገናኘት የተካኑትን የቻይና የቴሌኮም ኩባንያዎች በማስገባትና የአውሮፓን የቴሌኮም ተቋማትን “ወግዱ” በማለት ህወሃት/ኢህአዴግ እንዲሰናበቱ ማድረጉ ዋና ርዳታ ሰጪ አገሮችን ቅር አሰኝቷል። ከዚህም በላይ ከቴሌኮም ንግዱ ጎን ለጎን አገራቱን ከመረጃና ከአጋርነት ማግለሉ የፈጠረው ቅሬታ ቀን ጠብቆ የህወሃት/ኢህአዴግን አመራር ዋጋ እንደሚያስከፍለው የመረጃው ባለቤት ጨምረው ገልጸዋል።
የዓለም ታላላቅ አገሮችን ቀልብ የሳበውና ከፍተኛ መረጃዎችን የያዘው ሪፖርት በአገር ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው በሚሰሩ የኅትመት፣ የድረገጽ፣ የድምጽና ምስል መገናኛዎች ሰፊ ሽፋን አለማግኘቱ የሪፖርቱን ባለቤት ብቻ ሳይሆን በትርጉሙ ላይ የተሳተፉትን አገራት የመረጃ ሰዎችን ያስገረመ ጉዳይ እንደነበር፣ ይሁንና በቅርቡ ሪፖርቱ ህይወት ዘርቶ በሁሉም ወገን እንደ ሰነድ የሚወሰድ እንደሚሆን የንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት ክፍል ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በላከው የኢሜይል መልዕክት ተናግሯል። በመልዕክቱ ስማቸውን መዘርዘር ባያስፈልግም የተለያዩ የስለላ ድርጅቶችና አገሮች ሪፖርቱ በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ክፍሉ ገልጾዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ወይም በእንግሊዝኛው (Information Network Security Agency (INSA) አኢጋን ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት እለት ድረስ መቃወሚያም ሆነ ማስተባበያ አላቀረበም። ኢንሳ በቻይና የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ አማካይነት የዜጎችን እንቅስቃሴ ወደ መረጃ ቋት ውስጥ በማስገባት የሚያካሂደው ስለላ፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ላይ እንዲሁም ኤምባሲዎች ላይ የሚያካሂደው ክትትልና በንጹሃን ላይ በሚፈጽመው አፈና በቅርቡ ይፋ የሚወጣ ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ሊቀርብበት እንደሚችል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አመልክተዋል።
ኢህአዴግ በደቡብ ሱዳን የሚያካሂደውን ጣልቃ ገብነትና ጥቅምን የመጋራት “ወረራ” እና የህወሃት ወገን የሆኑ ነጋዴዎች በጁባ ስለሚያካሂዱት ስለላ አኢጋን በዝርዝር አቀርበዋለሁ ያለውን ተጨማሪ መረጃ አስመልክቶ በጥልቀት እየሰራበት መሆኑን ለጎልጉል አስታውቋል። መረጃውን መቼና እንዴት በምን ዓይነት መልኩ ይፋ እንደሚያደርግ ግን ቀን ቀጥሮ አላስታወቀም።

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ሕዝብ ግንኙነት ባገኘው ፈቃድ መሠረት “አዲሱ ቴሌና ኢንሳ፡ የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ” በሚል ርዕስ የወጣውን ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡ አኢጋን በዘገባው ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው ጽሁፉን “ለማስተማሪነት፣ የቅስቀሳ ዘመቻ ለማካሄድ፣ ለጥናትና ምርምር እንደ ምንጭ በመጥቀስ ያለ ምንም ክፍያ መጠቀም ይቻላል፡፡”

“አዲሱ ቴሌ”
እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት
ኤጀንሲ (ኢንሳ)፡

የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከሚያካሂዳቸው በርካታ ተግባራት በተጨማሪ ላለፉት ወራት የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያካሄደውንና ሊያካሂድ ያሰበውን የስለላ ተግባር ሲመረምር ቆይቷል፡፡ በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አዲሱ ቴሌን (ኢትዮ ቴሌኮምን) ከዋንኛው የስለላ መ/ቤት ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ወይም በእንግሊዝኛው (Information Network Security Agency (INSA) – ኢንሳ ጋር በማጋባት ስለላውን በምን ዓይነት መልኩ ለማካሄድ እንዳሰበ የሚያትት ባለ 47 ገጽ ግርድፍ ዘገባ አቅርበናል፡፡
“አዲሱ ቴሌ” እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፡ የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ መረብ በሚል ርዕስ የቀረበው ይህ መረጃ በኢትዮጵያችን የተካሄደውንና በመካሄድ ላይ ያለውን የአፈና መዋቅር በጥቂቱ የሚያወሳ ነው። ዘገባው የህወሃት/ኢህአዴግ የደኅንነትና የአፈና ተቋማት ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር እንዴትና ለምን እንደተቆራኙ፣ የምዕራብ አገራት የቴሌኮም ቴክኖሎጂ የተገፋበትን ምስጢር፣ አዲሱን ቴሌ ከአገር ወዳዶች በማጽዳት የህወሃት/ኢህአዴግን ፖለቲካና ስውር አጀንዳ ማስፈጸም ይችላሉ ተብለው ለታመነባቸው ክፍሎች ወይም የአገዛዙ “ቁሶች” እንዲዛወር የተደረገበትን ምክንያት፣ በፖለቲካ ድርጅቶችንና ኃላፊዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) ላይ የሚካሄደውን ስለላ በመጠኑ ለማሳየት ጥረት ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም ይህንን የስለላ መረብ በመጣስ ሕዝባችን ትግሉን በምን ዓይነት መልኩ ማከናወን እንዳለበትና እንዴት የመረጃ ጫካ ውስጥ በመግባት መደበቅ እንደሚቻል የተወሰኑ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

No comments:

Post a Comment