Translate

Saturday, December 8, 2012

በባህርዳር ለሚከበረው 7ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት 200 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉ ታወቀ


ኢሳት ዜና:-ኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጡት በአሉን ለማክበር የወጣው ገንዘብ እስካሁን ባለው ግርድፍ መረጃ 200 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ሂሳቡ ሲወራረድ ወጪው ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል ተብሎአል።ህዳር ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

በትናንትናው  ዕለትም በ20 ሚሊየን ብር የተሰራችው ህዳሴ የተሰኘች መርከብ የከተማዋ ነዋሪዎች፣እንግዶች፣ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቃለች፡፡ህገመንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 የብሔርብሔረሰቦች በዓል ሆኖ እንዲከበር የፌዴሬሽን ም/ቤት በወሰነው መሰረት በዓሉ በፈንጠዝያና በግብዣ በየዓመቱ ሲከበር ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ ነው፡፡
የበዓሉ ማጠቃለያ ከ550 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ወጥቶበት በመገንባት ላይ ባለው የባህርዳር ስታዲየም ተጠናቋል
በተለይ በዓሉን በፌሽታ ለማሳለፍ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ብክነት መሆኑን አንድ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪ ጠቁመው የብሔርብሔረሰቦች መብትና ጥቅም እንዲሁም የሕገመንግስቱ ፍሬሃሳቦች የሚከበሩት መልካም አስተዳደር፣ግልጽነትና ተጠያቂነትን በመዘርጋት በስራ እንጂ በፌሽታ ሊሆን አይችልም ብለዋል፣ ዘጋቢያችን ከባህርዳር እንደገለጠው።
አቶ ሀይለማርያም በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ሰራተኞቹ በድብቅ ካምፕ ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው አጋዚዎቹ ሲያሸብሩዋው መዋላቸው ታውቋል። ሰራተኞች ፕሮጀክቱን የሚመራው ጠፍቷል፣ የሰራተኛው መብት ታፍኗል በማለት አቤቱታ ሲያቀርቡ ይሰማል።
የኢሳት ዘጋቢ ከባህርዳር እንደገለጸው ከከተማው የተሰበሰቡ ነድያን ጅንአድ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተሰብስበው በአንድ ቦታ እንዲከማቹ ከተደረገ በሁዋላ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በልተው ይስተረፉት ተረፈ ምርት እየቀረበላቸው መሆኑን ገልጿል።
አንዲት ወጣት ለዚህ በአል የወጣው 200 ሚሊዮን ብር በከተማው የሚታየውን የስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር በብዙ እጅ ለመቀነስ ይጠቅም ነበር ስትል አስተያየቱዋን ሰጥታለች።
ኢህአዴግ ጫካ በነበረበት ጊዜ ደርግ ህዝቡን እያስራበ ለ10ኛው አብዮት በአል ከፍተኛ ገንዘብ አወጣ በማለት ይተች ነበር።

No comments:

Post a Comment