Translate

Monday, December 17, 2012

የጎልጉል ቅምሻ


(ከዚህም ከዚያም)

iron phone


ካውያ እንደ ስልክ
ባለቤቱን በርካታ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ መሥራት እንደሚችል በማሳየት ለማስደሰት ቆርጦ የተነሳው ፖላንዳዊው ባል እንዳሰበው አልሆነለትም፡፡
ባለቤቱ ከሥራ ስትመጣ ማከናወን የሚገባውን ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ ሳይፈጽም መቅረቱ ሁልጊዜ የሚያሳስበው ባል ቴሌቪዥኑን ለኩሶ ከጎኑ ቢራውን እየተጎነጨ ልብስ መተኮስ ጀመረ፡፡
በመካከል ስልኩ ሲያንቃጭል እጁ ላይ ያለው የጋለ ካውያ ስልክ የመሰለው አባወራ ካውያውን ጆሮው ላይ በመደገን ባደረሰው ጉዳት አሁን በአንድ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን በተመለከተ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች እጅግ ደካማ እንደሆኑ አስመስክሯል፡፡ ከእንግዲህ ወደቤት ሥራ እንደማይመለስ የተናገረው ባል ጉዳዩ ሲያት ቀላል እንደሚመስል ከዚህ በኋላ ግን ለባለቤቱ ተገቢውን ክብር እየሰጠ አርፎ እንደሚቀመጥ ተናግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ አራት ጊዜ ቃለመሃላ ሊፈጽሙ ነው
በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አራት ጊዜ ቃለመሃላ በመፈጸም ለ12ዓመታት በፕሬዚዳንት መንበር ላይ ከቆዩት ሩዝቬልት ጋር እኩል ሊሆኑ ነው፡፡
የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ ሲመረጡ ቃለመሃላ በሚገቡበት ወቅት የጠቅላይ ፍርድቤቱ ዳኛ በፈጸሙት የቃላት ግድፈት ምክንያት መሃላው በግል ተደግሞ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሕገመንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ጃኑዋሪ 20 ፕሬዚዳንቱ ቃለመሃላ መፈጸም የሚገባቸው ሲሆን ቀኑ እሁድ ላይ በመዋሉና ቃለመሃላ እሁድ የማድረግ ልምዱና አሠራር ስለሌለ በ20 በግል ቃለማሃላ ከፈጸሙ በኋላ በ21 በይፋ እንደገና ይፈጽማሉ፡፡
ባራክ ሁሴን ኦባማን በድብቅ ሙስሊም ናቸው በማለት የሚወነጅሏቸው አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩን በቀላሉ አላዩትም፡፡ ጃኑዋሪ 20 በግል በቁርዓን ላይ እጃቸውን በመጫን መሃላ ያደርጋሉ በኋላ ግን በማግስቱ በይፋ መጽሐፍቅዱስ ላይ ጭነው ቃለመሃላ ይፈጽማሉ በማለት ያልተረጋገጠ ወሬ እያሰራጩ ይገኛል፡፡
ድቡልቡል ባቤል
ወደፊት የሚመጣው አይታወቅም – የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ሱናሚ፣ … ቢከሰት ማምለጥ አለብኝ፤ ቤተሰቤንም ማዳን አለብኝ በሚል ቻይናዊው ገበሬ እንደ ኖህ መርከብ ወይም ከጥፋት ውሃ በኋላ እንደነበሩት ሰዎች ሰማይጠቀስ የባቤልን ፎቅ ሳይሆን እንደ ኳስ ድቡልቡል የሆነና በውሃ ላይ ያለምንም ችግር የሚንሳሰፍ ማምለጫ አዘጋጅቷል፡፡
ይኸው እስከ 14ሰዎችን መያዝ የሚችለው መጠለያ መገለባበጥ እንዳይኖር የወንበር ቀበቶ ሲኖረው፤ የኦክሲጂን ማጠራቀሚያ እና ሌሎች ጠቃሚ ነገሮችን ያካተተ ነው፡፡ በውሃ ላይም ወደላይ በመሆን ሁልጊዜ እንዲንሳፈፍ የሰራውን የፈጠራ ዕቃ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማት ሱናሚ፣ የመሬት መንቀጥቀጥን፣ ወዘተ ለመከላከል ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ተስፋ አለው፡፡
የእጅ ስልክና ቲቪ ለልጆች ጸረትምህርት ነው ተባለ
በ4ሺህ ተማሪዎች ላይ በእንግሊዝ አገር በተደረገ ጥናት በመኝታ ክፍላቸው ቴሌቪዥን ያላቸው እና የእጅ ስልክ ያላቸው ልጆች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ጥናቱ አረጋግጦዋል፡፡
በተለይ እነዚህን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ የማንበብና አንብቦ ጥያቄዎችን የመመለስ ውጤታቸው ከማይጠቀሙት በ20 ነጥብ እንደቀነሰ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በአንጻሩ የሙዚቃ መሣሪያ ያላቸው ልጆች ውጤታቸው በ30ነጥብ እንደጨረመ ተነግሯል፡፡ በማኅበራዊ ድረገጾች (እንደፌስቡክ፣ ማይስፔስ፣ እና የመሳሰሉት) ላይ በርካታ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ልጆች በሳይንስና ሒሳብ እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ጥናቱ ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ከፍትፍቱ ፊቱ
መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለሠራዊቱ አባላት ልጆች እስከ 900 የሚደርስ ስጦታ ሲያድሉ የዋሉት ቀዳማይ እመቤት ሚሼል ኦባማ ከስጦታው ጋር ፈገግታ አለማሳየታቸውን በተለይ የእንግሊዝ ጋዜጦች ሚሼልን “ፈታ፤ ፈገግ” እንዲሉ በነገር ወጋ አድርገዋቸዋል፡፡
የሠራዊቱ ቤተሰብ የሚከፍለው መስዋዕትነት ታላቅ የመንፈስ መነቃቃት እንደሚሰጣቸው የተናገሩት እመቤት ኦባማ ባለቤታቸው ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የሠራዊቱን ቤተሰብ በማጽናናት፣ በማገዝ፣ በመደገፍ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡
12ዓመት በ12/12/12 12፡12
ባለፈው ረቡዕ የአውሮጳውያኑ 12ኛ ወር 12ኛ ቀን ሲሆን ዕድሜው 12ዓመት እንደሆነ የተነገረለት ልጅ ቤተሰቡ ጉዳዩ በቀላሉ እንዲታይ ይገባዋል ይላሉ፡፡
“ልጄ የተወለደ ጊዜ ለልደት ሰርተፊኬቱ ቅጽ ስታስሞላኝ የነበረችው ሴት ልጄ በ12ኛው ወር በ12ኛው ቀን በ12ኛው ሰዓት በ12ኛው ደቂቃ ላይ መወለዱን ስትነግረኝ ትንሽ ትንሽ ተደናግሮኝ ነበር” የሚለው ከጃፓን ተሰድዶ አሜሪካ የሚኖረው አባት ባለፈው ረቡዕ ልጁ 12ኛውን ዓመቱን ማክበሩን ገለጾዋል፡፡ በርካታ የምጽዓት ቀን ናፋቂዎች በበዙበት ዘመን ጉዳዩን ቀለል አድርጎ መታየት እንዳለበትም ሳይጠቁም አላለፈም፡፡
“ኦባማ የሻሪያ ህግ በአሜሪካ ለመተግበር ይፈልጋል”
ከሜኖሶታ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑትና አክራሪ የክርስትና አመለካከታቸው የሚታወቁት ሚሼል ባክማን ፕሬዚዳንት ኦባማ በአሜሪካ እስላማዊ አጀንዳን ለማስፋፋት እንዲሁም የሻሪያን ሕግ ለመተግበር እንደሚፈልጉ አስታወቁ፡፡
የአዶልፍ ሒትለር አካሄድ ለማወቅ ሰዎች “ትግሌ (Mein Kampf)” በተሰኘው የሒትለር ጽሁፍ ላይ የጠለቀ ጥናት እንዳደረጉ ሁሉ አሁንም የፕሬዚዳንቱን አካሄድ ለመገንዘብ አሜሪካውያን እስላማዊ ጥቅሶችን በጥንቃቄ ማጥናት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ የምክርቤት አባሏ የኦባማ አስተዳደር የእስላማዊ ጉባዔ ድርጅትን ይደግፋል በማለት የሚከስሱ ሲሆን የሒላሪ ክሊንተን ረዳት የሆኑትን ሁማ አቤዲን ቤተሰቦቻቸው (ሟች የሳዑዲአረቢያ ተወላጅ አባታቸውን፣ የፓኪስታን ተወላጅ እናታቸውን፣ …) ከሙስሊም ወንድማማች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው በማለት የኦባማ አስተዳደር እስላማዊነትን እንደሚደግፍ እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ ባለፈው ሐምሌ ወር ከሚሼል ባክማን ጋር በመሆን ሌሎች አራት አክራሪ የም/ቤት አባላት ከጽንፈኛ ሙስሊሞች ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ወደ አሜሪካ ፌዴራል መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሰርገው ገብተዋል በማለት በይፋ ክስ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል፡፡
ጳጳሳዊ ትዊት
“ወዳጆቼ በትዊተር አማካኝነት ከእናንተ ጋር በመገናኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለመልካሙ ምላሻችሁ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ሁላችሁንም ከልቤ እባርካችኋለሁ፡፡” ይህንን የመጀመሪያ የትዊተር መልዕክት ራሳቸው ያስተላለፉት የሮማው ካቶሊክ ጳጳስ አቡነ ቤኔዲክት ናቸው፡፡
ለበርካታ ወራቶች ሲጠበቅ በነበረው በዚህ የመጀመሪያ መልዕክት የ85ዓመቱ ጳጳስ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ተከታዮቻቸው መልካሙን የተመኙ ሲሆን ወደፊት ግን በረዳቶቻቸው አማካኝነት በበርካታ ቋንቋዎች ሲላኩ እርሳቸው እንዲፈርሙባቸው ይደረጋል፡፡ የእኛስ የሃይማኖት መሪዎች …?
ኦባማዶን
የዛሬ 65ሚሊዮን ዓመት ዝርያው የጠፋው የዳይኖሱር ዘር ሳይንቲስቶች በኦባማ ስም በመሰየም ኦባማዶን በማለት ጠርተውታል፡፡
ይኸው ትናንሽ ነፍሳትን የሚመገበው የእንሽላሊት ዳይኖሱር የተገኘው የዛሬ 40ዓመት አካባቢ በአሜሪካ የሞንታና ጠቅላይግዛት ነው፡፡ ጥርሱ የፕሬዚዳንቱን ይመስላል በማለት ዳይኖሱሩን በባራክ ኦባማ ስም እንደሰየሙት ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል፡፡
የሳምንቱ ምርጥ ፎቶ
ምስሉን ያገኘነው ከፌስቡክ ነው፡፡ “ድሮና ዘንድሮ ምን ይመስላሉ?” ብሎ ለሚጠይቅ ብዙ ምስክርነት ይሰጣል፡፡
ዘገባውን ለማጠናቀር በየጽሁፉ ከጠቀስናቸው ምንጮች በተጨማሪ ሌሎችንም የሚዲያ ውጤቶች መጠቀማችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከዜናዎቹ ማነስ አኳያ በየጸሁፉ ለመግለጽ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment