Translate

Saturday, December 22, 2012

ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ የሞራልና ተፈጥሮዓዊ ግዴታ



ወያኔ/ኢህአዴግ የሰላማዊ በሮችን ሁሉ በመዝጋት በሀይል እየገፋና እየደፈጠጠ ስለ ሰላም የሚያወሩትን፣ ነጻነት የሚጠይቁትን፣ እንደወንጀለኛና ሽብርተኛ ታርጋ እየሰጠ ዴሞክራሲን ማፈኑ፣ ነጻነታችንን መግፈፉና የፖለቲካውን ምህዳር ማጥበቡ፤ የሀገራችን ህዝብ ሆ! ብሎ የተዘጋውን የሰላም በር ለማስከፈትና እንደ አረቡ አለም ጸደይ አቢዎት ተባብረን ስርአቱን የምናስወግድበት ቀን ሩቅ አይሆንም።
ሰሞኑንንም በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይኼው የሰላሙ ትግል ተዳፍኖባቸው ለቀበሌና ለወረዳ ማሟያ በሚደረገው ምርጫ አንሳተፍም ብለዋል። ወያኔ ለዚህ ሁሉ ህዝብን ወደ አላስፈላጊ አማራጭ መግፋቱ አሁንም በታሪክ ተጠያቂ ያደርገዋል። በእኛ እምነት በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ ማናቸውንም አማራጭ ሀሳቦችን ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት መወያየት ስልጡን የሆነ፣ ስልጣን የህዝብና በህዝብ የሚመጣ መሆኑን ማረጋገጫ ስለመሆኑ አሁንም ደግመን ደጋግመን እንናገራለን።
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኖቭል የሰላም ሽልማት ሲቀበሉ ሰላማዊ የትግል አማራጭ ከወታደራዊ መፍትሄ እጅግ የተሻለ ስለመሆኑ የማያከራክር ቢሆንም በሰላማዊ መንገድ ብቻ ተጉዞ ሰላምን ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩ፤ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ኃይልን መጠቀም ግዴታ ብቻ ሳይሆን ከሞራል አንፃር ተገቢ ስለመሆኑ ያብራሩበት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎችና ሁኔታዎች የኃይል አማራጭ ተገቢነት እየጨመረ መምጣቱን እና ለሰላም ሲባል ደም አፍሳሽ ጦርነት ውስጥ እንኳን ሊገባ እንደሚችል ማስረጃዎችን በመጥቀስ  ያስገነዘቡበት ነው:: ወያኔ/ኢህአዴግ ደግሞ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው።

ባራክ ኦባማ ሲናገሩ “ እውነቱን በመቀበል እንጀምር − ብጥብጥ ያለበት ቅራኔን በእኛ እድሜ ማስቀረት አንችልም። ለወደፊቱም  ሕዝቦች − በግልም ሆነ በጋራ − ኃይልን መጠቀም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ከሞራል አንፃርም ተገቢ የሚሆንበት ሁኔታ ይኖራል”
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁለገብ ትግልን እንደ አማራጭ ሲያቀርብ የሰላማዊ ትግልን ውበት በመጠራጠር አልነበረም። ሰላምን መመኘት፣ ስለሰላም መዘመር፣ ስለሰላም ማስተማር፣ ስለሰላም መስበክ በእርግጥ ሰላምን ያስገኛል? ሰላም የሚደፈርሰው ሰዎች ስለሰላም ጥሩነት በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ነውን? በጭራሽ! ሰላምን መመኘት፣ ስለሰላም መዘመር፣ ማስተማርና መስበክ ጥቅም ቢኖራቸውም ሰላምን ለማስገኘት በቂ አይደሉም፤ ሆነውም አያውቁም። ፕሬዝዳንት ኦባማ በዚሁ ንግግራቸው ያሉትም ሲቪል ዜጎች በገዛ መንግሥታቸው የሚታረዱበት ሁኔታ፤ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወይም አንድን የዓለም አካባቢ ሊያምሱ የሚችሉ ብጥብጦችና ሰቆቃዎችን ለመከላከል ኃይልን የመጠቀም አማራጭ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ስለሆንም ወያኔ እየገፋን፣ በሀገራችን ዘረኝነትን እያነገሰብን፣ የዴሞክራሲን ጮራ እያጠፋብን፣ የነጻነት ብርሃንን እያጨለመብን ባለበት ሰአትም ሰላም ኃላፊነት መቀበል ነውና ስለ ሰላም መስዋዕትነትን እንከፍላለን።
በሰላም ስም ባርነትን ማስፈን የአምባነገነኖች አንድ የጋራ ባህርይ ነው። አምባገነኖች ሰላም ማለት ሁሉም ሰው ከገዢዎች ተቆንጥሮ የሚሰጠውን መብት አመስግኖ ተቀብሎ፤ እንዲጫወት የታዘዘውን ባህርይ እየተጫወተ መኖር ማለት አድርገን እንድንወስድ ይፈልጋሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰላም፣ ነፃነትና ክብር የማይነጣጠሉ ነገሮች መሆናቸውን ነው። ስለ ሰላም ማሰብ የምንፈልገው ሙሉ ስብዕናችን በተረጋገጠበት ሁኔታ እንጂ ስብዕናችን በተዋረደበት ጊዜ ያለው አስፈሪ ዝምታ ማለት አይደለም።
ኦባማም እየተናገሩ ያሉት “ሰላም የሚታይ ብጥብጥ አለመኖር ማለት አይደለም። ፍትሃዊ ሰላም ዘላቂነት የሚኖረው በእያንዳንዱ ግለሰብ ተፈጥሮዓዊ መብቶችና ክብር ላይ የተገነባ ሲሆን ነው።… ዜጎች የመናገር፣ የማምለክ፣ መሪዎቻቸውን የመምረጥ ወይም ያለፍርሃት የመሰብሰብ ነፃነታቸው በተገፈፉ ጊዜ ዘላቂ ሰላም አይኖርም።” ከዚህ ምን እንማራለን? መልሱ ለእኛው ለኢትዮጵያውያን ይሆናል..
እኛ ኢትዮጵያውያንም እንደ ዜጋ የመናገር፣ መሪዎቻችንን የመምረጥና የመሰብሰብ፣የእኩልነት መብት ማጣት ብቻ አይደለም የተፋጠጥነው። የዛሬ መብቶቻችንን ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋችንንም ሊያጨልምብን ከሚሞክር መሰሪ ሥርዓት ጋር ነው። በወያኔ አገዛዝ ዜጎች ተዋርደውና ተሸማቀው አሜን ብለው እንዲገዙ መደረጉ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝብና እንደ አገር የመቀጠላችን ጉዳይ አጠራጣሪ እየሆነ በመምጣቱ ነፃነታችንና አንድነታችንን፣ ክብራችን የተጠበቀበት ሰላም ለማምጣት ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ የሞራልና ተፈጥሮዓዊ ግዴታችን እና ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment