Translate

Monday, December 10, 2012

መስተዳድሩ የሚድሮክን ሁዳ ሪል ስቴት መሬት ነጠቀ


ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር እንደዘገበው  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ለሚገኘው ሁዳ ሪል ስቴት ሜክሲኮ አደባባይ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ ሰጥቶት የነበረውን የግንባታ መሬት  የነጠቀው  መሬቱን ከተረከበ ካለፉት 8 አመታት ጀምሮ ግንባታ ባለማካሄዱ ነው፡፡ 6ሺ 400 ሄክታር ስፋት ያለው መሬት የተሰጠው  ከፍታቸው ከ20 ፎቅ በላይ የሆኑ መንትያ ሕንፃዎች እንደገነቡበት ነበር።ታህሳስ ፩(አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ በሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕና በደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሥር ካሉዋቸው በርካታ ኩባንያዎች መካከል፣  ሁዳ ሪል ስቴት፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን፣ ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ሚድሮክ ፋውንዴሽን በግንባታሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡


የሁዳ ሪል ስቴት የሜክሲኮ አደባባይን ፕሮጀክት መሬት የነጠቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ሁዳ ሪል ስቴት በመሀል ፒያሳ ከከተማው አስተዳደር ሕንፃ ፊት ለፊት የተሰጠውን መሬትም እንደሚነጥቅ በቅርቡ ማስጠንቀቁን ጋዜጣው ዘግቧል።ሚድሮክ ከ15 ዓመታት በፊት በመሀል ፒያሳ 36 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ቢሰጠውም እስካሁን ግንባታውን አላከናወነም።
በሼክ አላሙዲ ስም የተያዙ በአዲስ አበባም ሆነ በመላ አገሪቱ እጅግ ሰፋፊ የሆኑ መሬቶች ሳይለሙ ታጥረው ተቀምጠዋል።  አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ግንባታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ካላከናወኑ መሬታቸው እንደሚወሰድባቸው በተደጋጋሚ በመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሲነገር ቢሰማም፣ ሼክ አላሙዲ በአንዳንድ ቦታዎች ከ15 አመታት በላይ መሬት አጥረው ቢቀመጡም እርምጃ ሲወሰድባቸው አይታይም። ጉዳዩን የታዘቡ ሰዎች አላሙዲንን በመንግስት ውስጥ ያሉ መንግስት በማለት ይጠሩዋቸዋል። የአዲስ አበባ መስተዳዳር በምን ድፍረት ይህን እርምጃ ለመውሰድ እንደተነሳሳ ግልጽ አይደለም። መስተዳዳሩ እንዳለው የፒያሳውን መሬት መልሶ የሚወሰድ ከሆነ ሼክ አለሙዲን በስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ጋር የነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት እየላላ መምጣቱን የሚያመላክት ሊሆን ይችላል በማለት አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ።
ሼክ አላሙዲን በአለም ካሉት ሀብታዎች መካከል በ46ኛ ደረጃ በአፍሪካ ደግሞ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment