Translate

Monday, December 10, 2012


የጎልጉል ቅምሻ

(ከዚህም ከዚያም)
Lin
በምስራቅ ቻይና የዢያንግ አውራጃ የኒቂያዖ ፖሊስ የደረሰው ክስ ግራ የሚጋባ ሆኗል፡፡ የ41ዓመቱ ፌ ሊን “ተኝቼ ሳለ ሌቦች ክፍሌ በርግደው በመግባት ብልቴን ሰረቁት” በማለት ነበር ወንጀሉን ያብራራው፡፡ ሲቀጥልም ሌቦቹ ቤቱ እንደገቡ ጭንቅላቱ ላይ የሆነ ነገር አድርገው ሱሪውን ወደታች ካወረዱ በኋላ ሮጠው እንደጠፉ አስረድቷል፡፡ “በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ምንም የተሰማኝ ነገር አልነበረም፤ በኋላ ግን እየደማሁ መሆኔን ሳስተውል ብልቴ ተበጥሶ መሄዱን አስተዋልኩ” ብሏል፡፡

ፖሊስ እንደሚለው ሌቦቹ ሊን በሚያዘወትራቸው በርካታ ሴቶች የቀኑ አፍቃሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምት በመስጠት ፍለጋውን ቀጥሏል፡፡ ሊን ግን ይህንን የፖሊስ መላምት ካለመቀበል በተጨማሪ የትም ሂያጅ ሳይሆን ታማኝ እንደሆነ ለራሱ ይመሰክራል፡፡ በስርቆቱ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ቢሆንም በርካታዎች ግን “የት አስቀምጦት ነው ሊሰረቅ የቻለው” በማለት የመከራከሪያ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡
ከፊልም ሙያ ወደ ምክርቤት
ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይ አሽሊ ጀድ የዴሞክራቲክ ፓርቲን በመወከል ለአሜሪካ የህግ መወሰኛ ም/ቤት (ሴኔት) ልትወዳደር እንደምትችል በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የባራክ ኦባማ ደጋፊ የሆነችው አሽሊ የምትወዳደረው ከኬንታኪ ጠቅላይ ግዛት ሲሆን ተፎካካሪዋም በመወሰኛው ም/ቤት የሪፓብሊካኑ ንዑሳን መሪ የሆኑት ሚች ማኮኔል ናቸው፡፡
አብዛኛውን የፊልም ኢንዱስትሪና ታዋቂነትን ይዛ ወደ ዘመቻ የምትገባው አሽሊ ውሳኔዋን አሳውቃ ለውድድር የምትቀርብ ከሆነ እጅግ በርካታ ደጋፊዎቿ ከሌሎች ጠቅላይግዛቶች በመምጣት ለምርጫ ዘመቻ በፈቃደኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል እየገቡ ይገኛል፡፡
ከቶ አይቀር ሞቱ ምንም ቢረዝሙ
የዓለማችን ረጅሟ ሴት ቻይናዊቷ ያዖ ደፈን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ የ39ዓመቷ ረጅም የዛሬ ሁለት ዓመት በዓለም የድንቆች መዝገብ የዓለማችን ረጅም ሴት በመባል ተመዝግባ ነበር፡፡ 7ጫማ ከ7ኢንች (2ሜትር ከ33ሴ.ሜ.) የምትረዝመው ያዖ የሞተችበትን ምክንያት የቻይና ዜና ባያስታውቅም የረጅምነት በሽታ (ጃይጋንቲዝም) እና ሌሎች ስትሰቃይ ቆይታለች፡፡
ወጣት ሳለች የቅርጫት ኳስ ትጫወት የነበረችው ያዖ በ15ዓመቷ 6ጫማ ከ7ኢንች (ሁለት ሜትር) ትረዝም ነበር፡፡ በበሽታ ትሰቃይ ከነበረችበት አልጋ ሆና “በፍጹም ደስተኛ አይደለሁም፤ ለምን ይህንን ያህል ረጅም ሆንኩ? ይህንን ያህል ባልረዝም ኖሮ ሰዎች እንደዚህ አይመለከቱኝም” በማለት የዛሬ ሦስት ዓመት ሃዘኗን መግለጽዋ ተዘግቧል፡፡
“አላሁ አክበር” በቤተክርስቲያን
የሙስሊም ሕዝብ ጉዳዮች ምክርቤት (MPAC) ለመጀመሪያ ጊዜ ዓመታዊውን ስብሰባ በቤተክርስቲያን ሊያደርግ ነው፡፡ በፓሳዴና ካሊፎርኒያ በሚገኘው የሁሉም ቅዱሳን ኤጲስቆጶሳዊ ቤ/ክ (All Saints Episcopal Church) እንደሚካሄድ የተነገረለት ይኸው የሙስሊሞች ስብሰባ እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰበት ይገኛል፡፡
“በመቻቻል ስም ኢስላሚስቶች ጅል በሆኑ ክርስቲያኖች እየተጠቀሙ ነው”፤ “የአገራችንን (የአሜሪካንን) ሕገመንግሥት ለማፍረስና የሻሪያ ሕግ ለማስፈን ከሚሰራ ድርጅት ጋር በማበር የአገሬንና የልጅ ልጆቼን መጻኢ ዕድል አደጋ ላይ በመጣላችሁ ተጠያቂዎች ናችሁ” የሚሉ ጠንካራ መልዕክቶች የደረሷቸው መሆኑን የገለጹት የቤክኑ አስተዳዳሪዎች ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ የደኅንነትና የፖሊስን ድጋፍ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ የምክርቤቱ ፕሬዚዳንት ሳላም አልማራያቲ “እንደቀድሞው ሁሉ ስብሰባውን በሆቴል ወይም በስብሰባ አዳራሽ ማድረግ እንችል ነበር፤ ሆኖም ቤ/ክ ውስጥ ማድረጋችን ም/ቤታችን ለሰላም እና ፍትሕ የቆመ ለመሆኑ ማሳያ እንዲሆን በመፈለጋችን እና ለሙስሊሞችም እርስበርሳቸው እየተነጋገሩ ችግራቸውን ይዘው ከሚኖሩ ለአብዛኛው የአሜሪካ ሕዝብ መልዕክታቸውን እንዲያደርሱ ታስቦ የተደረገ ነው” ይላሉ፡፡ አክራሪ የክርስቲያን ተቋማት መሪዎች የሙስሊሙን ም/ቤት በእጅ አዙር ለአሸባሪዎች ዕርዳታ የሚሰጥ ራሱ አሸባሪ የሆነ ድርጅት ነው በማለት ይከስሳሉ፡፡ የመንግሥትና ሃይማኖትን ጥምረት የሚቃወሙም እንዲህ ዓይነቱን የመንግሥት ድጋፍ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ አጥብቀው ያወግዛሉ፡፡
ከ6ሴቶች 9ልጆች
በአሜሪካ የዊስኮንሲን ጠቅላይግዛት ነዋሪ የሆነው ኮሪ ከርቲስ ከስድስት የተለያዩ ሴቶች ዘጠኝ ልጆችን በመውለዱ ቤተሰቡን በሚገባ ማስተዳደር እስከሚችል ድረስ “መራባት እንዲያቆም” ፍርድቤት ወስኖበታል፡፡
ወደ 90ሺህ ዶላር ያልተከፈለ የልጆች ማሳደጊያ ድጎማ ዕዳ ያለበት የ44 ዓመቱ ዕዳውን ከፍሎ እስኪጨርስ ድረስ 10ኛ ልጅ መጨመር እንደማይችል ዳኛው ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በኬንታኪ ጠቅላይ ግዛት ከ11ሴቶች 12ልጆችን የወለደውን “አቶ ዘረብዙ” 13ኛ ልጅ እንዳይጨምር መራባት እንዲያቆም የወሰኑበት ዳኛ በአመክሮ በሚቆይበት ከ1 እስከ 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከወሲብ እንዲታቀብ ትዕዛዝ ሰጥተውታል፡፡ የሁለቱም ፍርድቤት ውሳኔዎች አፈጻጸም ግን በውል አልታወቀም፡፡
ፕሬዚዳንት ሂላሪ ክሊንተን?
የዛሬ አራት ዓመት ለፕሬዚዳንትነት ፓርቲያቸውን ወክለው በመወዳደር በባራክ ኦባማ የተሸነፉት ሂላሪ ሮድሃም ክሊንተን በ2016 ዳግም ለፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ የሚል ወሬ በስፋት እየተናፈሰ ነው፡፡ በቅርቡ በተጠናቀቀው ምርጫ የተሸነፉ የፓርቲያቸውን እጩዎች የሚያበረታታ በራሳቸው እጅ የተፈረመ ደብዳቤ መላካቸው በተንታኞች ዘንድ በቀላሉ አልታየም፡፡ ምዕራብ ኒውዮርክን በመወከል ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው በጠባብ ውጤት ለተሸነፉት ኔት ሺናጋዋ በላኩት ደብዳቤ ላይ በአሁኑ ምርጫ ቢሸነፉም በቀጣይ ዓመታት በህዝባዊ መድረኮች ላይ የእርሳቸውን ድምጽ እንደሚሹ ሂላሪ ክሊንተን ጠቁመዋል፡፡
ባራክ ኦባማ በዚህኛው የምርጫ ዘመቻቸው መሪቃል ወደፊት (Forward) የሚል እንደነበር ሁሉ ሂላሪ ክሊንተን በደብዳቤያቸው ላይ “Onward” በማለት የጠቀሷት ቃል ምናልባት የምርጫ ዘመቻቸው የመፈክር ቃል ትሆን የጎልጉል ግምት ነው፡፡ መቆየት ደጉ ብዙ ያሰማናል፡፡
ባለሦስት እግሩ በራሪ
የሥራ ሰዓት ሲረፍድ፤ ታክሲ ሲጠፋ ወይም መንገዱ በትራፊክ ሲጨናነቅ፤ ሰዓቱ ሲበር በሰማይ መብረር ያሰኛል፡፡ በእርግጥ መብረር ይቻላል፡፡
መፍትሔው 75ሺህ ዶላርና የፓይለት መንጃፈቃድ ማውጣት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ አንዴ ነዳጅ ሞልቶ ለ5ሰዓታት መብረር ነው – በበራሪው ባለሦስት እግር፡፡
ሳቅ በሳቅ LOL
ለሦስት ዓመታ በከንፈር ወዳጅነት ከቆዩ በኋላ ከሦስት ወር በፊት ሲለያዩ ለወንድየው ቀላል የሆነው መለያየት ልጅቷን አእምሮዋን በማሳት ወደ ወንጀል መርቷታል፡፡ በቴክሳስ ጠቅላይግዛት ነዋሪ የሆነችው ኤልሳቤጥ ማክሌይን ከወንድ ጓደኛዋ ከተለያየች በኋላ ህይወቱን ቀውጢ በማድረግ በቀን እስከ መቶ ጊዜ ስልክ ትደውልለት ነበር፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው ወጣትም ለፖሊስ ያመለክታል፡፡
እርሷም ከተለያዩ ስልኮች መደወሏንና ማስፈራራቷን ቀጠለች፡፡ በቀን እስከ 750 ጊዜ ድረስ በመወደልና በአንድ ጊዜ እስከ 126 አጭር ፈጣን መልዕክት (ቴክስት) በመላክ ህይወቱን መቅኖ ቢስ አደረገችው፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ግን የልጁን እናት በመኪና በመግጨት ወደ መንገድ ከጎተተቻት በኋላ በሞትና ህይወት መካከል ጥላት ለቀድሞው የከንፈር ወዳጇ “ህይወት እንዴት ነው ሳቅ በሳቅ (LOL)” በማለት አጭር መልዕክት ትልካለች፡፡ እናትየው በርካታ የአጥንት ስብራትና ጉዳት ደርሶባት በህክምና የእየተረዳች ሲሆን ኤልሣቤጥ በወንጀል ተከስሳ የ65ሺህ ዶላር የገንዘብ ዋስ ተበይኖባታል፡፡
የሳምንቱ ምርጥ ፎቶ
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሚጓጓዙበት ካዲላክ ባለአራት እግር ታንክ ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡ ከ300ሺህ ዶላር በላይ ወጪ የፈሰሰበትና የአርፒጂ ጥይት የማይበሳው ይህ መኪና አሠራሩና ውስጡ ያካተተው ቁስና መከላከያ እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ለዚህ ሳምንት መርጠነዋል፡፡
ለማንኛውንም የባዮኬሚካል ጥቃት እንዳይጋለጥ ልዩ መከላከያ ይለብሳል፡፡

ቀጥተኛ ጥቃት ቢደርስበት እንኳን እንዳይፈነዳ የነዳጅ ማጠራቀሚያው ልዩ ስፖንጅ ለብሷል፡፡
አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የፕሬዚዳንቱን ዓይነት ደም በተጨማሪ ይቀመጣል፡፡
ከፊትለፊት በምሽት ማየት የሚያስችልና አስለቃሽ ጋዝ ተደምደውበታል፡፡
ጎማው በቀላሉ በስለትና ሹል ነገሮች መበሳት እንዳይል የተደረገ ሲሆን ባጋጣሚ ጎማው ቢተነፍስ ቸርኬው ያለችግር መሽከርከር ይችላል፡፡
ከውስጥና ከውጭ የለበሰውና የተሰራበት እንደ አሉሚኒየም፣ ቲታኒየም፣ … ያሉት መኪናውን በእርግጥም ተንቀሳቃሽ ምሽግ የሚያስብለው ነው፡፡
በሮቹ እንደ ቦይንግ 757 የፓይለቶች በር ጋር ይመሳሰላል ቢባልም ከውስጡ ያለው መከላከያ እጅግ የተቀቀ ነው፡፡
ስለ መስታወቱ ብዙ ማለት ባይቻልም በርካታ ርብራብ ያለውና ጥይቶችን በቀላሉ እንደ ቤዝቦል ጓንቲ አፍኖ የሚያስቀር ነው፡፡
ዋጋው ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገሩ ውድነው፤ በሰዓት 60ማይል ብቻ የሚሄድ ሲሆን በአንድ ጋሎን (3.7ሊትር) 8 ማይል (wd 13ኪሎሜትር) ብቻ ነው የሚጓዘው::
ምስሉ ላይ በመጫን ዝርዝር መረጃውን አጉልቶ ማየት ይቻላል::
ዘገባውን ለማጠናቀር በየጽሁፉ ከጠቀስናቸው ምንጮች በተጨማሪ ሌሎችንም የሚዲያ ውጤቶች መጠቀማችንን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ከዜናዎቹ ማነስ አኳያ በየጸሁፉ ለመግለጽ ባለመቻላችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment