Translate

Saturday, December 22, 2012

የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ተመሰረተ



www.ginbot7pf.org በሚል ድረ ገጽ ላይ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል የሚባል ድርጅት መመስረቱ ተገለጸ ።  መግለጫውን ያወጣው የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል እንዳብራራው ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓም ” የወያኔን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በትጥቅ ትግል ለማስወገድ “የግንቦት7 ሕዝባዊ ኃይል” የሚል ስያሜ የሰጠነውን፣ በሃገር ወዳድና ለህዝብ ተቆርቋሪ በሆኑ ወጣቶች፣ ምሁራንና ዜጎች የተሞላውን ድርጅት መመሥረታችን በዛሬው እለት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ እናበስራልን” ብሎአል።
“የሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት፤ የዜጎች መብቶች፣ ሃገራዊ አንድነት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበሩባት ጠንካራና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ሆኖ የማየትን ራዕይ የሰነቀ ድርጅት መሆኑን” የገለጸው ህዝባዊ ሀይሉ፣ መንግስትን በኃይል የማስወገድ፤ ሰላማዊና ዲሞክራሲ የሥልጣን ሽግግር በሃገሪቱ እንዲኖር የማስቻል እና ከማንኛዉም የፓለቲካ ድርጅት ጋር ያልወገኑ ነፃ፣ ጠንካራና ብቃት ያላቸው ህገ-መንግሥታዊ የመከላከያ፣ የፓሊስና የደህንነት ተቋማት እንዲኖሩ አስተዋጽዖ የማድረግ ተልዕኮ” ይዞ መነሳቱን ገልጿል።

ህዝባዊ ሀይሉ “በሃገራችን በወያኔ አምባገነናዊ እብሪት ያልታፈነ፣ ያልተዋረደና ያልተዘረፈ የሃገሪቱ ዜጋ እንደማይገኝ ገልጾ፣ ሹማምንቱ በሃብት ላይ ሃብት፤ በድሎት ላይ ድሎት ሲጨምሩ፣ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ ግን መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መንገላታት፣ መታሰር፣ መደብደብና መገደል ሆኗል” ብሎአል። “የወያኔ  የአመጽ እብሪት በሕዝባዊ አመጽ የሚተነፍስበት ሁኔታ  እስካልመጣ ድረስ፣ ወያኔ መብታቸውን ከመጠየቅ ውጭ ምንም እንከን የሌለባቸውን ንጹሃን ዜጎች ከማሰር፣ ሰቆቃ ከመፈጸም፣ ከመግደል ከማሳደድና  ከማፈናቀል” እንደማይቦዝን ህዝባዊ ሐይሉ ገልጿል።
የግንቦት7 ህዝባዊ ሀይል ” ዜጎች በሽብርተኛነት እየተከሰሱ በእድሜ ልክ እስራት ሲቀጡና ሰቆቃ ሲፈፀምባቸው የታዘባችሁ ወጣቶች፤ ለሃይማኖት እኩልነት በመታገላቸው በእስር ላይ እየማቀቁ፣ እየተገረፉና እየተሰቃዩ ያሉ የሙስሊም ምዕመናን ተወካዮች ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ወገኖች፤ በቤተክህነትና በክርስትና ተቋማት ላይ እየተፈፀመ ያለው ደባ የሚያንገበግባችሁ ፤ ለወያኔዎችና ሸሪኮቻቸው እድገትና ምቾት ሲባል ከይዞታችሁ የተፈናቀላችሁ፤ ገቢን ሳይሆን ወገንተኛነትን መስፈረት ባደረገ መመዘኛ ከአቅም በላይ የሆነ የወያኔ ግብር፣ ታክስና መዋጮ የተማረራችሁ ነጋዴዎች፤ ማኅበራችሁ በወያኔ ፈርሶ ወይም ተጠልፎ የጋራ ድምፃችሁን የምታሰሙበት፣ ከቀጣሪያችሁ ከወያኔ  ጋር ፍትሃዊ የጉልበታችሁን ዋጋ ክፍያ መደራደሪያ ያጣችሁ ላብአደሮች፣ መምህራን፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች፤ ምንም አይነት የአካዳሚ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ ጥራቱን ያልጠበቀ ትምህርት እንድትከታተሉ የተፈረደባችሁ፣ ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ከየኮሌጁና ከየዩንቨርስቲው ስትመረቁ እጣችሁ ድንጋይ ማንጠፍ የሆነው ወጣት ተማሪዎች” ትግሉን ተቀላቀሉ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ህዝባዊ ሀይሉ “አደገኛ በረሃዎችንና ባህሮችን በማቋረጥ ለመሰደድ ልባችሁ እየከጀለ ላሉ ወጣቶች፣ በአረብ ሃገራት ለባርነት ስራ ተሽጠው እጣቸው ተገዶ  መደፈር፣ በፈላው ወሃ መቀቀል፣ መደብደብ፣ መዋረድና ከፎቅ ላይ እየተወረሩ ክቡር ህይወትን ማጣት ለሆነው ሴቶች፣  ለሃገር አንድነትና ክብር መሰለፍ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው እንደ ባዕድ ጦር የተበተኑና የተገፉ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በሚታየው ዘረኛነት እየተቃጠሉ፣ በሕዝብ ላይ ዝመቱ በተባሉ ቁጥር ከህሊናቸው  ጋር መዳማት የመረራችው የኢትዮጵያ ወታደሮች እና በድህነት አስገዳጅነት፣ እንዲሁም በሌሎችም ማስፈራሪያዎችና ጫናዎች የወያኔ/ኢህአዴግ ድርጅቶች አባል የሆኑ ወገኖች በሙሉ” ጥሪውን ሰምተው ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጠይቋል።
በ http://www.ginbot7pf.org ድረገጽ ላይ የወጣው ዜና እንደሚያመለክተው ህዝባዊ ሀይሉ ራሱን በትጥቅና በሰው ሀይል አደራጅቷል።

No comments:

Post a Comment