Translate

Wednesday, December 26, 2012

የሚያስቅና የሚያሳቅቅ የፍርድ ቤት ውሎ


ዕለቱ “በእነ ኤልያስ ክፍሌ የፍርድ መዝገብ” ምስክርነት ይሰጣል የተባለበት ዕለት ነበር። በዚህ መዝገብ ውብሸት ታዬ፣ አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሄር፣ ሂሩት ክፍሌ እና ርዮት አለሙ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

እነ ውብሸት ታዬ መጀመሪያ ሲታሰሩ በቴሌቪዥን የሰማነው “የቴሌ እና የመብራት ሃይል ተቋማትን ማፈራረስ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ መሞከር” የሚል ነበር። ከዛ እያደር እያደር አቃቤ ህግ በምን እንደከሰሳቸው ረሳው መሰለኝ፤ ለምስክርነት በሄድንበት ጊዜ የሰማነው አንድም ከመብራት ሃይልና ቴሌኮሚዩኒኬሽን ጋር የሚያያዝ ነገር አልነበረውም። አረ ልብ ብለን ካየነውማ ከህገ መንግስቱም ጋር የሚጋጭ ነገር አላየንበትም።  
ለማንኛውም፤ በጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና በአቶ ዘሪሁን ላይ ለምስክርነት የቀረቡ ሶስት ልጆች ነበሩ። ሶስቱም  የምንመሰክረው እውነት ካልሆነ አቡነ ገሪማ ይገልብጡን ብለው ማህላ ፈፀሙ።
በነገራችን ላይ አቡነ ገሪማ አድዋ ውስጥ የሚገኙ ቁጡ ፃድቅ ናቸው። ከየት ትዝ አሉኝ…? ሌላ ጊዜ እርሳቸውን የሚመለከት ጨዋታ ይኖረን ይሆናል… እድሜ እና ማሳታወሱን ከሰጠን!
ወደ ማስታወሻችን ስንመለስ፤ መስካሪዎቹ ከአድዋው አቡነ ገሪማ ይልቅ የአድዋውን መለስ የሚፈሩ እና የሚያከብሩ መሆናቸው ያስታውቅባቸዋል። እንዴት ማለት ጥሩ ጥያቄ ነው… ይከተሉኝማ፤
የመጀመሪያው መስካሪ መጣ፤ የመኖሪያ አድራሻውን ሲጠየቅ የጎዳና ተዳዳሪ ነኝ አለ። ወዘናው ግን አይመስልም። እሺ ይሁንለት… ቀጥል ተባለ…
“ቦና ታከለ ከተባለ የቡቲክ አስተናጋጅ ጋር ሆነን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ “በቃ!” የሚል ፅሁፍ ፅፈናል አለ።
ሁለተኛው መስካሪ መጣ የመኖሪያ አድራሻ ተጠየቀ። ድንቡሽቡሽ ያለው ልጅ ሞልቀቅ ብሎ፤ “ቦሌ” ይላል ብለን ስንጠብቅ ምስኪን ለመምሰል እየሞከረ የጎዳና ተዳዳሪ ነኝ አለን። ይሄኔ እውነቱን ንገረኝ ካሉኝ የጎዳና ተዳዳሪ መሆን ተመኘሁ። የጎዳና ተዳዳሪነት እንዲህ የሚያሳምር ከሆነ ከቤታችን ውስጥ ምን እየሰራን ነው? ስል ራሴን ጠየኩ። ለማንኛውም ምስክርነቱን እንስማ፤
“ቦና ታከለ ከሚባል ሊስትሮ ሰራተኛ ጋር በመሆን “በቃ” የሚል ፅሁፍ ፅፈናል” አለ። ቆይ ቆይ ቆይ የመጀመሪያው ልጅ የቦና ታከለን ስራ ምን ነበር ያለው…? ማስታወሻዬን ገለጥ ገለጥ ሳደርጋት “የቡቲክ አስተናጋጅ” ይላል። ይሄኛው ደግሞ በአንድ ጊዜ ሊስትሮ አደረገው። “እሺ… ስንት ሰዓት ላይ ነበር የፃፋችሁት?” “ከሌሊቱ አስራ አንድ ሰዓት።” ልብ አድርጉልኝ የመጀመሪየው መስካሪ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነበር ያለው። ገድ ፈላ…
ቀጥሎ ቦና ታከለ ራሱ መጣ። እሰይ አሁን እውነቱን ከዋናው ሰው ልንሰማ ነው። ቦና ለመሆኑ ስራህ ምንድነው?፡”ሶፍት ነጋዴ ነኝ!” (ያዝ ቀበሌ ይላሉ የኛ ሰፈር ልጆች የማይሆን ነገር ሲሰሙ።) የቦና ታከለን ስራ አንደኛው ጓደኛው የቡቲክ አስተናጋጅ ሲለው ሲለው ሌላኛው ደግሞ ሊስትሮ አለው። ራሱ ሲመጣ “ሶፍት ነጋዴ ነኝ” አለን። እነዚህ ጓደኛማቾች ሳይሆኑ ጉደኛማቾች ናቸው! እያልኩ በሆዴ እያንሰላሰልኩ ምስክርነቱን መስማት ቀጠልኩ…
አቶ ዘሪሁን ባዘዘኝ መሰረት “በቃ” የሚል ፅሁፍ በየአደባባዩ ፅፈናል። ይሄኔ ዳኛው የጠየቁት ነው የማይረሳኝ “ምንድነው የበቃው…?” አሉት። ልጁ ፈራ… ትንሽ ቁልጭ ቁልጭ አለ። ደግመው ጠየቁት “ምንድነው የበቃው?” “መ… መለስ በቃ” ይሄኔ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የታፈኑ ሳቆች ከዚህም ከዛም ሹልክ ሹልክ እያሉተሰሙ። ዳኛው ቆጣ ብለው ስነ ስርዓት! አሉ እና ቦና ቀጠለ…
ስንት ሰዓት ነበር የምትፅፉት? ሲባል ምን አለ መሰልዎ…? “ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ” አለ። ግራ ተጋባን እንዲህ ያለ ሃራምባ እና ቆቦ፣ ባሌ እና ቦሌ ጉለሌ እና ሰላሌ… አረ እንደውም እነዚህ ይቀራረባሉ እንደነ ቦታ ታከለ አይነት የተራራቀ ምስክርነት ሰምቼ አላውቅም። ለዛውም መፅሐፍ ተይዞ ተምሎ ይገልብጠኝ ተብሎ የተገለባበጠ ምስክርነት… ብዙዎቻችን “ምንድነው ጉዱ” በሚል ርስ በርስ እየተያየን ቀጠልን!
ሂሩት ክፍሌ ላይ ምስክር ሊሆን የቀረበው አንድ ወጣት ነበር። በነገራችን ላይ ሂሩት ክፍሌ በጣም የሚገርም አይነት የእስር እድል ነው ያላት። መንግስት ደንገጥ ባለ ቁጥር ዘሎ ነው የሚያስራት። ለምሳሌ በቅንጅት ጊዜ ታስራለች። ከዛም ቀጥሎ ደግሞ፤ “ከአርበኞች ግንባር ጋር አብራችኋል” ተብለው ወደ አርባ የሚጠጉ ሰዎች ሲታሰሩ ታስራለች። አሁንም ደግሞ አሸበርሽ ተብላ ነው የታሰረችው። በአንድ ወቅት በቃሊቲ እስር ቤት ሄጄ ስጠይቃት እንደውም “መጣ የተባለ ፋሽን አያልፋትም” እንደሚባሉ ፋሽነኛ ሴቶች፤ አንቺ ደግሞ መጣ የተባለ እስር አያልፍሽም ማለት ነዋ…? ብዬ ልቀልድ ሙከራ አድርጌያለሁ።
በሂሩት ላይ ምስክርነት የቀረበው ወጣት “መካኒክ ነኝ” አለን። እሺ እስቲ ቀጥል መካኒኩ፤ ሂሩት ክፍሌን የማውቃት በ97 ዓ.ም አብረን ታስረን በነበረ ጊዜ ነው። አለ። ወንድ እና ሴት አስር ቤት የመተዋወቅ እድላቸው ምን ያህል ጠባብ እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል።
እንኳን ሌላ ቀርቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ውስጥ የተወለደ የገዛ ልጁንም ሆነ ባለቤቱን ማየት ባለመቻሉ ነበር የልጁን ስም “ናፍቆት” ያለው።   
ለማንኛውም “ምስክሩ” ቀጠለ። “እርሷ ባለችኝ መሰረት ሃዋሳ ከተማ ሄጄ አመፅ የሚቀሰቅስ ወረቀት ለጥፊያለሁ” አለ። ለዚህም ገንዘብ ተቀብያለሁ። ሲል ጨመረልን። ገንዘቡ የምንድነው? ቢባል… “የእኔ ክፍያ እና ለቀለም መቅዣ ነበር” አለን።  ጥሩ… ከዛስ…? “ከዛ…” አለና ትንሽ አሰብ አድርጎ… “ከዛ… እኔ በዘጠና ሰባትም ዓመተ ምህረትም በዚሁ ጉዳይ ታስሬ ስለነበር፡ ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለ ወንጀል መስራት ስላልፈለኩ ለፖሊስ ጠቆምኩ” ብሎን እርፍ…!
አረ በህግ አምላክ መካኒኩ… ሀዋሳ ሄጄ ወረቀት ለጥፊያለሁ ብለሃልኮ… ብዬ ጮኬ ልናገር ምንም አልቀረኝም።   
ምስክርነቱ ቀጥሏል። በርዮት አለሙ ላይ የቀረበችው ምስክር የርዮት ጓደኛ ነበረች። እሺ እንዴት መጣሽ…? ተባለች። “ፖሊስ አስገድዶኝ!” በሆዳችን አይዞሽ አልናት። ግና ፖሊስ አስገዳጆችን ይከላከል እንጂ ያስገድድ ዘንድ ደግ ነውን…? ይህንንም በሆዳችን የጠየቅነው ነው…!
“ምንድነው የምትመሰክሪው?”
“ለርዮት ካሜራ አውሻት አውቃለሁ እና እርሱን ትመሰክሪያለሽ ተብዬ ነው የመጣሁት” እሺ ቀጥዬ… “ጓደኛዬ ስለሆነች ካሜራም ሆነ ሆነ እስክርቢቶ እንዋዋሳለን፤ ካሜራው እርሷ ስትፈልግ እርሷ ጋር እኔ ስፈልግ ደግሞ እኔ ጋር ይሆናል” አለች። ከዛም በቃ ይህንኑ እንድትናገር ነው የመጣችውና ጨረሰች።
ታድያ ይሄ ወንጀሉ ምንድነው? ካሜራ የተዋዋስን በሙሉ ልንታሰር ነው ማለት ነው? ግራ የሚያጋባ ምስክርነት ነበር። ቴሌን መብራት ሃይል እና ህገመንግስቱ የሚናዱት በፎቶ ካሜራ ነው? እንኳን ሌላው ቀርቶ “በቃ” የሚል የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ቴሌን እንዴት የወድመዋል? መብራት ሃይልንስ እንደምን ያፈርሰዋል? (ስንል ጠይቀን መልስ ስናጣ ራሳችን በሳቅ ፈረስን!)
እዝችጋ አንድ የዘጠና ሰባት ቀልድ ትምጣ…
ያኔ አሉ ሁለት ፖሊሶች አብረው እየሄዱ ነበር። በወቅቱ፤ አብዛኛዎቹ፤ የአዲሳባ ከተማ ፖሊሶች በመንግስት አመኔታን አጥተው ታማኝ ካድሬ የሆኑ ፖሊሶች ብቻ ከፌደራል ፖሊስ ጋር እየተጣመሩ ነበር ጥበቃ የሚያደርጉት። ታድያ አንድ ካድሬ ፖሊስ እና አንድ ፌደራል ፖሊስ አብረው እየሄዱ ሳለ፤ የፌደራል ፖሊሱ አንድ ጥያቄ ካድሬ ቀመሱን ፖሊስ ይጠይቀዋል።፡
“ባለፈው ወጣቶቹ አውቶብስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ የነበረው ለምንድነው?” ብሎ ጠየቀ። ካድሬ ብጤውም “ያው ህገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ ነዋ!” አለው በርሱ ቤት ጨዋታ ማሳመሩ ነው። ይሄኔ ፌደራሉ ትንሽ አሰብ አደረገና እንግዲያስ መንግስት ነው ጥፋተኛ…! አለ። ካድሬው የአዲሳባ ፖሊስ ደንገጥ ብሎ እንዴት…? ቢለው ግዜ “ህገመንግስቱን ለምን በአውቶብስ ይዞት ይዞራል…?” ብሎ ጠየቀው አሉ።
እናላችሁ ወዳጆቼ… በአሁኑ ሰዓት በነገርኳችሁ አይነት የተጣረሱ የሚያስቅና የሚያሳቅቅ የፍርድ ቤት ምስክርነቶች ሁሉም ተከሳሾች ከአስራ አራት አመት በላይ ተፈርዶባቸዋል። ርዮት አለሙ ብቻ ይግባኝ ጠይቃ ወደ አምስት አመት ዝቅ ተደርጎላታል።
እውነቱን ለመናገር መንግስታችን ጣጣ የለውም “አንጥሴ” የሚሉትን ራሱ ህገመንግስቱን እና ተቋማትን በሀይል ለመናድ እንደማሴር አድርጎ ሊያስመሰክርብዎ ይችላል። ግን ማስነጠሳችንን አንተውም! (ሃሃ..ተቀኘን ማለት ነው!?)   

No comments:

Post a Comment