Translate

Tuesday, March 22, 2016

የማያልቀው ወያኔያዊ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ስቃይ

ይህ ጽሑፍ በመጀመሪያ በገጠሪቱ የጠገዴ ኣካባቢ ተወላጅ በሆኑ የስኳር በሽተኛ የነበረውን ልጃቸው በዳንሻ ኣካባቢ በሚገኘው በዲቪዥን ሆስፒታል በየሁለት ወሩ ክትትል እያስደረጉ ሲያሳክሙ የነበረውን፣ በመጨረሻም ከ3 አመት በፊት ሆስፒታሉ ውስጥ በሞተባቸውና እንዲሁም ባለቤታቸውን የዛሬ 5 ኣመት እዛው ሆስፒታል ውስጥ ባጡ ኣባት ለልጃቸው ናማ ጻፍልኝ ብለው በልጃቸው ጸሓፊነት በአባት ተራኪነት ለልጃቸው “በል እንግዲህ ይህ ለኣለም አሰማልኝ”  ብለው በነገሩት መሰረት በልጃቸው ዘመድ በኩል ደርሶን የተዘጋጀ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የሚደርሰውን ግፍ በጥቂቱም ቢሆን የሚያሳይ ነው። ለሁለቱም ልጃቸውና ሚስታቸው ወደ ጎንደር ሪፈር ጻፉልኝ ብለው ሃኪሞቹን እየለመኑዋቸው ሳለ ደህና ናቸው እየተባሉ እንደሞቱባቸው ይገልጻሉ።  እኝህ ኣባት ይህ “አልበቃ ብሏቸው ደግሞ…”
ይላሉ “የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በግድ ትግሬ ነን በሉ እያሉ በየቤታችን እየዞሩ ያስፈራሩናል” ይላሉ…. “ከእንግዲህስ እንተላለቅ እንደሆን እንጂ በማንነታችን እንኳ ከንግዲህ ብሗላ ኣንደራርደርም” ብለው ማስጠንቀቂያ ያዘለ ሃሳባቸውንም ይገልጻሉ።
ይህን ጽሑፍ በማንበብ የህዝቡን ስቃይ እንኳን ተካፈሉሏቸው….. ከዛም ስቃያቸው ይብቃ ብላችሁ ዘብ ቁሙላቸው!!! ጽሑፉ ከታች ይቀጥላል፤ መልካም ንባብ::
በጠገዴ ወረዳ በዳንሻ አካባቢ በግምት ወደ 35 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ የድሮ ያከባቢው ስሙን ቀይረው “ኣዉረራ” ወይንም ደግሞ “ዲቪዥን” የሚል ኣዲስ ስም አውጥተው የወልቃይት ጠገዴን የኢኮኖሚ “የጀርባ ኣጥንት” የሆነ ኣካባቢ በአሁኑ ስአት ደግሞ ወያኔ እንደስኳር አገዳ አኝኮ የተፋቸውን የድሮ ታጋዮቹ በከፍተኛ የገንዘብ ፍሰትና እርዳታ እንዲሁም ዘመናዊ  ሆስፒታል በ1983  የዛሬ 25 አመት 25,000 ወታድሮቹን ከነሙሉ ትጥቃቸው ያሰፈረበት ውብና ሰፊ መሬት ነው። ይህ ቦታ የወልቃይት ጠገዴ የእርሻ ቦታ የነበረ ብቻ ሳይሆን ከብቶቻቸውን የሚያረቡበትና ወደ ታችኛው ሰፊ የእርሻ ቦታቸው የሚያልፉበትም ነው። አካባቢው ለምን “አዉረራ” ወያንም ደግሞ “ዲቪዥን” ብለው አዲስ ስም አወጡለት ብትሉ አዉረራ ማለት “አስወረራት” ማለት ሲሆን ዲቪዥን  ደግሞ ከቀጥታ የእንግሊዝኛ ቃሉ የተወሰደ ሲሆን “ማከፋፈል” እንደማለት ነው። የምነግራቹህ ቦታ እጂግ በጣም ሰፊና ለም መሬት ያለበት ሲሆን በቡድን በቡድን ነው የተከፋፈሉት ማለትም የአድዋ የአክሱም ወዘተ እያለ ማለት ነው። ክፍፍሉ በቁጥር የተደረገ ሲሆን ከባዶ 01 ጀምሮ እስከ 07 ይደርሳል። ዜሮው ማስፈሩ እንደሚቀጥል ነው የሚተነብየው:: እና በግድ “ወረን ተከፋፍለናታል” ብለው እራሳቸውን ሰይመው ይኖራሉ:: ይህ ኣካባቢ የEFFORT “ህይወት ሜካናኢዝድ እርሻ ኢንዱስትሪ” መገኛ ማእከልም ነው:: ይህ እርሻ ኢንዱስትሪ ብዙ ገበሬዎችን ያለምንም ካሳ እያፈናቀለና እየገደለ ወደ ድህነት መቀመቅ የከተተበት የእርሻ ኢንዱስትሪ ነው።
እነዚህ ወታደሮች ለወልቃይት ጠገዴ ህዝብ እጅግ በጣም የመረረና የከረረ ጥላቻ ያላቸው ናቸው ። ወያኔ ለስንትግዜ በምን ኣይነት ዘዴ ለምን አላማ ኮትኩቶ እዚህ ደረጃ ለደረሰ አመለካከት እንዳደረሳቸው እግዜር ብቻ ነውየሚያውቀው። ያካባቢው ሰዎችና ንብርቶቻቸው ለምሳሌ ከብቶቻቸው በዛ መንቀሳቀስ ኣይችሉም። ከተገኙ በርግጠኝነት ይወረሳሉ፤ ባለቤቱም ተፈልጎ ይታሰራል ደግሞም ከነቤተሰቡ ጭምር ነው እንጂ። ፖሊስ ናቸው እንዳትል  አይደሉም፤ “ጡረትኛ ነን” ሲሉ ይደመጣሉ ግን ደግሞ ሴቶቹም ወንዶቹም እስካፍንጫቸው ድረስ የታጠቁ ናቸው። ከሌላ አካባቢ የመጣ ከሆነ በዋነኝነት ከአማራ ወይንም ከኦሮሞ የመጡ ከሆነ ደግሞ በተለይ ደግሞ መታዎቂያቸው ከሌለና ወይንም የማይነበብ ከሆነ እጣ ፈንታው እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው:: ነገር ግን ባወሳሰዳቸውና ወካባቸው ሁኔታ ወስደው ምን ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው። እነዚህ ሰዎች የፈለጉትን ለማድረግ ሙሉ ነጻነት ተሰቷቸዋል ከፈለጉም ለክልሉ መንግስትም ቢሆን ደውለው የሚያስፈራሩ ጀግኖች ናቸው:: ታዲያ ፖሊስ ፍርድ ቤት ምናምንቴ ብሎ ነገር የላቸውም:: የምታዩት ነገር ወጣ ያለና ግርምትን የሚፈጥር ነው፤የወልቃይት ጠገዴን በቁም ለማሰር የተቀመጡ ባለሙሉ ስልጣንና ነጻ ኣውጭ ቡድን ናቸው። ያስራሉ፣ይደበድባሉ፣ያንገላታሉ፣ ይሳደባሉ፣ ያስፈራራሉ ፤ ለራስህ በህሊናህ በሹክታ ለምን ይህ ይሆናል ስትል መልስ የለም። ብቻ ያከባቢው ሰው ሲያዩ ኣይናቸው ይቀላል፤ ደማቸው ይፈላል፤ ጅማታቸው ተገታትሮ ሲንቀጠቀጡ ታዩዋቸዋላችሁ። ከማሰርና ንብረት መዝረፍ በዘለለም በተለያየ ግዜ ታዋቂ ያከባቢው ሰዎችም የገደሉበት ሁኔታ አለ። በቃ ፍጹም የሆነ ከደርግ የባሱ ግፈኞችና ፋሺስት ናቸው። እነዚህ ወታደሮች የሚሉት ነገር ቢኖር ታግለን ሰላም ኣመጣንላችሁ ነው ፤ ሌላ የሚያወሩት ቋንቋ የላቸውም። እና በቃ ነጻነትክን 100% ሰጥተህ እሺ ብለህ ማለፍ ብቻ ነው ያለህ ኣማራጭ። እግዚኦ ምንድን ያለው ችግር ኣይገባህም በቃ ብቻ ግን ያሳዝናሉም ያበሳጫሉም።
በኣሁኑ ግዜ ወልደው ከብረው ብዙዎቹ ደህና የሚባል ኑሮ ያላቸው ናቸው፤ ሰው ሲቀየር ማየት ደስ ይላል። ኢትዮጵያውያን በመሆናቸውም ደስ ይላል ግን ያለቀቃቸው በሽታና ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው የሚያጠራጥርህ ለወልቃይት ጠገዴ ህዝብና ለሌላው ኢትዮጵያዊ ያላቸው እጂግ በጣም የመረረና የከረረ ጥላቻ ስታዩ ነው በጣም ነው የሚያሳስባችሁ። ብድግ ብለው “እኛኮ” ብለው ዲስኩራቸውን ይለቁባችሗል፤ ለዛውም ባይናቸው ከላይ ወዳታች ከታች ወደላይ  ሰዉነትህን እየገሸለጡ ነፍስህን አፈርድሜ እያበሉ ነው እንጂ። ኣብዛኛው ህዝቡ የሚፈልጋቸው መሰረታዊ የልማት ኣገልግሎት ሰጪ እንደ ህክምናና ትምህርት ቤት የመሳሰሉ እዛ ተሂዶ ነው። ህብረተሰቡ እዛ መሄድ አለበት: ለእነዚህ ሰዎች ከፍ ብዬ እንደነገርኳችሁ ዘመናዊ የተባለ ሆስፒታል የዛሬ 25 አመት ተገንብቶላቸዋል። ወደ 300 ሺ ይሆናል ለሚባለው ያከባቢው  ተወላጅ ህዝብስ ብትሉ ደግሞ ኣንድ የማይረባ ጤና ጣብያ ብቻ ነው ያለው።
እኔንም ጨምሮ ያከባቢው ሲቪል ሰው ከነርሱ ጋር መገናኘት ባይፈልግም የግድ እነርሱ ወዳሉበት ሄዶ ነው መታከም ልጆቹን ማስተማር ያለበት ግን ቀላል ኣይደለም ትራስፖርትም ችግር አለ።  ሆስፒታሉ ጋር ደርሶ ለመታከም በጣም ብዙ ፈተና ማለፍ ኣለብህ። ከዚህ የተነሳ ብዙ ግዜ ብዙ ሰው በመንገድ ይሞታል በተለይ ወላዶች። እዛ ሄዶ ከሚታከም ወደ ባህል ሃኪም አቅም ያለው ደግሞ ወደ ጎንደር ሄዶ ነው መታከም እሚመርጠው። ከምንም ተነስቶ የሆስፒታሉ በር ላይ ቆሞ መታወቂያህ ኣሳየኝ ይልሃል በቃ ሰዉን በተገኘ ኣጋጣሚ ማሰቃየት ሌላው ስራቸው ነው ማለት ይቻላል። መታወቂያ ከሌለህ ምንም እንኳን በኣስቸጋሪና ኣድገኛ ሁኔታ ላይ ብትገኝም ይመልሱሃል፤ ብትገባም ኣብዛኛው ሃኪሙ እያፋጠጠ በጣም የምት ሰቃይበትን በሽታ በ2 ደቂቃ በቁጣ መንፈስ እየገላመጠ  “በል ወደ ውጭ” ይልሃል ፤ ጭልም ብሎብህ ተስፋ ኣጥተህ ትመለሳለህ እድለኛ ካልሆንክም ሬሳህን ይዘህ ወደቤትህ ትመጣለህ። የነርሱን ሰው ግን ተነስተውና እጅ ነስተው ኣስቀምጠው አክመው ተሳስቀውና ተመራርቀው ይሽኛኛሉ። ይህን ስታይ ከበሽታህ በተጨማሪ ውስጥህ ብግን ብሎ ለጨጓራ ህመም ትጋለጣለህ። ይህን ያወቀ ያከባቢው የገጠር ታካሚ ህዝብ ቢጨንቀው ልባቸው እንኳን ቢራራ ብሎ ለሃኪሞቹ ቅቤና ሌላ እጅ መንሻ ሰጥተው ወዳጅ ኣድርገው ተለማምጠው ይታከማሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ መኖርክን ሽምጥጥ አድርገህ ክደህ ‘ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ኣገር ላይ ነኝንዴ ያለሁት?’ ብለህ ራስህን ሳትወድ በግድ እንድትጠራጠር ያደርጉሃል። በጣም የሚያሳዝነኝ ሌላው ነገር ደግሞ የነዚህ ሰዎች ልጆች በአመለካከት ከወላጆቻቸው 7 እጥፍ ክፉ ሆነው ነው እንዲያድጉ ማድረጋቸው ነው ማለትም ለአካባቢው ሰው ከወላጆቻቸው በላይ የመረረና የከረረ ጥላቻ አላቸው። ብቻ ምን አለፋችሁ ለህዝቡ ነቀርሳ ናቸው የሚል አገላለጽ ጉዳዩን የሚያቀለው ይመስለኛል።
በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ ከ1997 ወዲህ የመጡት ሰፋሪዎችም ሰርተው የሚበሉ ሰፋሪዎች ሳይሆኑ ግልጽ ታጣቂዎች ናቸው ቢያንስ ክላሽና ቦምብ ያልያዘ ሰፋሪ የለም። እነርሱ ደግሞ ጭራሽ የለየላቸው ወንበዴዎች ናቸው ብል መሳሳት ኣይሆንብኝም ማለትም በቃ ነገር ነገር የሚሸታቸው ሰዎች ናቸው:: ሳትደርስባቸው የሚደርሱብህ፣ በሱሪያችን ነው የምንኖረው ምናምን እያሉ ትግስትህን እየተፈታተኑ ወዳልሆነ ውሳኔ የሚገፋፉህ፣ ምንም የማያውቁትን ምስኪን ፍጥረቶችን ለምሳሌ ብዙ ከብቶችን ባንድ ግዜ በማጤ ወገባቸውን የሚሰብሩ፣ የእነርሱን ነገር ስለምናውቅ እኛ ቆመን እንኳ ስናያቸው  በእልህ ትልልቅና ጥንታዊ ዛፎችን ላይጠቀሙበት ቆርጠው የሚጥሉ፣ ገበሬዎቹን የሚደበድቡ እልም ያሉ ወንበዴዎች ናቸው። ሙቀት በሚሆንበት ግዜ ወዳገራቸው  የሚሄዱ ክረምት ሲሆን የሚመጡ ከትግራይም ከወልቃይት ጠገዴም ከሁለቱ መሬት ያላቸውና የሚያርሱ ጥጋበኛ ወንበዴዎች ናቸው። እነዚህ ደግሞ ከድሮዎቹ የሚለያቸው በጣም ሰፊ የሆነ ቦታ ከወልቃይት ጠገዴ ከወደ ጎንደርም ኣዋሳኝ የሆኑ ቀበሌዎች ጭምር የተሰጣቸው ስልጡን ወታደሮችና ፈጣን  ነጋዴዎች ናቸው። በኣጭር ግዜ ውስጥ ባለመኪናና በከተማ ውስጥ ባለቤት የሆኑ ናቸው። ያከባቢው ኗሪ ህዝብ ግን ከቀን ወደ ቀን በድህነትና በሽታ የሚማቅቅ እንጂ እድገት የሚያሳይ ኣይሆንም።
የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ስቃይ ተጽፎ ስለማያልቅ በዚህ ልቋጨውና እነዚህ ወታደሮች ምንም እንኳን በጉልበታቸው ሰፍረው ብዙ ግፍ የፈጸሙ ቢሆንም ኢትዮጵያዊነታቸው አምነው እስከተቀበሉ ድረስ  መኖራቸው ጥሩ ነው እኔ በበኩሌ ደስ ይለኛል:: ቢሆንም ግን ለወልቃይት ጠገዴ እንዲሁም ለሌላ ኢትዮጵያዊ ያላቸው የተንሸዋረረ ኣመለካከትና ጭፍን ጥላቻ ካልተቀየረ ግን የህበረተሰቡ የታፈነ ትዕግስት እየተፈታተነ  ጫፍ ሲደርስ ኣደጋ  አለው ብዬ ስላመንኩበት ነው ይህን ጽሑፍ ጻፍልኝ የምልህ ልጄ እንጂማ የነርሱን ክፋት ለመዘርዘር እንዳልሆነ እንዲታወቅልኝ ኣሳስባለው ፤ በእርግጥ ብዘረዘረውም ፍትሃዊ ነው ብዬ ኣምናለው። በመጨረሻም እግዚኣብሔር ስቃዩና ስቅላቱ በቃቹህ ብሎን ከወገኖቻችን ጋር በሰላም የምንኖርበት ግዜ ያምጣልን በማለት የጥልቅ  ሃዘናቸውን መርሻ የሆነውን ተስፋቸውን በቃላቸው ገልጠዋል።

No comments:

Post a Comment